1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት

ሰኞ፣ መጋቢት 22 2006

ኮፐንሐገን ዴንማርክ ውስጥ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ፉክክር ኬንያውያን ፍፁም የበላይ ሆነው አጠናቀዋል። በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያውያን ሙሉ ለሙሉ እጃቸውን ለኬንያውያን ሰጥተዋል። የሊቨርፑል ግስጋሴን የሚገታ አልተገኘም። ብዙም ያልቀናው ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ነገ ማታ የጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየር ሙንሽንን ይገጥማል።

https://p.dw.com/p/1BZIW
ምስል Getty Images

ለአሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ የነገው ጨዋታ የሞት ሽረት ነው።

በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያውያን አትሌቶች ትናንት በወንድም በሴትም ተሳክቶላቸዋል። በተለይ በሴቶች ፉክክር ኬንያውያኑ ተወዳዳሪዎች በግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠቃላይ ቡድኑ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ በተርታ ተከታትሎ በመግባት ዓለምን አስደምሞዋል።

የማራቶን ሯጮች
የማራቶን ሯጮችምስል Fotolia/ruigsantos

ውድድሩን ግላዲስ ቼሮኖ በ1 ሠዓት ከ07 ደቂቃ ከ28 ሠከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች። ማሪ ዋቼራ ንጉጊ በ15 ሠከንዶች ዘግይታ በሁለተኛነት አጠናቃለች። አፍታም ሳይቆይ ከ8 ሠከንድ በኋላ ሳሊ ካፕቲች ቼፕዬጎ ሶስተኛ ሆና ስትገባ፤ ሉሲ ዋንጉዪ እና ሜርሲ ጄሮቲች ኪባሩስ በመከታተል አምስቱም በኬንያ ባንዲራ ስር ደምቀው ታይተዋል። ነፃነት ጉደታ በ1 ሠዓት ከ08 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ በማጠናቀቅ ስድስተኛ ወጥታለች። ሌሎቹ አራት ኢትዮጵያውያት፤ ፀሐይ ደሳለኝ 9ኛ፣ ገነት ያለው 10ኛ፣ ማሜ ፈይሳ 12ኛ እንዲሁም ሒሩት ዓለማየሁ 16ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

በወንዶች የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር እዛው ኮፐንሐገን ውስጥ ኬንያዊው ጄኦፍሬይ ኪፕሳንግ ከአንድ ሠዓት በታች በመግባት የዓመቱ ፈጣን ሠዓትን ማስመዝገብ ችሏል። ጄኦፍሬይ ውድድሩን በአንደኛነት ለመጨረስ የፈጀበት 59 ደቂቃ ከ07 ሠከንድ ብቻ ነው። በግማሽ ማራቶን ታሪክ ለአስር ዓመታት ያህል ልምድ ያካበተውና ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል። የሀገሩ ልጅ ሳሙኤል ፀጋይ በ59 ደቂቃ ከ20 ሠከንድ ሁለተኛ በመሆን ብር አግኝቷል። ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ሶስተኛ በመውጣት ነሐስ አጥልቋል።

ኤርትራውያን 5ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ሆነው ባጠናቀቁበት ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አዱኛ ተክሌ 9ኛ፣ ቦንሳ ዲዳ 14ኛ እንዲሁም ፍቅሬ አሠፋ 19ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የትናንትናውን የቡድን ውጤት በጥሞና ሊመረምረው ይገባል።

ከአትሌቲክስ ወደ እግር ኳስ ነው የምንሻገረው። ኤርትራ በቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ የማጣሪያ ጨዋታዎች እንደማትሳተፍ ትናንት ይፋ አደረርጋለች። «የቀይ ባሕር ግመሎቹ» የተሰኘው የኤርትራ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለማጣሪው ከደቡብ ሱዳን ጋር ሊገጥም ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ኤርትራ በርካታ ተጫዋቾቿ ለውድድር በየሄዱበት የውሃ ሽታ የመሆናቸው ነገር የተደጋጋመ መሆኑ ቢታወቅም፤ ከማጣሪያው ለምን እንደወጣች ግን የሰጠችው መግለጫ የለም።

የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች
የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾችምስል picture-alliance/dpa

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ውጤት እናምራ። ዘንድሮ የሊቨርፑል ግስጋሴ ብዙዎችን አስግቷል። ትናንት በሜዳው አንፊልድ ላይ ቶትንሐምን 4 ለባዶ እንዳይሆን አድርጎ ሸኝቷል። ኤቨርተን ፉልሀምን 3 ለ1 በሆነ አስተማኝ ውጤት ረትቷል። በትናንቱ ሌላ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ብዙም ተስፋ የሌለው አስቶን ቪላን 4 ለ1 ቢቀጣም፤ እስካሁን የሰበሰበው 54 ነጥብ ግን በ7ኛ ደረጃ ላይ ከማዝገም አልታደገውም።

ማንቸስተር ዩናይትድ ነገ ማታ ለ4 ሩብ ጉዳይ ላይ የጀርመኑ ባየር ሙንሽንን ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ በሜዳው ኦልድትራፎድ ጋብዞታል። የነገው ጨዋታ ለአሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስ የሞት ሽረት ነው ተብሏል። ሞየስ ባለታሪኩ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ተክተው ማንቸስተር ዩናይትድን ማሰልጠን ከጀመሩ ወዲህ ቡድኑ በፕሬሚየር ሊግ እስካሁን ያስመዘገበው ውጤት ለበርካታ ደጋፊዎቹ እምብዛም የሚዋጥ አልሆነም። ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰዓት የስፔኖቹ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና ካምፕኑ ስታዲየም ውስጥ ይገናኛሉ።

ቸልሲ እታች በሚገኘው ክሪስታል ፓላስ ከትናንት በስትያ 1 ለባዶ ተሸንፎ ጉድ ሆኗል። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ከትናንት በስትያ ተገናኝተው የተጋራነው ነጥብ ይበቃናል ሲሉ አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል። ለሊቨርፑል ግን የሁለቱ ነጥብ መጣል ሲሳይ ነው የሆነለት።

አሁን ሊቨርፑል ቁንጮውን በ71 ነጥብ ሊቆጣጠር ችሏል። ቸልሲ 69 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለጊዜውም ቢሆን እጅ ሰጥቷል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን ለመላቅ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸንፍ ይጠበቅበታል። ማንቸስተር ሲቲ በ67 ነጥብ ነው ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው። አርሰናል ከመሪው ሊቨርፑል በ7 ነጥቦች ርቀት ዝቅ ብሎ እጅ ነስቷል፤ 64 ነጥቦቼን ይዤ አራተኛ ደረጃዬን ግን ማንም አይነጥቀኝም ብሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከስሩ የሚገኘው ኤቨርተን ቀሪ ጨዋታውን ቢያሸንፍ እንኳን 63 ነጥብ ላይ ነው የሚቆመው።

የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬዝ 29 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አሁንም እንዳስጠበቀ ነው። የቡድኑ ልጅ ዳንኤል ስቱሪጅ በ20 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በሁለተኛነት እየተከተለው ነው። የማንቸስተር ሲቲው ያያ ቱሬ እስካሁን 17 ግቦችን አስቆጥሮ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የባየር ሙንሽኑ ሮበን ከመሀከል
የባየር ሙንሽኑ ሮበን ከመሀከልምስል dapd

ከፕሬሚየር ሊግ ወደጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ እንሸጋገር። ገና ቡንደስ ሊጋው ተጠናቆ ሳያበቃ ባየር ሙንሽን እጅግ ፈጣን በሚባል ሁናቴ ለ24ኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ተረጋግጧል። ባየር ሙንሽን ከትናንት በስትያ ከሆፈንሀይም ጋር 3 እኩል አቻ በመውጣት ከ19 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያሸንፍ ቀርቷል። እንዲያም ሆኖ ግን ባየርን ሙንሽን በሁለተኛ ደረጃ 55 ነጥብ ይዞ ከሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ23 ነጥብ ርቀት ከፍ ብሎ ለብቻው ተኮፍሷል። በደረጃ ሠንጠረዡ ሶስተኛ የሆነው ሻልካ ከዶርትሙንድ ጋር ልዩነቱ የአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን በ48 ነጥብ አራተኛ ነው። ዎልፍስቡርግ 5ኛ ቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ ደግሞ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ ትናንት ሐምቡርግን 3 ለአንድ በመርታት ለጊዜውም ቢሆን ጀርመንን ወደፊት በሻምፒዮንስ ሊግ ከሚወክሏት ቡድኖች ውስጥ ለመግባት ችሏል። የቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ አጥቂ ማክሲሚሊያን ክሩሰ ለቡድኑ ትናንት አንድ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ይህንኑ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል።

«3 ነጥብ መሰብሰባችን ለእኛ በጣም ወሳኝ ነበር። ወደ እላይ መግፋታችን እንዳይገታ አድርጓል። ቡድኑ ከ90 ደቂቃ በላይ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረጉ ታይቷል። ዛሬ እጅግ በጣም ጥሩ ነው የሰራነው። »

ትናንት ከቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ በተጨማሪ ቬርደር ብሬመን ሐኖቨርን 2 ለ1፣ አሸንፏል። ከትናንት በስትያ በተደረጉ ጨዋታዎች ፍራይቡርግ ኑረንበርግን 3 ለ2፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽቱትጋርትን 3 ለ2 እንዲሁም ማይንትስ አውስቡርግን 3 ለባዶ ረትተዋል። ዎልፍስቡርግ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 2 ለአንድ ሲያሰናብት፤ ባየር ሌቨርኩሰን ከአይንትራኅት ብራውንሽቫይግ አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ጌታፌ ቫሌንሺያን 3 ለአንድ ቀጥቷል። ሪያል ቫላዶሊድ አልሜሪያን እንደምንም 1 ለባዶ አሸንፏል። ኦሳሱና ከሪያል ሶሴይዳድ እንዲሁም ቪላሪያል ከኤልሼ አንድ እኩል ተለያይተው ነጥብ ተጋርተዋል። ከትናንት በስትያ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ራዮ ቫሌካኖን ያርበተበተበት ጨዋታ ግብ የተንበሸበሸበት ነበር። ቫሌካኖ 5 ለባዶ የግብ ጎተራ ሆኖ አምሽቷል። ባርሴሎና ኤስፓኞላን 1 ለዜሮ አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ አትሌቲኮን 2 ለ1፤ ሴልታቪጎ ሴቪላን 1 ለምንም ረትተዋል።

የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ቪክቶር ቫላዴስ
የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ቪክቶር ቫላዴስምስል Getty Images

የደረጃ ሠንጠረዡን አትሌቲኮ ማድሪድ በ76 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ባርሴሎና አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ 2ኛነቱን አስጠብቋል። ሪያል ማድሪድ 73 ነጥብ ይዞ በቅርብ ርቀት ይከተላል። የሪያል ማድሪዱ ግብ አዳኝ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ28 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እንደተቆጣጠረ ነው። የአትሌቲኮ ምድሪዱ ዲዬጎ ኮስታ 25 ግቦች አሉት፤ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ23 ግቦች ሦስተኛ ነው።

በጣሊያኑ ሴሪኣ ደግሞ ትናንት ቬሮና ጄዮናን 3 ለባዶ፣ ላትሲዮ ፓርማን 3 ለ2፣ ሮማ ሳሱዎሎን 2 ለምንም እንዲሁም ቶሪኖ ካግሊያሪን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ሳምፕዶሪያ ከፊዮሬንቲና ያለምንም ግብ ነጥብ ሲጋራ፤ መሪው ጁቬንቱስ በናፖሊ 2 ለዜሮ ጉድ ሆኗል።

እንዲያም ሆኖ ግን ጁቬንቱስ በ81 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡን በአንደኛነት እየመራ ነው። ሮማ 70 ነጥቦች ሰብስቦ በ2ኛነት ይከተላል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ናፖሊ 64 ነጥቦች ነው ያሉት። የጁቬንቱሱ ካርሎስ ቴቬዝ በ18 ከመረብ ያረፉ ኳሶች የግብ አዳኝነቱን እየመራ ነው። የቶሪኖው ሲሮ ኢሞቢሌ በ17 ግቦች ይከተላል። የቬሮናው ሉካ ቶኒ 15 ግቦች አሉት፤ ሦስተኛ ነው።

ሌዊስ ሐሚልተን
ሌዊስ ሐሚልተንምስል AP

የመኪና ሽቅድምድም። ማሌዢያ ውስጥ ትናንት በተካሄደው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪው የብሪታንያ ተወላጁ ሌዊስ ሐሚልተን አንደኛ ሆኖ አጠናቋል። ጀርመናዊው ኒኮ ሮዘንበርግ በመርሴዲስ ሁለተኛ ሆኗል። የሬድ ቡል አብራሪው ሌላኛው ጀርመናዊ ሠባስቲያን ፌትል በሶስተኛነት ነው ያጠናቀቀው። በፌራሪ መኪናው ሲምዘገዘግ የነበረው ስፔናዊው ፈርናንዶ አሎንሶ የመኪናውን ሞተር ሲያጠፋ እራሱን ያገኘው በአራተኛ ደረጃ ላይ ነው።

አጫጭር ስፖርት ነክ ዜናዎች

ሪያል ማድሪድ ለአሽሌ ኮል 8 ሚሊዮን ፓውንድ ሊከፍል ተዘጋጅቷል። ክፍያው ለሁለት ተከታታይ የጨዋታ ዘመን እንደሆነም ዘ ሰን የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ ዛሬ ዘግቧል።

ሊቨርፑል ዲጃን ሎሬን የተባለውን የሣውዝሐምፕተን የመሀከል ተመላላሽ በእጁ ለማስገባት እየጣረ መሆኑን ዴይሊ ሚረር ጋዜጣ ዛሬ አስነብቧል።

የቸልሲው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ከሰሞኑ ሊሸጡዋቸው ያሰቧቸውን ተጨዋቾች ይፋ አደረጉ። ጆሴ ልሸጣችሁ ነው ሲሉ መርዶ የነገሯቸው ተጨዋቾች፤ ሣሙኤል ኤቶ፣ ፈርናንዶ ቶሬስ እና ዴምባ ባ ናቸው። በአንፃሩ የኖቲንግሐሙ ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎው ላይ ግን አይናቸውን መጣላቸውን አልሸሸጉም።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስ በተከላካይ እጥረት እየተሰቃዩ ነው። ነገ ለሻምፒዮንስ ሊግ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙንሽንን የሚገጥሙት ሦስት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው በሌሉበት ነው። በነገው ጨዋታ ፓትሪክ ኤቭራ፣ ጆኒ ኤቫንስ እና ክሪስ ሳምሊን አይሰለፉም ሲል ዴይሊ ኤክስፕሬስ አትቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ