1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ታሪክ

ሴኔጋላዊው የታሪክ ሰው፤ ሼክ አንታ ዲዮፕ

ዓርብ፣ ሰኔ 22 2010

በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ነጻነታቸውን በመቀዳጃቸው ዋዜማ በአህጉሪቱ በሚገኙ አብዛኞቹ ምሁራን ዘንድ አንድ መጽሐፍ ተወዳጅ ነበር። መጽሐፉ “የኔግሮ ሃገራት እና ባህል” በሚል ርዕስ በሴኔጋሊያዊው ሼክ አንታ ዲዮፕ የተከተበ ነው። ፕሮፌሰሩ ከዘረኝነት ጭፍን ጥላቻ የተላቀቀ አጠቃላይ የአፍሪቃ ታሪክን የመጻፍን መንገድ የከፈቱ ናቸው ይባልላቸዋል።

https://p.dw.com/p/2yLW0
Illustrationen - African Roots
ምስል Comic Republic

ሴኔጋላዊው የታሪክ ሰው፤ ሼክ አንታ ዲዮፕ

በምዕራባዊው ዓለም በጣሙኑ የሚደነቀው ጥንታዊው የግብፅ ባህል አፍሪቃዊ ነው። ከጥቁር አፍሪቃ በመጡ ህዝቦችም በርካታ ተጽዕኖ አርፎበታል።

“ይህ ሰብዓዊነት የተወለደው አፍሪቃ ውስጥ ነው። ይህ ጥልቅ ጥቁር የሆነው ሰብዓዊነት የተወለደው ከናይል ወንዝ ምንጭ ነው። ከዚያ ይህ ሰብዓዊነት ሸለቆውን ቀስ በቀስ ተቆጣጠረ። ከዩጋንዳ አካባቢ ተነስቶ እስከ ናይል ዴልታ ለመድረስ 120 ሺህ ዓመታት ወስዶበታል” ይላሉ ሼክ አንታ ዲዮፕ።

ፕሮፌሰሩ ይህንን ግኝት ይፋ ያደረጉት በጎርጎሮሳዊው 1954 ዓ.ም ነበር። በጠንካራ ሳይንሳዊ መከራከሪያዎች ላይ የተመሰረተው የእርሳቸው ግኝት በጥንታዊት ግብፅ እና በሌሎች የአፍሪቃ ቋንቋዎች መካከል ያለውን የስነ-ቋንቋ ቅርበት በማሳያነት አጣቅሷል። የዘረኝነት ጭፍን ጥላቻ ነግሶበት በነበረው የሳይንሱ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ግኝት ጉምጉምታ ማስከተሉ አልቀረም። በጊዜው የእርሳቸው ንድፈ ሀሳቦች አብዮታዊ ነበሩ ይላሉ ዳካር በሚገኘው እና በሼክ አንታ ዲዮፕ በተሰየመው ዩኒቨርስቲ የግብፅ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር አቡበከር ሙሳ። 

African Roots Cheikh Anta Diop
ምስል Comic Republic

“ይህ ሥራ ‘የኔግሮ ሃገራት እና ባህል’ በሚል ርዕስ ስር የታተመው በ1954 ዓ.ም ነው። መቆጣጠር የማይችሉት ቦምብ ሆኖ ነበር። ‘የኔግሮ ሃገራት እና ባህል’ በስልጠና ላይ ባሉ እያንዳንዱ አፍሪቃዊ እና ዳያስፖራ ምሁር መኝታ አጠገብ የማይጠፋ ሆኖ ነበር። በእርግጥ ምዕራባውያን መጽሐፉን ለማጣጣል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል” ይላሉ ፕሮፌሰር አቡበከር።       

ሆኖም የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤቱ ሼክ አንታ ሳይንሳዊ ብቃት ማጣጣሉን ቀላል አላደረገውም። የያኔው ወጣት ጎበዝ ተማሪ በኬሚስትሪ፣ ኒውክለር ፊዚክስ እና ፍልስፍና ጭምር ዲግሪ ነበረው። ሼክ አንታ ዲዮፕ ለታሪክና ስነ ቋንቋ ጥልቅ ስሜት ያላቸው እና ትልልቅ ጉዳዩችን መወጣት የሚወዱ ናቸው ይላሉ በዳካር ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ባባካር ዲዮፕ።

“እርሳቸው እንደ ብሔራዊ ቋንቋዎች፣ በአፍሪቃ የፌደራሊዝም ጥያቄዎች እና የኃይል ጉዳዮችን የመሰሉ በጣም ውስብስብ ጉዳዮችን ነበር የሚፈትሹት። ባለራዕይ ነበሩ። በርካታ መሠረታዊ ሀሳቦች አስቀምጠዋል። ዛሬ ስለ አፍሪቃ ታሪክ እንደዚሁም ስለ ሰው ልጅ ታሪክ ሲወራ የሼክ አንታን ጽሑፎች ሳይጠቅሱ ማለፍ የሚቻል አይደለም” ሲሉ ፕሮፌሰር ባባካር የሼክ አንታን አስተዋጽኦ ይዘክራሉ።

ሼክ አንታ ዲዮፕ የአፍሪቃ የኋላ ታሪክ እንደሚስባቸው ሁሉ የአህጉሪቱ መጻኢም ያሳስባቸው ነበር። በተማሪነት ዘመናቸው ከነጻነት በፊት ለነበሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን ያስገዙ ነበሩ። በ1960ዎቹ በሴኔጋል የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እና ዲሞክራሲ እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት ደግፈዋል። በመላው አፍሪቃ በመጓዝ አፍሪቃውያን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና በባህል እንዲዋሃዱ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በፖለቲካውም ይሁን በሳይንሱ ሼክ አንታ ዲዮፕ በማያወላውል አመለካከታቸው ልቀው የሚታዩ ነበሩ። “ሼክ አንታ በጣም ትሁት ነበሩ። ከእርሳቸው ጋር መጎዳኘት የጀመርኩት ተማሪ እያለሁ ነው። በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ነበሩ። ያ የመጀመሪያው ነገር ነው። ግልጽ መሆናቸው ደግሞ ሁለተኛው። ሀሳባቸውን የሚደብቁ አይደሉም። በእርግጥ ድምጻቸውን ማሰማት ነበረባቸው እርሱንም አድርገዋል። ግዙፍ ሥራዎችን የሚሸሹ አልነበሩምና በጣም ጠንካራ ሰው ነበሩ” ይላሉ ፕሮፌሰር ባባካር ዲዮፕ።  

Illustrationen - African Roots
ምስል Comic Republic

የሼክ አንታ ቁርጠኝነት ከቅኝ ገዢዎች በተወረሰው የሰውን ልጅ ታሪክ የማጭበርበር አካሄድ ላይ ወሳኝ ምት ለማሳረፍ የረዳ ነው። በጎርጎሮሳዊው 1964 እና 1999 ዓ.ም ባሉት ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት የባህልና የሳይንስ ድርጅት (UNESCO) ቀስ በቀስ የአፍሪቃን አጠቃላይ ታሪክ ማሳተም ሲጀምር የባለራዕዩ ምሁር አንታ ዲዮፕ ግኝቶች አስፈላጊውን ቦታ አግኝተዋል።      

ታማራ ዋኬርናግል/ ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.