1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ሶርያን ደበደቡ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 6 2010

አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በሶርያ ጦር ሰፈሮች እና የኬሚካል ጦር መሳሪያ የምርምር ጣቢያዎች ባሏቸው ቦታዎች ላይ ዛሬ ማለዳ ድብደባ ፈጸሙ።ድብደባው ባለፈው ሳምንት የሶርያ መንግሥት በኬሚካል ጦር መሳሪያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ለቀረበበት ውንጀላ የአጸፋ ምላሽ ነው ተብሏል። ጀርመንና ኳታር ሲደግፉ ሩሲያና ቻይና ተቃውመዋል

https://p.dw.com/p/2w30B
Syrien Damaskus Militärschlag
ምስል Imago/Xinhua/A. Safarjalani

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ የምርምር ማዕከል እና ማከማቻ ናቸው ባሏቸው ሶስት ቦታዎች ላይ ዛሬ ሚያዝያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ ድብደባ ፈፅመዋል። ድብደባው ባለፈው ሳምንት በሶርያዋ ዱማ ከተማ በኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጸፅሟል ለተባለው እና በርካቶች ለሞቱበት የሶርያ መንግሥት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ነው ተብሏል በደማስቆ የነበረ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ እንዳስተዋለው ድብደባው በማለዳ ተጀምሯል። ለ45 ደቂቃዎች ፍንዳታዎች እና በደማስቆ ሰማይ የሚያጓሩ የጦር አውሮፕላኖች ድምፅ ይሰማ ነበር።  የሶርያ እና መንግሥት እና አጋሩ ሩሲያ የአየር ድብደባው ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ ነው ሲሉ አውግዘዋል።

ድብደባው ያነጣጠረባቸው ቦታዎች

  • በደማስቆ አካባቢ የሚገኝ እና የኬሚካል እና ባዮሎጂካል የጦር መሳሪያ ምርት ጋር ግንኙነት አለው የተባለ የሳይንስ የምርምር ማዕከል
  • ከሆምስ ከተማ በስተ-ምዕራብ የሚገኝ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ማከማቻ
  • ከሆምስ አቅራቢያ የሚገኝ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ቁሳቁስ ማከማቻ እና ወታደራዊ የዕዝ ማዕከል
  • Infografik Karte Luftangriffe auf Syrien ENG

የሶርያ መንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያ የመንግሥት ኃይሎች በርካታ ሚሳይሎች መተው መጣላቸውን እና በድብደባው ጉዳት የደረሰበት በደማስቆ የሚገኘው የምርምር ማዕከል ብቻ መሆኑን ዘግቧል።

ድብደባው የበሺር አል-አሳድ መንግሥት ተመሳሳይ እርምጃ እንዳይወስድ ለማስጠንቀቅ የተደረገ መሆኑን አሜሪካ አስታውቃለች።ጄኔራል ጆ ደንፎርድ የተባሉ የአሜሪካ ጦር መኮንን ተጨማሪ የአየር ድብደባ ለመፈጸም አገራቸው እቅድ እንደሌላት ተናግረዋል። የጦር መኮንኑ እንዳሉት በአየር ድብደባው የበሺር አል-አሳድ አጋር የሆነችው የሩሲያን የጦር ሰፈር ላለማጥቃት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል።

Merkel empfängt dänischen Ministerpräsidenten Rasmussen
ምስል picture-alliance/dpa/W. Kumm

የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል "አስፈላጊ እና ተገቢ" ያሉትን አሜሪካን መራሽ ድብደባ አገራቸው እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።  መራሒተ-መንግሥቷ "አጋሮቻችን የሆኑት አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ቋሚ አባልነታቸው በዚህ መንገድ ኃላፊነት መውሰዳቸውን እንደግፋለን"ሲሉ ተደምጠዋል። ባለፈው ሐሙስ አንጌላ ሜርክል ጀርመን በማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ባትሳተፍም እንደምትደግፍ ግን ገልጸው ነበር።

ከባሕረ-ሰላጤው አገራት በድብደባው ላይ መግለጫ በማውጣት ቀዳሚ የሆነችው ኳታር የሶርያ መንግሥት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ለማስቆም ድብደባዊ ተገቢ ነው ስትል ድጋፏን ገልጻለች። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልትንበርግ ድብደባው የሶርያ መንግሥት በኬሚካል የጦር መሳሪያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንዳይወስድ ያዳክመዋል ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የሶስቱ ልዕለ-ኃያላን የአየር ድብደባ በቀጣናው የረበበውን ውጥረት እንዳያባብሰው ተሰግቷል። የሶርያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሶስቱ አገራት ድብደባ ጠብ ጫሪነት ነው ሲል አውግዟል። መግለጫው እርምጃው የከፋ የዓለም አቀፍ ሕግጋት ጥሰት ነው ሲልም አክሏል።

Syrien Damaskus Militärschlag
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Ammar

ሩሲያ የእነ አሜሪካንን እርምጃ በማውገዝ ከሶርያ ጎን ተሰልፋለች። ሶርያ ከሽብርተኞች ጋር በገጠመችው ውጊያ የአገሪቱ ጦር እገዛ እያደረገ መሆኑን የገለጸችው ሩሲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንደምትጠራም አስታውቃለች።

ቻይና በዓለም አቀፍ ግንኙነት የኃይል አጠቃቀምን እንደምትቃወም ገልጻለች። ለሶርያ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል ያለችው ቻይና የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ማዕቀፍ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርባለች።

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላኽ አሊ ኻሚኒ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ የፈጸሙት ድብደባ ወንጀል መሆኑን ገልጸው የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ተናግረዋል።  ኻሚኒ የሶስቱን አገሮች ፕሬዝዳንቶች ወንጀለኛ ብለዋቸዋል።

እሸቴ በቀለ