1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊላንድ እና የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ቀጠሮ ጉዳይ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7 2001

ከአስራ ስምንት ዓመት በፊት ከሶማልያ ተገንጥላ ነጻነትዋን ባወጀችው በሰሜናዊ ሶማልያ በምትገኘዋ ሶማሊላንድ ውስጥ እአአ ለፊታችን መስከረም ሀያ ዘጠኝ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ታቅዶዋል።

https://p.dw.com/p/Ip5N
ፕሬዚደንት ዳሂር ሪያሌ ካሂን በመዲናይቱ ሀርጌሳ ድምጻቸውን ሲሰጡምስል AP

ሆኖም፤ ምርጫው ሊዘገይ ይችል ይሆናል የተባለበት ድርጊት የዚችኑ ሀገር መረጋጋት እንደሚያናጋ እና ዴሞክራሲያዊ አመራርን እንደሚያ ለሰብዓዊ መብት የሚሟገተው ዓለም አቀፉ ድርጅት ሂውመን ራይትስ ዎች አስታውቋል። ዓለም አቀፍ ትውቂያ ለማግኘት ጥረትዋን በቀጠለችው ሶማሊላንድ ውስጥ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ብዙ ጊዜ ተላልፎዋል።

እርግጥ፡ እአአ ባለፈው 2007 ዓም መደረግ የነበረው የሶማሊላንድ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለተላለፈበት ድርጊት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ቴክኒካዊ ጉዳዮችን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። ይሁንና፡ ለሰብዓዊ መብት የሚሟገተው ዓለም አቀፉ ድርጅት ሂውመን ራይትስ ዎች ባለስልጣን ክሪስ አልቢን ላኪ ምርጫው በየጊዜው ወደፊት የሚገፋበት ድርጊት የህግ የበላይነትን ሊያስተናንስ ይችላል የሚል ስጋት ነው ያሰሙት።

« ሶማሊላንድ ምንም እንኳን ብዙ አዳጋች ሁኔታዎች ብታሳልፍምናን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ችላ ያላት ቦታ ብትሆንም፡ ዴሞክራሲያዊ አመራርን ተክላለች። ይሁንና፡ ምርጫው ካላንዳች ህጋዊ ምክንያት እስካሁን በአስራ ስምንት ወራት ተላልፎዋል፤ አሁንም እንደገና ሊራዘም የሚችልበት ስጋት መኖሩ ነው የሚገመተው። ይህም በቀላሉ መፍትሄ ሊገኝለት የሚችለው አሳሳቢ ችግር ሶማሊላንድ ባለፈው አሰርተ ዓመት ያስመዘገበችውን መሻሻል ሁሉ ሊያበላሽ ቃትቶዋል። »

ይኸው ሂውመን ራይትስ ዎች ሶማሊላንድን ምርጫ አስመልክቶ ያወጣው ዘገባው ትክክለኛ እንዳልሆነ ነው የሶማሊላንድ አምባሳደር ለዜና ምንጭ ሮይተርስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ያስታወቁት። መንግስታቸው የምርጫውን ዕለት ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚስተር አብዲላሂ መሀመድ ዱዋሌ በመግለጽ ዓለም አቀፉ በለጋሽ ሀገሮች ርዳታ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Somaliland Hargeisa Skyline
ምስል DW/Richard Lough

« ለጋሽ ሀገሮች የምርጫ ሳጥኖችን፡ የምርጫ ወረቀቶችን፡ ሌላ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለመስጠት የገቡትን የርዳታ ቃላቸውን እንዲጠብቁ ነው አሁን የምንጠብቀው። የመራጮችን ስም የያዘው ዝርዝር እንዲወጣ እየጠበቅን ነው። በጣም ድሀ ሀገር ብንሆንም ባለፉት ዓመታት ካለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ርዳታ ምርጫዎችን አካሂደናል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በወቅቱ ለጸጥታው ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሰጥተናል። እንደሚታወቀው፡ ባለፉት ጊዚያት የአሸባሪዎች ጥቃት ሰለባ ሆነናል። ስለሆነም፡ መንግስት ምርጫው ግልጽ፡ ካላንዳች ሁከት አስተማማኝ በሆነ የጸጥታ ሁኔታ ሊካሄድ የሚያስችል ዕቅድ ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። »

መንግስት ሁኔታዎች እንደሚጠብቀው ከተሳኩለት፡ ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ የፊታችን መስከረም ሀያ ዘጠኝ ለማካሄድ ነው ያቀደው።

ሶማሊላንድ በጎረቤትዋ ሶማልያ አንጻር ሰላምና ዴሞክራሲያዊ መረጋጋት የሚታይባት ሀገር ብትሆንምና ለመንግስትነት የሚያበቃትን ቅድመ ግዴታ ሁሉ ብታሟላም፡ እስካሁን ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም። ለዚሁ ጥረትዋ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አወንታዊ መልስ አለመስጠቱ ቅር እንዳሰኛቸው የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚስተር አብዲላሂ መሀመድ ዱዋሌ በማስታወቅ ይህ ለምን እንደሆን አጠያይቀዋል።

« ገሀዱ ሲታይ ነጻ መንግስት አቋቁመናል። በህገ መንግስት ላይ የተመሰረተ መንግስት አለን። ባለፉት ዓመታትም ምርጫዎች አካሂደናል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን አሁንም በኛ አኳያ አድሎአዊ መለኪያ የያዘ አሰራር ነው የተከተለው። እኛ መንግስት ለመመስረት የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተናል። ጥያቄአችን በህጋዊና በታሪካዊ ሁኔታዎች የተደገፈ ነው፤ ምክንያቱም ለመንግስትነት የሚያበቃንን በሞንቴቪዶ ውል የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ሁሉ አሟልተናልና። »

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሶማሊላንድ እውቅና ይስጥ አይስጥ የሚለው ጥያቄ በጣም የተወሳሰበ መሆኑን ይናገራሉ። የእውቅናውን ጉዳይ በተመለከተ ይላሉ፡

« ደጋፊ እና ተቃዋሚ መከራከሪያ ሀሳቦች አሉ። ብዙዎች ሶማሊላንድ እስካሁን ላሳየችው መሻሻል እውቅና ልታገኝ ይገባታል ብለው ያስባሉ። ይህ ያስገኘችውን ውጤት ያጠናክራልና። ይሁንና፡ ብዙዎች የድህረ ቅኝ አገዛዙን የአፍሪቃ ካርታ መቀየሩ ሊያስከትለው የሚችለው ሁኔታ ያሳስባቸዋል። በሶማሊላንድ በስተደቡብ የሚገኘው የሶማልያ መንግስት ደግሞ አሁንም ሶማሊላንድን እንደ አንድ ግዛቱ ነው የሚመለከተው። እና ይህ በጣም ከፋፋይ ጉዳይ ነው። አንድ ግልጽ የሆነ ጉዳይ ቢኖር ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶማሊላንድን ለብዙ ጊዜ ችላ ብሎ መቆየቱ ነው። እና ለጋሽ ሀገሮችና ዋና ሚና የያዙ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ሶማሊላንድን እንደ አንድ ነጻ መንግስት አወቁ አላወቁ፡ ይህችው ሀገር እስካሁን ያስመዘገበችው መሻሻል የሚጠናከርበትን ታታሪነት ማሳየትና የሶማሊላንድ መንግስትም የሚከተለውን አንዳንዱን መጥፎ አሰራር እንዲተው ግፊት ማሳረፍ ይገባቸዋል። »

አርያም ተክሌ/ሸዋዬ ለገሠ/DW