1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያና የውሀ ክልሉ ቁጥጥር

ማክሰኞ፣ ጥር 1 1999
https://p.dw.com/p/E0hU

ከዛሬ አምስት ዓመት አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ ከአጋሮቿ ጋር በጀመረችው ፀረ ሽብር ዘመቻ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ የባህር ኃይል መርከቦች በበባህረ ሰላጤና በአፍሪቃ ቀንድ ቁጥጥር እያካሄዱ ነው ። በዚህ ተግባር ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ካናዳ ፈረንሳይ ጀርመን ፓኪስታንና ብሪታኒያ ይገኙበታል ። የሰላም ፅናት ዘመቻ የሚባለው የዚህ ተልዕኮ አካል የሆነው የጀርመን ባህር ሀይል አዛዥ Thorston Wiedermann ለዶይቼቬለ እንደተናገሩት ይህን ተልዕኮ ለማሳካትም የአካባቢው አገራት ፖለቲካዊ ውሳኔና ስምምነት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ።
የሰላም ፅናት ዘመቻ ግብረ ኃይል በኤደንና በኦማን ባህረ ሰላጤ በአረብና በቀይ ባህር እንዲሁም በህንድ ውቅያኖስ ላይ ነው ቅኝትና ቁጥጥር የሚያከናውነው ። ግብረ ኃይሉ የሚጠብቀው ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ማይል ርዝመት ያለውን የውቅያኖስ ክልል ነው ። የባህር ኃይሉ ጥበቃውን የሚያከናውነውም ባህሮቹንና ውቅያኖሱን ከሚያዋስኑት አስራ አንድ አገራት በሀያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ነው ። በዚህ ግብረኃይል ውስጥ ተካፋይ የሆነችው ጀርመን በህዳር ወር ነበር እዚያ የሚገኘውን የባህር ኃይሏን ቆይታ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ያራዘመችው ። በአሁኑ ሰዓትም ቁጥሩ ሁለት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ የሚደርስ የጀርመን ባህር ኃይል በአፍሪቃ ቀንድ ሰፍሯል ። እዚያ የሚገኘው የጀርመን ባህር ኃይል አዣዥ ቶርስተን ቪደርማን እንደሚሉት የባህር ኃይላቸው ዐብይ ተግባር አሸባሪነትን መዋጋት ነው ።
ድምፅ
“እኛ ከየካቲት ወር ጀምሮ ሁለት ሺህ ሁለት ጀምሮ እዚህ የሰፈርነው ግልፅ የሆነ ሀላፊነት ተሰጥቶን ነው ። ይህም ሀላፊነት የሰላም ፅናት ዘመቻ በሚባለው ተልዕኮ አማካይነት አሸባሪነትን መዋጋት ነው ዐብይ ዓላማችን ። ከዚህ ውጭ በአካባቢው የሚታዩት የጦር መሳሪያ የሰዎችና የአደንዛዝ ዕፅ በስውር የማስገባትና የማስወጣት ዕንቅስቃሴዎችን መቆጣጠሩ አሸባሪነትን ከመዋጋት ጋር ሲያያዝ የሚከናወን ነው ። ይህ ነው እኛ እንድናስፈፅመው የሰጠን ሀላፊነት ። “
ይሁንና በዚህ ዕንቅስቃሴ ውስጥ የሚያጋጥም ችግር አለ ። ይኽውም ግብረ ኃይሉ ቅኝትና ቁጥጥሩን የሚያከናውነው ከየሀገራቱ የውሀ ክልል በሀያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ነው ። ከየሀገራቱ ድንበር አንስቶ ዓለም ዓቀፉ ግብረኃይል እስሚቆጣጠረው የውሀ ክልል ድረስ ባለው ውሀ ላይ በሀያ ኪሎሜትሩን ክልል ጥሰው ለማለፍ የሚሞክሩ ኃይላት የሚጠቀሙት ደግሞ ፈጣን መጓጓዣዎችን ነው ።
ድምፅ
በባህር ከመጡ ረዥሙን ዓለም ዐቀፍ የውሀ ክልል ለመቋረጥ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው እነርሱን መቆጣጠር የሚቻለውም በፈጣን ጀልባዎች ነው ። ሰፊውን የባህር ክልል ለማዳረስ ሲባል ማለት ነው ። እኛም የምናደርገው ይህንኑ ነው ። “
እንደ ጀርመን ባህር ኃይል አዛዝ ቪደርማን የአካባቢው አገራት በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀሱትን አሸባሪዎች ለብቻቸው የመቆጣጠር አቅሙ የላቸውም ።በአፍሪቃ ቀንድ የሰፈረው ዓለም ዓቀፉ ሰራዊት በጀልባና በመርከብ ብቻ ሳይሆን የአየር አሰሳና ቅኝትም ያደርጋል ። በሂሊኮፕተርና በአነስተኛ ቃኚ አውሮፕላኖች የባህር አካባቢዎችን ያስሳሉ ። አሁን እዚያ ያለባቸው ችግር ወደ የሀገራቱ የባህር ክልል ዘልቀው ለመግባት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አለማግኘታቸው ነው ። ግብረ ኃይሉ ደግሞ ከተገደበበት የሀያ ኪሎሜትር የውሀ ክልል ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ የየሀገሩ ስምምነትና ፈቃድ መኖር አለበት ። እንደርሳቸው ዕምነት የአካባቢው አገራት ስምምነት ላይ የመድረስ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነቱ ያላቸው ይመስላል ። ተግባራዊ ሊሆን የሚችለውም በፖለቲካዊ ውስኣኔና ስምምነት መሰረት ነው ። “ዓላማው ከእያንዳንዱ ሀገር ጋር በሚደረግ ስምምነት መሰረት የሚከናወን ነው ለምሳሌ በዚህ ሁኔታ ከየመን ጋር ። ስምምነቱ ለውጤት ከበቃ በየሀገራቱ የውሀ ግዛት ክልል መዝለቅ ይቻል ነበር ። ይህ ስምምነትት ኖሮ በዚህ የውሀ ክልል ላይ መንቀሳቀስ ቢቻል ተልዕኮው በጋራ የመከናወን ዕድል ነበረው ። “