1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀዉስ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ

ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2006

ባለፈዉ መጋቢት ወር የሴሌካ አማፅያን ርዕሰ ከተማ ቦንጊን ከተቆጣጠሩወዲህ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ የፀጥታ ይዞታ ከዕለት ወደዕለት እየከፋ ነዉ። ክርስቲያንና ሙስሊሞች አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ ተነስተዋል። ሰዎች ጎዳና ላይ ጥቃት ይደርስባቸዋል፣ በቆንጨራ ወይ በጥይት ተመተዉ ይገደላሉ፤ አካላቸዉ ይጎድላል።

https://p.dw.com/p/1BBBU
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

ክርስቲያኑ ኅብረተሰብ ላይ ጥቃት የከፈቱት የሴሌካ አማፅያን በፈረንሳይና በአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች የኃይል ርምጃ ከዋና ከተማ ቦንጊ እና ከሌሎችም አካባቢዎች ሲሳደዱ፤ ፀረ ቆንጨራ ለሚባለዉ ቡድን ደጋፊዎችና ክርስቲያኖቹ የብቀላዉ ተራ መጣ። ብቀላዉም እጅግ ዘግናኝ ሆነ። ይህ ግን በሁሉም አካባቢ የሚታይ አይደለም፤ ከቦንጊ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ቧሊ ከተማ አንድ የካቶሊክ ቄስ የጥላቻ ርምጃዉን በመቃወም ተነሱ።

በዚህ ስፍራ በሚገኘዉ መጠለያ የሚገኙት ሴቶች ራሳቸዉን በሂጃብ ሸፍነዋል፤ ወንዶቹ ጀለቢያ ለብሰዉ ቆብ አጥልቀዋል። አብዛኞቹ እጅግ ዘግናኝ ገጠመኝ አሳልፈዋል፤ የቅርብ ቤተሰቦቻቸዉንም አጥተዋል። ሁሉም ለነፍሳቸዉ ስጋት ገብቷቸዋል። እዚህ መጠለያ ዉስጥ 700 ሙሊስሞች ይገኛሉ። መጠለያዉን ለየት የሚያደርገዉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተፈናቀሉ ሰዎችን የምታስጠጋበት መሆኑ ነዉ። ተፈናቃዮቹ ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ ነዉ የሚተኙት፤ ዛሬ ግን እሁድ ነዉ።

Zentralafrikanische Republik Gewalt Bangui
ምስል Reuters

ሥርዓተ ፀሎት ሲካሄድ አማንያኑ ወንበር ላይ መቀመጥ ይችሉ ዘንድ ተፈናቃዮቹ ዉጭ ወጥተዉ ይቆያሉ። ሲያበቃ ደግሞ ወደቤተ ክርስቲያኑ መግባት ይችላሉ። ቄስ ክሳቬር አርኖልድ፤

«እኔ እዚህ የማድርገዉ በእርግጥ ሊደረግ የሚገባዉን እንደማሳያ ሊሆን ይችላል። ማንኛዉም በእኔ ቦታ ያለ ይህንኑ ማድረግ ይኖርበታል።»

ቄስ ክሳቪየር አርኖልድ ፋግባ በፀረ ቆንጨራ ቡድንና በአካባቢዉ ሲቪል ኗሪዎች የሚታደኑትን ሙስሊሞች ቤተ ክርስቲያን በማስገባት ታድገዋል።

«እያንዳንዱ የሚፈፀመዉን ወንጀል በሚመለከትበት ሰዓት እኔና ዲያቆኑ አንድነገር ማድረግ እንዳለብን ወሰንን። ሙስሊሞቹ ምንም እርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ስንረዳ ልናመጣቸዉ ተነሳን። እነሱን ለመፈለግም ወደከተማ ወጣን፤ ከየጎዳናዉ፣ ቤት ለቤትም እየሄድን ሰበሰብናቸዉ። አንዳንዶች ወደጫካ ሸሽተዉ ነበር፤ አንዳንዶቹን ፈልገን አገኘናቸዉ። አንዳንድ ፍፁም ለእምነታቸዉ ያደሩ ወጣት ክርስቲያኖች ረዱን። ሙስሊሞቹን ወደቤተ ክርስቲያን አስገባናቸዉ። ካለፈዉ ጥር 9 ቀን አንስቶ ከእኛ ጋ ናቸዉ።»

Zentralafrikanische Republik Muslime Flüchlinge Gewalt 12.02.2014
ምስል picture alliance/AA

ከሙስሊሞቹ ሌላ አንዳንድ ክርስቲያኖችም በፀረ ቆንጨራ ቡድን የሚፈለጉ አሉ። እነሱ የሚታደኑት ለሙስሊሞች ዉሃና ምግብ ሰጥታችኋል ወይም ቤታችሁ ዉስጥ ደብቃችኋቸዋል በሚል ነዉ። እነሱም ወደቤተ ክርስቲያን ሸሽተዋል፤ ቄሱም ጭምር በየጊዜዉ ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል። አንድ ቀን ለጥቂት ነዉ ነፍሳቸዉን ያዳኑት።

«እሁድ ቀን ነበር የፀሎት በኋላ። አንድ ምዕመን ታሞ ነበርና ለእሱ ለህሙማን የሚደረገዉን ፀሎትና ቡራኬ ላደርግለት ሄድኩ። የቤተ ክርስቲያኑን ግቢ ለቅቄ መንገዱ ላይ ስወጣ መኪናዬ በፀረ ቆንጨራ ቡድን አባላት ተከበበች። እየጮኹ ሊገድሉኝ ፈለጉ። መኪናዬን አቁሜ ወረድኩና ከእኔ ምን እንደሚፈልጉ ጠየኳቸዉ። በሃሳባችሁ ማድረግ የምትፈልጉትን ማድረግ ትችላላችሁም አልኳቸዉ። ሞትም ቢሆን እንኳ አልፈራሁም ነበር። በአጋጣሚ አንደኛዉ መሪያቸዉ በዚያ በኩል ሲያልፍ ተመልክቶ ከዚያ ስፍራ በታተናቸዉ እና እሱ ነፍሴን አዳናት።»

አሁን ነፍሳቸዉ ስለተረፈ የእርዳታ ተግባራቸዉን ቀጥለዋል። ተፈናቃዮቹ ሙስሊሞች ቄሱን ያመሰግናሉ። የአፍሪቃ ኅብረት ወታደሮች በአካባቢዉ ጎዳና ላይ ቢኖሩም የፀረ ቆንጨራ ሚሊሺያዎች እዚያዉ ቤተ ክርስቲያኑ ጊቢ ድረስ ከአንዴም ሁለቴ መምጣታቸዉንና ከመካከላቸዉ ሁለቱን መጉዳታቸዉን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም ምናልባት ከቄሱና ከዲያቆናቸዉ በቀር ማንንም ማመን ከማይችሉበት ሁኔታ ላይ የደረሱ ይመስላል። ምንም እንኳን የሁለቱን ርዳታና መስተንግዶ ቢያደንቁም ከሀገር የሚወጡበትን ማምለጫ መንገድ ብቻ ነዉ የሚያሰላስሉት።

Zentralafrikanische Republik Ausschreitungen Gewalt Christen Muslime 30.01.14
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

ይህ በእንዲህ እንዳለም ባንጊ የሚገኙት ዓለም ዓቀፍ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከቤት ቤት በማሰስ ሙስሊሞቹን በማሳደድና በወንጀል የተጠረጠሩ የፀረ ቆንጨራ ሚሊሺያ አባላትና ደጋፊዎቻቸዉን መሳሪያዎች በመዉሰድ በቁጥጥር ሥር እያዋሉ መሆኑ ተሰምቷል። በቀጣይም ለፖሊስ አሳልፈዉ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል። የሀገሪቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸዉ በሳምንቱ መጨረሻ የቡድኑን አንዳንድ መሪዎች ያነጋገሩ ሲሆን የጥላቻና ብቀላዉን ድርጊት ለማቆም እንደሚተባበሩ መግለፃቸዉን አመልክተዋል።

ቤቲና ሩህል/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ