1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሽሽት ከናይጀሪያው ቦኮሃራም

ዓርብ፣ መጋቢት 5 2006

በርካታ ናይጀሪያውያን ቦኮሃራም የሚያደርሰውን ጥቃት በመሸሽ እየተሰደዱ ነው ። አብዛኛዎቹ የሚፈናቀሉት በተለይ ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገባቸው ከሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ ግዛቶች ነው ። በዚህ ሰበብ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መሄድ በተለይ በትላልቅ ከተሞች አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል ።

https://p.dw.com/p/1BPsY
Flüchtlingscamp Menawo
ምስል DW/M. Kindzeka

ጎምቤ በተባለው የናይጀሪያ ፌደራዊ ክፍለ ግዛት የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚያስተናግደውና በአደጋ ጊዜ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ የሚያደርገው በምሕፃሩ SEMA በተባለው ድርጅት ፅህፈት ቤት አሁን ብዙም እንቅስቃሴ የለም ። የድርጅቱ ሠራተኛ ላራባ አህመድ ወደ ዚህ አካባቢ የሚመጡት ተፈናቃዮች ለአካባቢው አዲስ አይደሉም ይላሉ ። « ወደ ዚህ አካባቢ ከሚመጡት አብዛኛዎቹ እዚህ ላለፉት 3040 ዓመታት ይኖሩ የነበሩ የጎምቢ ነባር ተወላጆች ናቸው ። በነበሩባቸው አካባቢዎች ችግሩ ሲባባስ የትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሆኑት ግዛቶች ተመልሰዋል ። ከሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች 80 በመቶው የጎምቤ ተወላጆች ናቸው ። እዚህ ሲመጡም ቤታቸውን ያውቃሉ፣ ዘመዶቻቸው የት እንዳሉም ያውቃሉ ። ስለዚህ ያን ያህል የሚረዳቸው ያጡ ሰዎች አይደሉም ። »ላራባ አህመድ የሚናገሩት ናይጀሪያ የቦኮ ሃራም የተባለው ቡድን የሚፈፅመውን የሽብር ጥቃት ሸሽተው ከመኖሪያቸው ስለሚሰደዱት ናይጀሪያውያን ነው ። አብዛኛዎቹ ከሰሜን ምሥራቆቹ የናይጀሪያ ግዛቶች ከቦርኖ ከዮቤ እና ከአዳማዋ ነው የተፈናቀሉት ።

Nigeria Flüchtlinge aus Borno
የቦርኖ ስደተኞችምስል DW

በእነዚህ ክፍለ ግዛቶች መንግስት ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል ። የግዛቶቹ ነዋሬ የሆኑ በርካታ ሰዎች የአሸባሪው የቦኮሃራም ጥቃት ሰለባ ናቸው ። በዚህ የተነሳም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ በምህፃሩ OCHA እንዳስታወቀው 300 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከታወጀባቸው ከነዚህ አካባቢዎች ለቆ ወደ ሌሎች የናይጀሪያ ግዛቶች ሸሽቷል ። ላርባ አሁን ወደ ጎምቤ የሚጡ ተፈናቃዮች ቁጥር ቀንሷል እያሉ በመናገር ላይ ሳሉ ወደ 200 የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ መንደር መግባታቸው ተነግሯቸዋል ።

Nigeria Flüchtlinge aus Borno
አሚና አልሃጂምስል DW

ያማልቱ ዴባ ፣ ቦርኖ በተባለው ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ድንበር ላይ የሚገኝ መንደር ነው ። በዚህ ስፍራ የሚኖር አንድ ቤተሰብ 40 ተፈናቃዮችን አስጠግቷል ። መሄጃ ያጡትን እነዚህን ስዎች ያስጠለሉት ኦማር ኢሳህ ቤታቸው ያፈራውን ለስደተኖቹ እየሰጡ ነው ። «ያለንን ምግብ እናካፍላችኋለን ፤ ጎረቤቶቻችንም ያግዙናል ።ምግብ አብስለው ለእንግዶቻችን ያመጡላቸዋል ። ይህ የማህበረሰባችን ልምድ ነው ። እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ርስ በርስ እንረዳዳለን ። » ወደ መንደሩ ከተሰደዱት ሰዎች ገጽታ ሃዘን ይነበባል ። ሰዎቹ ንብረታቸውን ሁሉ ጥለው በመሸሻቸው ጥገኛ ሆነዋል ። ቲጃን ሃሲ የተባሉ ተፈናቃይ ህዝቡ የሚገፉው ህይወት በፍርሃት የተሞላ በመሆኑ መኖሪያውን ጥሎ ለመሄድ መገደዱን ያስረዳሉ ።«በተደጋጋሚ በተፀመባቸው ጥቃት ምክንያት ሰዎቹ በፍፁም ፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት ። ሰላም የለም ፤ አሸባሪዎች መቼ ጥቃት እንደሚያደርሱ ማንም አያውቅም ። ጠዋት ከቤትህ ስትወጣ ምን ሊያጋጥምህ እንደሚችል አታውቅም ። ማታም ወደ ቤትህ ስትመለስ የሰላም እንቅልፍ አትተኛም ። ሁሉም በፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖረው ። በዚህ የተነሳም አካባቢያችንን ለቀን ለመውጣት ወሰን »አሚና አል ሃጂ ከመፈናቀሏ ሁለት ቀናት በፊት የወለደችውን ህጻን ወንድ ልጇን ታቅፋለች ። የ23 ዓመትዋ ወጣት የርስዋና የልጇ እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አታውቅም ።አሁን ለርስዋ ትልቁ ነገር ሰላም መገኘቱ ነው ።

« የትም ልኑር የት ደንታ አይሰጠኝም ። ዋናው ነገር ልጄ በሰላም መኖር መቻሉ ነው ። የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄድ በተለይ በትላልቅ ከተሞች አሉታዊ ጫና እያሳደረ መጥቷል ። ናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ የሚገኘው የጀርመኑ የኮናርድ አደናወር ድርጅት ቢሮ ሃላፊ ሂልደጋርድ ቤርንት ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ያስረዳሉ ።« በቀጣይ ይህ የጥቃቱ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የኤኮኖሚውን ችግር ያባብሰዋል ። ሰዎቹ ሥራ ወደ ማይገኝባቸውና ህዝብ ወደሚበዛባቸው ከተሞች ሲሄዱ እዚያ ብዙም ላይፈለጉ ስለሚችሉ ጭንቀት ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ። ይህ ደግሞ ወንጀል እንዲበራከት ያደርጋል ።»

ፊሊፕ ሾልዝና አድርያን ክሪሽ

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ