1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 4 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 4 2012

ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ድንቅ ጨዋታ አከናውነው ውጤት ግን አልቀናቸውም። ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ቡድን ሳምንት ከቡሩንዲ ጋር ይጋጠማል። አጠር ያለ ዘገባ ይኖረናል። ብቸኛዋ ኢራናዊት የኦሎምፒክ ባለድልድ ከእንግዲህ ኑሮ በኢራን በቃኝ ብላለች።

https://p.dw.com/p/3W8tx
Äthiopien Sport l Frauenmannschaft U20
ምስል DW/O. Tadele

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ድንቅ ጨዋታ አከናውነው ውጤት ግን ስላልቀናቸው ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አጠር ያለ ዘገባ ይኖረናል። ብቸኛዋ ኢራናዊት የኦሎምፒክ ባለድልድ ከእንግዲህ ኑሮ በኢራን በቃኝ ብላለች። በሴትነቷ ከኢራን ባለለሥልጣናት ከፍተኛ በደል እንደደረሰባት የተናገረችው አትሌት ኔዘርላንድ ትገኛለች። የጫካ ሰደድ እሳት በሚለበልባት አውስትራሊያ ታዋቂው የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ውድድር ነገ ይጀመራል። የአየሩ ኹኔታ እጅግ አሰሳሳቢ ነው ተብሏል። ጀርመናዊው የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋች ማሪዮ ጎይትሰ የእግር ኳስ ቀጣይ እጣ ፈንታው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።  ምናልባት ማሪዮን ሊፈልጉት ይችላሉ የተባሉ ሁለት ቡድኖች በቡንደስሊጋው እና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቢኖሩም የዶርትሙንድ ቆይታው ግን ያበቃ ይመስላል። 

ፕሬሚየር ሊግ

Fußball UK Burnley vs. Manchester City
ምስል Getty Images/A. Livesey

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በተለመደ ግስጋሴው ቀጥሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የፕሬሚየር ሊጉን 61 ነጥብ ይዞ እየመራ ነው። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ቶትንሀም ሆትስፐርን 1 ለ0 ያሸነፈ ሲኾን፤ ትናንት አስቶን ቪላን የጎል ጎተራ ያደረገው ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲን በ14 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሊቨርፑል ቀጣዩን ጨዋታ ካሸነፈ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ልዩነቱ 17 ይኾናል ማለት ነው። ማንቸስተር ሲቲ አስቶን ቪላ 6 ለ1 ነው የጎል ጎተራ ያደረገው። ቸልሲ በርንሌይን 3 ለ0፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ኖርዊች ሲቲን 4 ለ0 አሸንፈዋል። ኒውካስትል ከዎልቭስ አንድ እኩል ተለያይቷል። ዋትፎርድ ቦርሞስን ትናንት 3 ለ0 ድል አድርጓል። ላይስተር ሲቲ በሳውዝሀምፕተን 2 ለ1 ሲሸነፍ፤ ኤቨርተን ብራይተንን፤ ሼፊልድ ዩናይትድ ዌስትሀምን 1 ለ0 አሸንፈዋል። በ67ኛው ደቂቃ ላይ ማክስ ማየር ላይ በፈጸመው ከባድ ጥፋት ፒየር ኤሜሪክ አውባሜያንግን በቀይ ካርድ ያጣው አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ጋር ቅዳሜ ዕለት አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ጥሏል። አርሰናል 28 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይስተር ሲቲ 3ኛ፣ ቸልሲ 4ኛ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ 5ኛ ናቸው።

የሴቶች እግር ኳስ በኢትዮጵያ

ህንድ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አድርጋለች። ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኡጋንዳ አቻው ጋር ቅዳሜ ጥር 2 ተጫውቶ 2 ለ0 ተሸንፏል። ቡድኑ በቂ ልምምድ እና ዝግጅት እንዳላደረገ ቢነገርም ኡጋንዳ ውስጥ ያከናወነው ጨዋታ ግን ድንቅ እንደነበር የኡጋንዳ ቡድን አሰልጣኝ አዩብ ካሊፋ አልሸሸጉም። አዩብ ቡድናቸው የኢታዮጵያ አቻው ላይ ጨዋታው በተጀመረ 4ኛ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን ግብ በዡሊየት ናሉኬንጌ ቢያስቆጥርም ተፎካካሪው ጠንካራ እንደነበር መስክረዋል።

Äthiopien Sport l Trainer Samuel Abera
ምስል DW/O. Tadele

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በበኩላቸው ቡድናቸውን የዝግጅት ጊዜ ማነስ እንደጎዳው ተነግሯል፡፡ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ለሁለት ሳምንታት ብቻ ተዘጋጅቶ ወደ ውድድር የገባውን ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወደፊት በቂ የዝግጅት ጊዜ አንዲሰጥ ከጨዋታው አስቀድመው አሳስበው ነበር። ከሽንፈቱ መልስ አሰልጣኝ ሳሙኤል የሚከተለውን ብለዋል፡፡

በዙር ግጥሚያው ከኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ አሸናፊ የሚኾነው ቡድን በማጣሪያው ከታንዛኒያ እና ቡሩንዲ አሸናፊ ከአንዱ ጋር ይገጥማል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንም በመጪው ቅዳሜ ከሜዳው ውጪ የማጣሪያ ጨዋታውን ከብሩንዲ ጋር ያደርጋል። ብሔራዊ ቡድኑ ተመሳሳይ የዝግጅት ጊዜ ማጠር ችግሮች እንደገጠመው ለማወቅ ተችሏል። በአጠቃላይ የሴቶች እግር ኳስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገቢው ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ስብሰባ ያደረገ ሲኾን፤ የወንዶች ቡድን ቁጥር መጨመሩን እና የሴቶች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጧል። ፌዴሬሽኑን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በፕሬዝደንትነት አንዲመሩ አዲስ አበባ ውስጥ እሁድ ጥር 3 በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት አቶ ፍትኅ ወልደሰንበት በስፖርቱ ያለውን የደከመ የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በጥረት ላይ አንደሚገኙ ለዶይቼ ቬሌ (DW)ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Sport l Frauenmannschaft U20
ምስል DW/O. Tadele

የበጀት ችግር በስፋት በሚታይበት የእጅ ኳስ ስፖርት የወንድ ክለቦች ቁጥር ባለፉት አራት ዓመታት ከነበረበት 3 ወደ 12 ቢያድግም የሴት ቡድኖች አለመቋቋማቸውን እንደድክመት አንስተዋል፡፡ የሴት ቡድኖች የሚቋቋሙ ከሆነም የውስጥ ሊግ ውድድር በፍጥነት ለመጀመር መታሰቡን አቶ ፍትኅ አስረድተዋል፡፡ በሌሎች ስፖርቶች በተለይም በእግር ኳስ ላይ ለሴቶች የሚሰጠው ትኩረት በቅርብ ጊዜያት እያነሰ ቢመጣም በእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ተገቢውን ክትትል ለማድረግ መታቀዱን ፕሬዝደንቱ ጨምረው ጠቅሰዋል። ለሁለቱም ዘገባዎች መረጃዎቹን የላከልን የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛው ኦምና ታደለ ነው።

የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዝውውር ዜና

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የተጨዋቾች ዝውውር ጎላ ብሎ አልታየም። በስፔን ላሊጋ ግን ባርሴሎና የቶትንሀም አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖን ለማስመጣት ንግግር እያደረገ ነው ተብሏል። ባርሴሎና ሉዊስ ሱዋሬዝን የሚተካ ተጨዋችም ያስፈልገዋል።

Champions League - Group F - FC Barcelona v Borussia Dortmund
ምስል AFP/J. Lago

የባርሴሎናው አጥቂ የ32 ዓመቱ ሉዊስ ሱዋሬዝ በደረሰበት የቀኝ ጉልበት ጉዳት ለሚቀጥሉት አራት ወራት መሰለፍ እንደማይችል ተገልጧል። የፊታችን እሁድ ባርሴሎና ከግራናዳ ጋር በሚያደርገው የሴሪኣው ግጥሚያ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ የሱዋሬዝ አለመኖር ቡድኑን ይጎዳዋል ተብሏል። ሱዋሬዝ በላሊጋው ባስቆጠራቸው 11 ግቦች እስካሁን ሦስተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ነው። በተጨዋቾች የዝውውር መስኮቱ ከ18 ቀናት በኋላ ከመዘጋቱ በፊት ባርሴሎና ሉዊስ ሱዋሬዝን የሚተካ ተጨዋች ካላስፈረመ ምናልባት ፈረንሳዊው አጥቂ አንቷን ግሪዝማን ተክቶት ሊጫወት ይችላል።  

ማንቸስተር ዩናይትድ የስፖርቲንግ ሲፒ አማካይ ፖርቹጋላዊው ብሩኖ ፌርናንዴስን ለማስመጣት 65 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡ ተገልጧል።  የቤኔፊካው አማካይ ጌድሶን ፈርናንዴስ ደግሞ የህክምና ምርመራ አድርጎ ቶትንሀም ሆትስፐርን እስከ ነገ ድረስ ሊቀላቀል ይችላል ሲል ስካይ ስፖርት ዘግቧል።  ለዲስ ስፖርት እንደዘገበው ደግሞ አርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ የዋትፎርዱ ተከላካይ ክርስቲያን ካባሴሌ ላይ ዐይናቸውን ከጣሉ አራት የፕሬሚየር ሊጉ ቡድኖች ሁለቱ ናቸው። ዌስትሀም ዩናይትድ እና ኒውካስልም ተከላካዩን ወደ ቡድናቸው ማስመጣት ይፈልጋሉ። የቶትንሀሙ አማካይ ክርስቲኢን ኤሪክሰን ደግሞ ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ጋር የአራት ዓመት ተኩል ውል ለመፈረም መስማማቱን የጣሊያን መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል።  ዴንማርካዊው አማካይን ለመልቀቅ ቶትንሀሞች 17 ሚሊዮን ፓውንድ መጠየቃቸው ተዘግቧል።

Fußball Bundesliga Schalke 04 v Borussia Dortmund
ምስል Imago Images/M. Müller

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና የቦሩስያ ዶርትሙንድ አማካይ የ27 ዓመቱ ማሪዮ ጎይትሰ በቡድኑ ውሉ ባለመራዘሙ ወደፊት ለየትኛው ቡድን ተሰልፎ እንደሚጫወት ጥያቄ አጭሯል። የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ምናልባት በአፍላ ወጣትነቱ ወቅት አሰልጣኙ የነበሩት ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ወደ ሊቨርፑል ሊያመጡት ይችሉ ይኾናል ተብሏል። ማሪዮ በቡንደስሊጋው ሔርታ ቤርሊንም ሊሄድ ይችላል እየተባለ ነው። እንደ ማሪዮ ሁሉ ሔርታ ቤርሊን ዡሊያን ድራክስለር፤ ኤሚር ቻን እና ሞሐመድ ዳውድ ላይ ዐይኑን ጥሏል። ማርዮ ጎይትሰ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የማሸነፊያዋን ግብ በማስቆጠሩ ምንጊዜም ይታወሳል።

አትሌቲክስ

የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) የቀድሞ ኃላፊ ላሚን ዲያክ የሩስያ ስፖርተኞች የአደንዛዥ ዕጽ ቅሌትን ለመሸሸግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ተቀብለዋል በሚል ዛሬ ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ ክስ ተከፈተባቸው። የ86 ዓመቱ ሴኔጋላዊው ምንም ጥፋት የለብኝም ብለዋል። ላለፉት ሦስት ዓመታት በቤት ውስጥ እስረኛ ኾነው ምርመራ ሲደረግባቸው የቆየው ላሚን ዲያክ ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ የ10 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል። የፍርድ ሒደቱ ከዐሥር ቀናት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሏል።

IAAF Präsident Lamine Diack Peking China
ምስል picture-alliance/dpa/W.Hong

በሪዮ ኦሎምፒክ ለሀገሯ ብቸኛውን ሜዳሊያ ያስገኘችው የ21 ዓመቷ ወጣት ኢራናዊት አትሌት ኪሚያ ዓሊዛዴኅ  ደረሰብኝ ባለችው ጾታዊ በደል እና እንክብካቤ ማጣት የተነሳ ኢራንን እስከወዲያናው ተሰናብታ ኔዘርላንድ መግባቷን ዐስታውቃለች። ኢራን ውስጥ ተንሰራፍቷል ያለችው «ግብዝነት፣ ውሸት፣ ፍትኅ ዕጦት እና ቅጥ አልባ አጉል ሙገሳ» ሀገሯን ጥላ እንድትሰደድ እንዳስገደዳት ገልጣለች። «ልበሺ ያሉኝን ስለብስ አድርጊ ያሉኝን ሳደርግ ቆይቻለሁ» ያለችው ኢራናዊት «በይ ያሉኝን ሳስተጋባ» ነበር በማለት እያንዳንዱን ዐረፍተ ነገር ሳይቀር ባለሥልጣናቱ ካሉዋት ውጪ መናገር አትችል እንደነበረም አክላለች። «እንደ እቃ ነው የምንታየው» በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢራናውያን በተመሳሳይ ጭቆና ውስጥ ናቸውም ብላለች።

ኪሚያ በሪዮ ኦሎምፒክ የቴክዋንዶ ፍልሚያ ለሀገሯ የነሐስ ሜዳሊያ በማስገኘት ታሪክ አስመዝግባለች። ወደፊት ለኢራን ፈጽሞ እንደማትሰለፍ የተናገረችው ኢራናዊት አትሌት በቀጣዩ የቶክዮ ኦሎምፒክ የመወዳደር ዕቅድ አላት። በምን መልኩ እንደምትሰለፍ ግን አልተገለጠም።

Kimia Alizadeh | 2016 Rio Olympics - Taekwondo
ምስል Reuters/I. Kato

የጫካ ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጥፋት ባደረሰባት አውስትራሊያ እጅግ የሚጠበቀው የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ነገ ይጀምራል። በእሳት ቃጠሎው የተነሳ ዐየሩ በመበከሉ ውድድሮች በዝግ አዳራሾች ውስጥ ይከናወናሉ ተብሏል። የፎርሙላ አንድ ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን በዚህ የጫካ ሰደድ እሳት ቃጠሎ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚውል ግማሽ ሚዮን ዶላር ርዳታ ለማበርከት ቃል መግባቱ ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ