1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶርያ እና የአውሮጳ ህብረት ውሳኔ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2005

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ትናንት በብራስልስ ባካሄዱት ምክክር ላይ ህብረቱ በሶርያ ላይ የጣለው የኤኮኖሚ ማዕቀብ እንዲቀጥል ተስማሙ። ይሁንና፣ ሚንስትሮቹ ህብረቱ በሶርያ ላይ ያሰረፈውን እና የፊታችን ቅዳሜ የሚያበቃውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማራዘም ሳይሳካላቸው ቀርቶዋል።

https://p.dw.com/p/18fnV
ምስል Georges Gobet/AFP/Getty Images

ለሶርያ ተቃዋሚዎች የጦር መሣሪያ ይቀረብ አይቅረብ ለሚለው ጥያቄ ውሳኔው የያንዳንዷ የህብረቱ አባል ሀገር ውሳኔ እንደሚሆን ነው የተገለጸው። በዚሁ ውሳኔ ብሪታንያ እና ፈረንሣይ በሌሎቹ የህብረቱ አባል ሀገራት ላይ ፍላጎታቸውን መጫን ችለዋል።

የብሪታንያ እና የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ዊልያም ሄግ እና ሎውሮ ፋቢዩስ በሶርያ ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያው ማዕቀብ እንዳይራዘም በተዘዋዋሪ መንገድ በአቻዎቻቸው ላይ ጫና አሳርፈዋል በማለት የጦር መሣሪያው ማዕቀብ ያልተራዘመበትን ውሳኔ የተቃወሙት ወቀሳ አሰምተዋል። በውሳኔው ብዙዎቹ ደስተኞች ባይሆኑም፣ በስምምነት ገላጋይ ሀሳብ ላይ በይፋ እንደደረሱ ነበር ከስብሰባው በኋላ የውጭውን ተመልካች ለማሳመን የሞከሩት።

Syrien, Rebellen, Waffen,
ምስል Reuters

የብሪታንያ ውጉሚ ዊሊያም ሄግ ለሶርያ ዓማፅያን የጦር መሣሪያ ስለሚቀርብበት ሁኔታ ሁሉም በጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው ያስታወቁት።

« የጦር መሣሪያውን የምናቀርብበትን ርምጃ የምንወስደው ከሌሎች ሀገራት ከተመካከርን እና ሁኔታዎችን በሚገባ ከመረመርን በኋላ፣ እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቀደው መሠረት ብቻ ይሆናል። ይህ የዛሬው ውሳኔ ግን እየከፋ በሄደው የሶርያ ሁኔታ ወይም የአሳድ መንግሥት አልደራደርም ባለበት ድርጊት አንፃር ወደፊት ርምጃ መውሰድ የምንችልበትን ዕድል ፈጥሮልናል። » ከብዙ ሰዓታት ምክክር በኋላ ውጉሚዎቹ ደረሱት የተባለው ገላጋይ ሀሳብ ግን የሶርያን ውዝግብ ይበልጡን እንደሚያባብሰው እና የሶርያን ሕዝብ እንደማይረዳ የኦስትርያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚኻኤል ሽፒንድልኤገር በመግለጽ ለሶርያ ተቃዋሚዎች ይደረግ የሚባለውን የጦር መሣሪያ አቅርቦቱን ሀሳብ ነቅፈዋል።

Syrien Assad-Regime
ምስል Reuters

« ወደ ሶርያ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ የምናቀርብበት ሁኔታ አይረዳንም። ሰላም ያወርዳል ማለት አይደለም፣ በዚህ ፈንታ የጦር መሣሪያውን እሽቅድምድም ነው የሚፈጠረው። በኔ አስተያየት ይህ እጅግ በጣም መጥፎ ነው። በዚህም የተነሳ በሶርያ የጦር መሣሪያ እሽቅድድም እንዲጀመር አልፈልግም። የምፈልገው ውዝግቡን ሊያበቁ የሚያስችሉ የፖለቲካ ሀሳቦች እንዲቀርቡ ነው። »

ብዙ ክፍፍል ለሚታይበት የሶርያ ተቃዋሚ ቡድን የሚሰጥ የጦር መሣሪያ አክራሪዎች እጅ ይገባል በሚል በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ከተስፋፋው ሥጋት ጎንም የማዕቀቡ አለመራዘም በቅርቡ ይደረጋል የተባለውን የዤኔቩን ውይይት ሥጋት ላይ ይጥላል ባይ ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ የጦር መሣሪያውን ማዕቀብ በተመለከተ የተለያየ አቋም ቢይዙም፣ የሶርያን ሕዝብ ስቃይ እና ውዝግቡን ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ሲሉ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ካትሪን አሽተን አሞግሰዋል። ይሁንና፣ የትናንቱ ውሳኔ በህብረቱ ውስጥ ያለውን ልዩነት በግልጽ ያሳየ ነው።

ክርስቶፍ ሀስልባኽ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ