1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፣ ግንቦት 8 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2008

ቁጡ ነበሩ ግን ዝነኛ፤ ብዙዎችንም ለዝና አብቅተዋል፤ ዶክተር ወልደ-መስቀል ኮስትሬ። እሁድ ግንቦት 7 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ ማክሰኞ የቀብር ስርዓታቸው ይፈጸማል። 75 ሺህ ተመልካች የሚይዘው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም መጸዳጃ ቤት የተዘነጋ ቦንብ የማንቸስተር ዩናይትድ የመጨረሻ ጨዋታ እንዲስተጓጎል ሰበብ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/1Ioma
Monaco Woldemeskel Kostre Bester Trainer des Jahres 2006
ምስል Getty Images/AFP/V. Hache

ስፖርት፣ ግንቦት 8 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ቦንቡ እንዴት ተረሳ? ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው። የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ 26 ተጨዋቾችን መርጠዋል። እነማን ተመርጠው እነማን ቀሩ? በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የ18 ዓመቱ ወጣት የዓለም ዝነኞችን ልቆ አንደኛ ወጥቷል። በዕለቱ የተፈጠረ ክስተት ግን ዋነኛ ተፎካካሪዎችን ከውድድሩ አስወጥቷል።

ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ አረፉ

ከ30 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ እና እግር ኳስ ስፖርት ዘርፍ አገልግለዋል። በተለይ በአትሌቲክስ መስክ ስማቸው ገኖ ይሰማል። ከበርካታ የኦሎምፒክ ድል ጀርባ የእሳቸው ጥረት እና ምክር አለበት፤ አሠልጣኝ፣ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ። ወደዚህች ዓለም የመጡት በ1942 ዓ.ም. እንደሆነ «ከሳተና ሯጮች በስተጀርባ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ» የተሰኘው የሕይወት ታሪካቸውን የሚያዘክረው መጽሐፍ ይጠቀሳል።

ለክብር እና ዝናቸው በማይመጥን፦ አዲስ አበባ፤ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው አነስተኛ አፓርትመንታቸው ሕመማቸውን እየቻሉ አራተኛውን ፎቅ ተመላለሱበት። ትናንት ግን አልቻሉም። ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬን በቅርበት በመከታተል የሕይወት ታሪካቸውን የጻፈው ጋዜጠኛ እና የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ፍቅር ይልቃል ዝነኛውን አሠልጣኝ ሲገልጥ «ከባርሴሎና እስከ ቤጂንግ በነበሩ ኦሎምፒኮች በአትሌቲክሳችን ከተመዘገቡ ውጤቶች ጀርባ ያሉ ሰው ናቸው።» ይላቸዋል። «ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ካስመዘገበቻቸው 48 ሜዳሊያዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሆኑት በቀጥታ በእኚህ አሠልጣኝ መሪነት የተገኙ ናቸው። እናም በጣም በውጤታማነት የምናከብራቸው አሠልጣኝ ናቸው» ሲል ይገልጣቸዋል።

ወደ 20 የሚጠጉ ምዕራፎችን አካቶ በ2006 ዓ.ም. የታተመው የዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬን የሕይወት ታሪክ ያካተተው መጽሐፍ ሰሜን ሸዋ እንደተወለዱ ይጠቅሳል። ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ የሕመማቸው መነሻ የሆነው የመኪና አደጋ አጋጣሚ አስገራሚ መሆኑን የመጽሐፉ ደራሲ ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ይናገራል።

ኢትዮጵያን በታላላቅ የኦሎምፒክ ውድድሮች ለድል ያበቁት አሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ከስማቸው ጋር የሚመጥን ሕይወት ሳይገፉ እንዳለፉም ይዘረዝራል።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የአሠልጣኞች ሽልማትን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ዓመት ያገኙት የረዥም ርቀት አሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ-መስቀል ኮስትሬ በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም መለየታቸው እንዳሳዘነው ዓለም አቀፉ ማኅበር ገልጧል።

እግር ኳስ

ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር
ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበርምስል picture-alliance/dpa/S.Nogier

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ እና በርመስ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ሊያከናውኑ የታቀደበት ጊዜ ሊደርስ ግማሽ ሰአት ሲቀረው አንስቶ ትናንት ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም በጭንቅ ተይዛ ነው የቆየቸው። ፖሊስ ስታዲየሙ ውስጥ የታደሙ ተመልካቾች ገሚሱ ወደ ውጪ እንዲወጡ የተቀሩት ደግሞ ባሉበት ረግተው እንዲቆዩ በማሳሰብ በአነፍናፊ ውሻ መላ ስታዲየሙን ሲያሥሥ ነበር።

ዘግየት ብሎ እንደተሰማው የውጥረቱ ሰበብ ቀደም ሲል ስታዲየሙ ውስጥ የደኅንነት እና ጥበቃ ልምምድ ሲያደርግ የነበረ የግል ኩባንያ ለልምምድ ያስቀመጠውን ቦንብ በመርሳቱ ነው ተብሏል። ቦንቡ በባለሙያዎች ቁጥጥር እንዲፈነዳ ተደርጓል። ፖሊስ ግን ቦንቡ እንዴት ሊረሳ እንደቻለ ለማወቅ በጥልቀት ምርመራዬን እቀጥላለሁ ብሏል። የማንቸስተር ዩናይትድ እና የበርመስ ጨዋታም ለነገ ተሸጋግሯል።

ትናንት በተደረጉ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቀደም ሲል ዋንጫ የማግኘት የጠበበ ዕድል የነበረው ቶትንሀም ሆትስፐር በጠበበ ልዩነት የሁለተኛነት ዕድሉንም አስረክቧል። ድንቅ ጨዋታ በማከናወን አስቶን ቪላን 4 ለ0 ያንኮታኮተው አርሰናል ከቶትንሀም ሆትስፐር በአንድ ነጥብ በልጦ ባገኘው 70 ነጥቡ የሁለተኛነት ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በዚህም መሠረት አርሰናል ሌስተር ሲቲን ተከትሎ፣ ቶትንሀም ሆትስፐርን አስከትሎ የሚቀጥለው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል።

ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም የቦንብ ስጋት
ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም የቦንብ ስጋትምስል Getty Images/A. Livesy

እሁድ ከስዋንሲ ሲቲ ጋር አንድ እኩል የወጣው ማንቸስተር ሲቲ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ማለፉን አረጋግጧል። ምናልባት ደረጃውን በማንቸስተር ዩናይትድ ሊነጠቅ የሚችለው ማንቸስተር ዩናይትድ በርመስን በ18 ግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻለ ብቻ ነው። ሆኖም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የአውሮጳ ሊግ ቦታውን ማስጠበቅ ችሏል። 63 ነጥብ ያለው ሳውዝሐምፕተንም ትናንት ክሪስታል ፓላስን 4 ለ1 በመርታት የአውሮጳ ሊግ ደረጃውን አስከብሯል።

60 ነጥብ ይዞ በስምንተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የሊቨርፑል አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ለአውሮጳ ሊግ ብዙም ትኩረት የሰጡት አይመስልም። ይልቁን ረቡዕ ከስፔኑ ሴቪላ ጋር በሚኖራቸው ፍልሚያ የአውሮጳ ሊግ የዘንድሮን ዋንጫ በእጃቸው ካስገቡ ድሉ ጣምራ ሆነላቸው ማለት ነው። ምክንያቱም በቀጥታ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆናቸው ይረጋገጣል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ሮይ ሆድግሰን ለዩሮ 2016 ግጥሚያ የመረጧቸውን 26 ተጨዋቾች ይፋ አድርገዋል። የማንቸስተር ዩናይትዱ የ18 ዓመት ወጣት አጥቂ ማርኩስ ራሽፎርድ ቡድኑ ውስጥ ተካቷል። የመጨረሻውን ማጣሪያ ግን ወደፊት አልፎ የቡድኑ 23 አባላት ውስጥ መግባቱ ገና አልተወሰነም። የኒውካስል ዩናይትዱ የክንፍ ተጨዋች አንድሮስ ቶውንሴንድ እና የአርሰናሉ አማካይ ጄክ ዊሼርም በአሠልጣኝ ሮይ ሆድግሰን ሰኔ 3 ፈረንሣይ ውስጥ በሚጀምረው ውድድር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

የአርሰናሉ ቲዮ ዋልኮት፣ የኤቨርተኑ ፊል ሃጊይልካ አለያም የዌስትሐም ዩናይትዱ ማርክ ኖብልን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ግን ቦታ አላገኙም፤ በአሠልጣኙ አልተጠሩም። ሀሪ ኬን በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ትዊተር አድራሻው፦«በእንግሊዝ ቡድን በመታቀፌ ደስ ብሎኛል። ከልጆቹ ጋር ለመገናኘት ቸኩያለሁ» ሲል ጽፏል። የቶትንሀም ሆትስፐሩ ጂሚ ቫርሲ እና የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ እንዲሁም የሊቨርፑሉ ዳንኤል ስቱሪጅ በቡድኑ ከተካተቱት ታዋቂ ተጨዋቾች መካከል ይገኙበታል። በዩሮ 2016 የሚሳተፉ 24ቱም ቡድኖች 23 ተጨዋቾችን ያካተተውን ቡድናቸውን እንዲያስመዘግቡ የተሰጣቸው ቀነ-ገደብ ሊያከትም 15 ቀናት ብቻ ይቀሩታል።

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና የዋንጫው ባለቤት በሆነበት የቅዳሜው ግጥሚያ ሉዊስ ሱዋሬስ ግራናዳ ላይ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። በላሊጋው 40 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍም ከሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ5 ግቦች በልጦ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗል። የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ 26 ግቦችን በማስቆጠር ሦስተኛ ወጥቷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሐኖቨር እና ሽቱትጋርት ወደ ሁለተኛ ዲቪዢዮን ወራጅ ሆነዋል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በቡንደስሊጋው በሚቀጥለው ዙር መቆየቱን ለማረጋገጥ ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው ኑረንበርግ ጋር የደርሶ መልስ ግጥሚያ በማድረግ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ኑረንበርግ ትናንት ፓዴርቦርንን 1 ለ0 አሸንፎ ነው ለዚህ የደረሰው። ፓዴርቦን ወደ ሦስተኛ ዲቪዚዮን አሽቆልቁሏል።

ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ የዳነው ቡድን አይንትራኅት ፍራንክፉርት አሠልጣኝ
ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ የዳነው ቡድን አይንትራኅት ፍራንክፉርት አሠልጣኝምስል picture-alliance/dpa/K. Lenz
የሊቨርፑል አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ
የሊቨርፑል አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕምስል Getty Images/O.Scarff

ባየር ሙይንሽን፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባየር ሌቨርኩሰን ለሻምፒዮንስ ሊግ አልፈዋል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ አራተኛ በመውጣቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያን ተቆናጧል። ሻልከ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊ መሆኑ ተረጋግጧል።

ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮች

የኬንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም በሕግ እንደሚያስጠይቅ ደንግጓል። ሆኖም ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፉ መሥሪያ ቤት (WADA) ኬንያ ሕጓን በማሻሻል ለዓለም አቀፍ ደንብ ልትገዛ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል። ዋዳ የኬንያ ምክር ቤት የደነገገው ሕግ ጥድፊያ ይታይበታል ብሏል። ኬንያ ውስጥ የስፖርት ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሳዲቅ ሳባኒ ከናይሮቢ

«በርካቶች የሚተቹት ሕጉ በጥድፊያ በመደንገጉ ነው። የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ ያልመከሩበት በችኮላ የተረቀቀ ሕግ በመሆኑ ነው የተተቸው። ሕጉ ዋዳ ያሳስቡኛል ሲል የጠቀሳቸውን በርካታ ነጥቦች መዳሰሰ ያሻዋል። ያም ብቻ አይደለም በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ ስለሚሆኑበት መንገድ ማረጋገጫ መስጠት መቻል አለበት።»

ብራዚል ውስጥ ሊከናወን የታቀደው የሪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከሦስት ወራት ያነሱ ጊዜያት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት ዋዳ እስካሁን ኬንያን በተመለከተ ለምን ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰ ብዙዎችን አስደምሟል። በእርግጥ በረዥም ርቀት አትሌቲክሱ ዘርፍ የኬንያ እና የኢትዮጵያ ተሳትፎ በብዙዎች በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ኢትዮጵያም ቢሆን የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም በርካታ አትሌቶች መጠርጠራቸው እና መመርመራቸው ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ያመላክታል።

የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የስፔን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም የ18 ዓመቱ ወጣት ሆላንዳዊ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ትናንት አንደኛ በመውጣት ታሪክ ሠርቷል። በፎርሙላ አንድ የውድድር ታሪክ ማክስ በዕድሜ ትንሹ እና በአጭር የውድድር ጊዜያት ለድል በመብቃት የመጀመሪያው ሰው መሆን ችሏል።

የስፔን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ የ18 ዓመቱ ወጣት ሆላንዳዊ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን
የስፔን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ የ18 ዓመቱ ወጣት ሆላንዳዊ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐንምስል Getty Images/AFP/L. Gene

ቀደም ሲል በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም በዕድሜ አነስተኛ ሆነው የመጀመሪያ ውድድራቸውን ካሸነፉት የዓለም ምርጦች በዕድሜ ትኑሹ ነው ማክስ። ሚሻኤል ሹማኸር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1992 ዓመት የቤልጂየም ግራንድ ፕሪ የመጀመሪያ ውድድሩን ያሸነፈው በ23 ዓመቱ ነበር። ሌላኛው የዓለም ባለድል ሌዊስ ሐሚልተን በ2007 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያሸነፍ የ 22 ዓመት ወጣት ነበር።

የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሆኖ በ18 ዓመቱ የአንደኛነትን ማዕረግ የተጎናጸፈው ወጣት አሽከርካሪ ማክስ በፎርሙላ አንድ ስማቸው ገናና የሆኑትን በሙሉ ልቆ ተገኝቷል። በውድድሩ የፌራሪ አሽከርካሪዎች ኪም ራይኵነን እና ሰባስቲያን ፌትል የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። የመርሴዲስ አሽከርካሪዎቹ ኒኮ ሮዝበርግ እና የዓለም ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን በመጀመሪያው ዙር ሽቅድምድም እርስ በእርስ በመላተማቸው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ