1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2009

በደብሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ለድል በቅተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ዘንድሮ ምን ነካው? አስብሏል። በ15 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ  አሽቆልቁሏል። ቸልሲ ቀንቶት ደረጃውን አሻሽሏል።

https://p.dw.com/p/2RxON
Marathon 2003 in Frankfurt
ምስል AP

የጥቅምት 21 2008 ስፖርት

ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ተመሳሳይ ነጥብ ይዘው በግብ ልዩነት ብቻ የደረጃ ሰንጠረዡ  ላይ ተናንቀዋል። በተለይ ሊቨርፑል በአጠቃላይ የዚህ ዓመት ውድድር ከሁሉም የላቀ ብቃት አሳይቷል። በሜክሲኮው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሰባስቲያን ፌትል በሁለት ሰአት ልዩነት ሦስተኛ፣ አራተኛ እና አምስተኛ እንደወጣ ተነግሮታል። ፌትል በሻምፓኝ ተራጭቶ ወዲያው እጅግ በተበሳጨበት ምሽት የሀገሩ ልጅ የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ኒኮ ሮዝበርግ በሁለተኛነት አጠናቋል። የብሪታንያው ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ በምሽቱ የአንደኛነትን ድል ተጎናጽፏል። የፍጻሜው ድል ግን ወደ ጀርመናዊው አጋድላለች።  

አትሌቲክስ
ትናንት በተከናወነው 37ኛው የደብሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመጎናጸፍ ለድል በቅተዋል። በትናንቱ ውድድር ደረጀ ደበሌ ቱላ (2:12:17) በመግባት አንደኛ ወጥቷል። ለሁለተኛ ደረጃ ድል የበቃው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተፎካካሪ ደረጀ ኡርጌቻ በዬቻ የገባበት ሰአት (2:14:38) ነው። አሰፋ ለገሰ በቀለ ደግሞ  (2:15:01) አጠናቆ ሦስተኛ ወጥቷል። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር የናሚቢያ አትሌት ሔላሊያ ጆንሰንስ አንደኛ ወጥታለች። የገባችበት ሰአት  (2:32:31) ነው። በአንድ ሰከንድ ልዩነት ለጥቂት ሁለተኛ የወጣችው ኢትዮጵያዊቷ እህቴ ገብረየስ ናት።

Irland Dublin Straßenszene
ማራቶን የተከናወነባት የአየርላንድ ሪፐብሊክ መዲና ደብሊን ከፊል ገጽታምስል Imago/Imagebroker

በፍራንክፉርት የማራቶን ውድድር ትናንት በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ማሚቱ ዲሣቃ ሙሊሳ (2:32:31) በመግባት አንደኛ ወጥታለች።  ጀርመን እና ኬንያ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል። በወንዶች ፉክክር ኬንያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው ገብተዋል። 

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ከፊታችን ዐርብ አንስቶ ለሦስት ቀናት እንደሚከናወን ተገልጧል። በዚህ ምርጫ ላይ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት አዲስ አበባን ወክሎ የሚወዳደር ይኾናል። 

እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ድል ተቀዳጅተው ደረጃቸውን አስጠብቀዋል። ሦስቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 23 ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ቸልሲ በ22 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ15 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። ከትናንት በስትያ ከበርንሌ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል።

ዌስትሐም ትናንት በኤቨርተን 2 ለ0 ተቀጥቷል። ከትናንት በስትያ ቀዳሚዎቹ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ተጋጣሚዎቻቸው ላይ አራት አራት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚው ማንቸስተር ሲቲ 4 ለ0 የረታው ዌስት ብሮሚችን ነው። ተከታዩ አርሰናል ሰንደርላንድን 4 ለ1 ሸኝቷል። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ክሪስታል ፓላስን የረታው 4 ለ2 ነው። ቸልሲ ትናንት ሳውዝሐምፕተንን 2 ለ0 ድል ነስቷል።

Fußball Chelsea Diego Costa
የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ ምስል Reuter/Toby Melville

የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ ትናንት ያስቆጠራት ግብ ተደምራለት እስካሁን 8 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ የብዙ ኳስ አግቢነቱን መሪነት ተቆናጧል። የማንቸስተር ሲቲው  ሠርጂዮ አጉዌሮ እና የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካኩ እያንዳንዳቸው 7 ግብ በማስቆጠር ይከተሉታል። 

እስካሁን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የቀድሞው የኒውካስትል ዩናይትድ ተጨዋች አለን ሺረር ላይ የደረሰ የለም። የ46 ዓመቱ ሺረር 260 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የግብ አግቢዎች አውራ ነው። የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዋይኔ ሩኒ እስካሁን 194 ግቦችን አስቆጥሯል። የአለን ሺረር ኮከብ ግብ አግቢነት ክብር-ወሰን ግን በቀላሉ የሚሰበር አይመስልም። የ31 ዓመቱ ዋይኔ ሩኒ አለን ሺረር ላይ ላይ ለመድረስ 66 ግቦች ይቀሩታል። የ45 ዓመቱ አንድሬው ኮል (ብዙዎች አንዲ ኮል በሚል ነው የሚያውቁት) ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንዲ ኮል ለመጨረሻ ጊዜ ለኖቲንግሀም ፎረስት ተሰልፎ በመጫወት በጨዋታ ዘመኑ 187 ግቦችን አስቆጥሮ ጫማውን የሰቀለው የዛሬ 8 ዓመት ግድም ነው።

ዛሬ ማታ ስቶክ ሲቲ ከስዋንሲ ሲቲ ጋር 10ኛ ተስተካካይ ጨዋታውን ያከናውናል። ሁለቱም ቡድኖች በሰበሰቡት ነጥብ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ስቶክ ሲቲ በ9 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ስዋንሲ ሲቲ እስካሁን ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለቴ አቻ ወጥቷል። ነጥቡ 5 ብቻ ነው። ደረጃው ደግሞ 2 ነጥብ ብቻ ይዞ መጨረሻ ደረጃ ላይ ከተኮራመተው ሰንደርላንድ በአንድ ከፍ ብሎ 19ኛ ነው። 

ቡንደስ ሊጋ
በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ቡድን ተደጋጋሚ ስኬት እያስመዘገበ ነው። ኮሎኝ ትናንት ሐምቡርግን 3 ለ0 አሸንፏል። የኮሎኝ አጥቂ አንቶኒ ሞዴስተ በ61ኛው በ82ኛው እንዲሁም በ86ኛ ደቂቃዎች ላይ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። 50 ሺህ ተመልካቾች በታደሙበት የትናንቱ ግጥሚያ ሀምቡርጎች ሌላኛው የኮሎኝ አጥቂ ዚሞን ሶለር ተናግሯል። 

Deutschland Fußball Bundesliga - 1. FC Köln vs. Hamburger SV
ለኮሎኝ ሔትትሪክ የሠራው አጥቂ አንቶኒ ሞዴስተ ምስል picture-alliance/dpa/M. Becker

«ዘንድሮ ሊያስቦርቁን የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉን ብዬ አስባለሁ።» ያለው የኮሎኝ አጥቂ በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ቡድናቸው የሚገባውን እንዳገኘ ገልጧል። «ሐምቡርጎች ተጨዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣባቸው ጥሩ ተጫውተናል። እናም ሦስት ግቦችን አስቆጥረናል። በእርግጥ ግቦቹ ይገቡናል» ሲልም አክሏል። 

የሐምቡርጉ ተከላካይ ጆሀን ጆሩ በበኩሉ «ከቀይ ካርዱ በፊት በጣም ጥሩ ነበር የተጫወትነው። ከዚያ በፊት ግን ለኮለኖች ቀይ ካርድ ሊያሰጥ የሚችል ክስተት መሀል ሜዳ ላይ ተፈጥሮ ነበር» ሲል አማሯል። በእርግጥም የኮለኑ ተከላካይ ማርኮ ሖይልገር በ56ኛው ደቂቃ ላይ በፈጸመው ጥፋት ቀይ ካርድ ከማየት ተርፏል። እስከዚያ ድረስ ሐምቡርጎች በጨዋታ በልጠው ታይተዋል። 

ከትናንት በስትያ አውስቡርግን 3 ለ1 የረታው ባየር ሙይንሽን የጀርመን ቡንደስ ሊጋን በ23 ነጥብ ይመራል። ላይፕዚግ 21 ነጥብ አለው 2ኛ ነው። ቅዳሜ ዕለት ዳርምሽታድትን 2 ለባዶ አሸንፏል።  ሆፈንሐይም 19 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ይከተላል። ትናንት ሄርታ ቤርሊንን 1 ለ0 ሸኝቷል። ኮሎኝ በ18 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ይዟል። 

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ፉክክር አትሌቲኮ ቢልባዎ ከኦሳሱና አንድ እኩል፤ እንዲሁም ላ ፓልማ ከሴልታ ቪጎ 3 ለ3 አቻ ወጥተዋል። ኤስፓኞላ ሪያል ቤቲስን 1 ለምንም አሸንፏል። አይበር ቪላሪያልን 2 ለ 1 ሸኝቷል። ዛሬ ማታ ዴፖርቲቮ ዴ ላ ኮሩኛ ከቫሌንሺያ ጋር ይጫወታል።  

የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የሜክሲኮ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት አሸንፏል፤ ኾኖም በአጠቃላይ ነጥብ ዋነኛው ተፎካካሪ ኒኮ ሮዝበርግ ለዋናው ድል እየገሰገሰ ነው። ሰባስቲያን ፌትል ከአራተኛነት በድንገት ሦስተኛ መውጣቱ ተነግሮታል። ቆየት ብሎ ደግሞ አምስተኛ መውጣቱ ተነግሮታል። ሌዊስ ሐሚልተን በዚህ ዓመት የውድድር ክፍለ-ጊዜ የትናንቱ ድል ስምንተኛው ኾኖ ተመዝግቦለታል። የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ውስጥ መሳተፍ ከጀመረ አንስቶ ደግሞ እስካሁን ለ51 ጊዜያት ድል ተጎናጽፏል። የትናንትና ውድድር ላይ ሌዊስ ሐሚልተን ስህተት አልባ ሊባል የሚችል ፉክክር ነበር ያከናወነው። በተመሳሳይ መርሴዲስ ተሽከርካሪ የተፎካከረው ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ሁለተኛ ወጥቷል። እንዲያም ኾኖ ግን የፎርሙላ አንድ የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድር አሸናፊ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። ቀሪዎቹ የብራዚል እና የዱባይ ውድድሮች ላይ ሌዊስ ሐሚልተን አንደኛ ቢወጣ እንኳን ኒኮ ሮዝበርግ የአጠቃላዩ ውድድር አሸናፊ ሊሆን ይችላል። የሚጠበቅበት ሁለተኛ እና ሦስተኛ መውጣት ብቻ ነው። 

Mexiko Formel 1 Siegerehrung
የፎርሙላ አንድ የሜክሲኮ ውድድር አሸናፊ፥ ሌዊስ ሐሚልተንምስል Getty Images/AFP/Y. Cortez

እስካሁን በተደረጉት ውድድሮች ኒኮ ሮዝበርግ በ349  ነጥብ ይመራል። ሌዊስ ሐሚልተን በ19 ነጥብ ይበለጣል። 330 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሁለተኛ ነው። በትናንቱ ውድድር ሦስት ሰዎች በሁለት ሰአት ልዩነት ውስጥ ሦስተኛ ደረጃ የተሰጣቸው መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል። 

በመጀመሪያ ሦስተኛ እንደወጣ የተነገረው ለሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ነበር። አፍታም ሳይቆይ ግን የሦስተኛ ደረጃ የሚገባው ለፌራሪ አሽከርካሪው ሰባስቲያን ፌትል ነው ተባለ። እናም ሰባስቲያን ፌትል ወደ መድረኩ በመውጣት ዋንጫውን ተቀብሎ፣ ሻምፓኝ እየተራጨ ከሀገሩ ልጅ ኒኮ ሮዝበርግ ጋር ተቃቅፎ ቦረቀ። 

በሁለት ሰአት ልዩነት ግን ቦታው ለሱ እንደማይገባ ተገለጠ። እናም የሦስተኛ ደረጃው ለሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ዳንኤል ሪካርዶ ተሰጥቷል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተወዳዳሪዎቹ የፈጸሙት ጥፋት ተገምግሞ አምስት ሠከንድ የሚያስቀጣው አዲሱ ሕግ የፈጠረው መሆኑ ተገልጧል። የሜክሲኮው ምሽት በእርግጥም የጀርመናዊው ተወዳዳሪ ሰባስቲያን ቬትል አልነበረም። በሁለት ሰአት ልዩነት ውስጥ ሦስተኛ፣ አራተኛ እና በስተመጨረሻም አምስተኛ ደረጃ እንዳገኘ ሲነገረው ዘንድሮ አንድም ጊዜ ማሸነፍ ላልቻለው የፌራሪ አሽከርካሪ እጅግ የሚያበሳጭ ነበር።   

Mexiko Formel 1 Vettel
ሠባስቲያን ፌትል 3ኛ በመውጣቱ ተደስቶ፥ አፍታም ሳይቆይ 5ኛ ተብሏልምስል Reuters/H. Romero

የሜዳ ቴኒስ
ሲንጋፖር ውስጥ በተከናወነው የዓለም የቴኒስ ማኅበር የፍጻሜ ግጥሚያ የስሎቫኪያዋ ዶሚኒካ ቺቡልኮቫ ጀርመናዊቷ አንጄሊክ ክሬበርን አሸንፋታለች። የ27 ዓመቷ ስሎቫኪያዊት በ30 ደቂቃ ውስጥ አንጀሊካን ያሸነፈችው 6-3 እና 6-4  በኾነ ውጤት ነው። «ይኽ በሕይወቴ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቅጽበት ነው» ስትል ማሸነፏ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራለች።  ዶሚኒካ ቺቡልኮቫ የትናንቱ ድል ተደምሮላት የዓመቱ ቁጥር 5 ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተወዳዳሪ ኾና እንደምትጨርስ ተገምቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ