1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ ላይ ያለመው ጥቃትና ብሪታኒያ

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2005

ሶሪያ ውስጥ መርዘኛ ጋዝ በመጠቀም ባለፈው ሣምንት ተካሂዶ በነበረ ጥቃት ከሶሥት መቶ የሚበልጡ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ ወዲህ የዳማስቆስን መንግሥት ተጠያቂ በማድረግ የአየር ድብደባ ለማካሄድ በዩ ኤስ አሜሪካና በአጋሮቿ የተያዘው ዝግጅት ውጣ-ውረድ እየበዛው ነው።

https://p.dw.com/p/19ZFo
ምስል Reuters

በአንድ በኩል የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች ድርጊቱ የባሸር-አል-አሣድ አገዛዝ ይሁን ወይም የዓማጺያኑ ይህንኑ የማጣራት ተግባራቸውን ገና አላከናወኑም። ሆኖም ዋሺንግተን ጥፋተኛውን ቀድማ በመለየት ለጥቃት ከወዲሁ የቆረጠች ነው የሚመስለው። እርግጥ የብሪታኒያ ከወታደራዊው ጥቃት ተሳትፎ በም/ቤት መገታት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጉዳዩን እያወሳሰበ መሄዱ አልቀረም።

የብሪታኒያ እንደራሴዎች ም/ቤት አገሪቱ ሶሪያ ላይ በሚካሄድ ወታደራዊ ጥቃት እንዳትሳተፍ በመግታት ባለፈው ምሽት ድምጽ ሲሰጥ ውሣኔው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን የክስረት፤ ለአንግሎ-አሜሪካው የጠበቀ ትስስርም ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ያልታየለት ድርጊት ነው የሆነው። ዴቪድ ካሜሮን በሶሪያ ላይ የጦር ዕርምጃ እንዲወሰድ እስከዚያው አጥብቀው ሲቀሰቅሱ መሰንበታቸው ይታወቃል።

በም/ቤቱ ድምጽ አጠጣጥ የካሜሮንን አቋም ደግፈው የባሸር-አል-አሣድን መንግሥት በመርዝ ጋዝ ጥቃት በመኮነን 272 እንደራሴዎች ድምጽ ሲሰጡ በአንጻሩ የብሪታኒያን ወታደራዊ ተሳትፎ 282 የሚሆኑ ተቃውመውታል። ወታደራዊውን ጥቃት ከተቃወሙት መካከል ከተቃዋሚው ሌበር ሌላ 30 የሚሆኑ የካሜሮን ወግ-አጥባቂ ፓርቲና ዘጠኝ የተጣማሪው ለዘብተኛ ዴሞክራቶች ወገን እንደራሴዎችም ይገኙበታል።

የብሪታኒያ ዜና ማሰራጫዎች ሰባት ሰዓታት ከፈጀ የጦፈ ክርክር በኋላ ፓርላማው ያደረገው ውሣኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ከፍተኛ ውርደት እንደሆነ ነው የዘገቡት። ካሜሮንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ዊሊያም ሄግ ባለፉት ወራትና ሣምንታት በሶሪያ አገዛዝ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወሰድ በዓለምአቀፉ መድረክ ላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲቀሰቅሱ መቆየታቸው አይዘነጋም። የሆነው ሆኖ ካሜሮን የም/ቤቱን ውሣኔ ምናልባት ባይዋጥላቸውም እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።

«ንጥረ-ነገር መሣሪያ ጥቅም ላይ በመዋሉ ግልጽ የሆነ ምላሽ መሰጠት እንደሚገባው ጽኑ ዕምነቴ ነው። ነገር ግን የዚህ ፓርላማ ፍላጎት መከበር እንዳለበትም አምናለሁ። የብሪታኒያ ፓርላማ ሕዝብ የአገሪቱ ጦር በሶሪያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረጉን ማየት እንደማይፈልግ ግልጽ አድርጎልናል። ውሣኔውን በአግባብ የተረዳሁት ሲሆን መንግሥትም ይህንኑ ተከትሎ ነው ዕርምጃ የሚወስደው»

ብሪታኒያ መርዘኛ ጋዝ በመጠቀሙ ድርጊት የዳማስቆስን መንግሥት ለመወንጀል ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ገና በአፍላው የመጀመሪያዋ ነበረች። ሶሪያን ለማጥቃት የጸጥታው ም/ቤት ሙሉ ድጋፍ መጠበቅ የለበትም ማለቷም አልቀረም። እንግዲህ መንግሥት የም/ቤቱን ውሣኔ በዚህ መልክ ጨርሶ የጠበቀው አይመስልም።

ብዙዎች እንደራሴዎች የትናንቱን ሁኔታ ከ 2003 ዓ-ምቱ የኢራቅ ጦርነት ሁኔታ ጋር አመሳስለውታል። በጊዜው የሌበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒይ ብሌይር አሰተማማኝ ያልሆነ የአሜሪካ ስለላ ድርጅት መረጃዎችን በመከተል ወታደሮቻቸውን ለጦርነት መላካቸው ይታወሳል። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በትናንቱ የም/ቤት ሽንፈት በአገሪቱ የውጭና የጸጥታ ፖሊሲ ላይ የነበራቸውን ቁጥጥር ማጣታቸውን ነው የፖለቲካ ታዛቢዎች የሚናገሩት።

የተቃውሞው ወገን መሪ የሌበሩ ኤድ ሚልድራንድ በበኩላቸው የብሪታኒያ እንደራሴዎች ም/ቤት ሕዝቡ ጦርነት እንደማይፈልግ ልሣኑ በመሆን አረጋግጧል ሲሉ ውሣኔውን አወድሰዋል። ሚልብራንድ አያይዘው እንደጠቀሱት ብዙሃኑ የብሪታኒያ ዜጎች የአገሪቱ ጦር በሶሪያ ላይ በሚካሄድ ጥቃት መሳተፉን እንደማይፈልጉ የዝንባሌ መለኪያ መጠይቅ ውጤት ያመለከተው ጉዳይ ነው። የሌበሩ መሪ የብሪታኒያና የአሜሪካ ግንኙነት የአሜሪካ ፕሬዚደንት ያለውን ሁሉ መፈጸም አለብን በሚል አስተሳሰብ ላይ መመስረት እንደሌለበት በማስገንዘብም ካሜሮንን በግድ የለሽነት አጥብቀው ወቅሰዋል።

ዩ ኤስ አሜሪካ በፊናዋ ከብሪታኒያው ፓርላማ ሽንፈት በኋላ ቢቀር የብቻ የጥቃት ዕርምጃን አማራጭ አድርጋ መመልከቷ አልቀረም። ሆኖም መከላከያ ሚኒስትር ቻክ ሄግል እንደገለጹት ዋሺንግተን በሶሪያ ላይ ለሚወሰድ ወታደራዊ ዕርምጃ ዓለምአቀፍ አበር ማፈላለጉን ገና አልተወችውም።

«ፍላጎታችን አብሮን የሚሰራ ዓለምአቀፍ ተጣማሪን ማፈላለግ ነው። በርከት ያሉ መንግሥታትም በንጥረ-ነገር መሣሪያ አጠቃቀም ሁኔታ ላይ ይፋ መግለጫ ሲሰጡ ይታያሉ። በመሆኑም ከአጋሮቻችን፣ አበሮቻችንና ወዳጆቻችን ጋር በጉዳዩ መምከሩን እንቀጥላለን»

የአሣድን መንግሥት ለመርዝ ጋዙ ጥቃት ተጠያቂ በማድረግ ወታደራዊው ጣልቃ ገብነት መደረጉን በግልጽ በመደገፍ ላይ ካሉት መንግሥታት መካከል ዋነኛዋ ፈረንሣይ ናት። በዚሁ ጉዳይ ወሣኝ የሆኑት ፕሬዚደንት ፍራንሱዋስ ኦላንድ በሶሪያ ላይ ከረቡዕ በፊት ድብደባ ሊካሄድ እንደሚችል መናገራቸውን የአገሪቱ ቀደምት ጋዜጣ ሌ-ሞንድ ውስጣዊ ምንጮቹን ጠቅሶ አመልክቷል። ኦላንድ የሶሪያን ተቃዋሚ ወገን ተጠሪዎች ተቀብለው ሲያነጋግሩ ወታደራዊው ጥቃትም በፍጥነት ሊካሄድ ይገባዋል ባይ ናቸው።

«የፖለቲካ መፍትሄ እንዲገኝ ሁሉም ነገር መደረግ ይኖርበታል። ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ብሄራዊው የተቃውሞ ሕብረት አማራጭ ለመሆን አስፈላጊውን ሃይል ሲያገኝ ብቻ ነው»

ወታደራዊው ጥቃት እንግዲህ በዚህም በዚያም የሚቀር አይመስልም። ጥያቄው ሁነኛ መፍትሄ፤ ለዘላቂ ሰላምም ዋስትና ሊሆን ይችላል ወይ ነው።

መሥፍን መኮንን

USA Präsident Barack Obama Verteidigungsminister Chuck Hagel
ምስል Saul Loeb/AFP/Getty Images
Weltkulturerbe Syrien Oase Palmyra
ምስል Fotolia/bbbar

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ