1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቃለመጠይቅ ከፕሬዝዳንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ጋር

ሰኞ፣ ጥር 19 2006

አዲሱ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ አዲስ መንግሥት መሰረቱ ። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተሰየሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬ ዛባያኬ ባቋቋሙት በአዲሱ ካቢኔ ሰባት ሴቶች ይገኙበታል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ2 ቀናት በፊት ሲሾሙ ፕሬዝዳንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ደግሞ ባለፈው ሀሙስ ነው ቃለ መሃላ የፈፀሙት ። ፕሬዝዳንት ሳምባ ፓንዛ

https://p.dw.com/p/1Ay4h
Zentralafrikanische Republik Interimspräsidentin Catherine Samba-Panza 23.01.2014
ምስል Reuters

ከጀርመን ጋር ተባብረው መስራታቸው ለሃገራቸው ምን ዓይነት ጠቀሜታ እንደሚኖረው በትክክል ያውቃሉ። ፕሬዚዴንቷን ከየዶይቸ ቬዎቹ ጋዜጠኞች ዲርክ ኮብ እና ቲአሱ ኮሲፊ ቃለ መጠይቅ አድርገውላቸዋል።
የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ የዛሬ ሳምንት ነበር በጊዜያዊው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ አግኝተው የተመረጡት። ካለፈው ዓርብ ጀምሮም ፕሬዚዳንቷ ስራቸውን ጀምረዋል። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ አዲስ ምርጫ ለማካሄድ የአንድ ዓመት ጊዜ ነው ያላቸው።
« ይህ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠን ጊዜ ነው። ይህንን ገደብ የመጠበቅ ግዴታ አለብን። ራሱ ከአንድ ዓመት በፊት «ሊብረቪለ» ላይ ያወጣነውን የጊዜ ገደብ ለመጠበቅ ስንል። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው መስሪያ ቤቶችን መልሶ ስራ እንዲጀምሩ ማድረጉ ላይ ነው፤ ምርጫ ሊዘጋጅ እንዲችል። ለነገሩ ይህ በጣም አዳጋች ነው። አስተዳደሩ በአጠቃላይ ፈፅሞ ተግባሩን ለማከናወን ተፅኖታል። ስለዚህ እንዳልኩት በመጀመሪያ የብሔራዊ እና የአካባቢውን መስሪያ ቤቶች ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ ይኖርብናል። የምርጫው ሂደት እንዲጀምር።»
የርስ በርስ ግጭት፥ ሁከትና አመፅ በነገሰባት በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ 2,2 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ አስቸኳይ ርዳታ እንደሚያስፈልገው ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገለፀው። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የመንግሥት ለውጥ እንደተደረገ የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ወዲያሁኑ ነበር ወታደሮችን ወደዚችው ሀገር ያዘመተችው። አሁን ደግሞ ግዚያዊ ፕሬዚዳንቷ ስልጣን እንዲጨብጡ ፈረንሳይ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ይባላል። ሳምባ ፓንዛ ግን ይህን ያጣጥላሉ።

ድምፅ 2
« እንደዛ ብዬ አላስብም። ይልቁንስ መላው ህዝብ፤ ወንድ ፣ሴት ወጣት በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ነው እኔ ስልጣን እንድጨብጥ የተባበረኝ። እኔ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ እንድሰለፍ በተደጋጋሚ ሞክረረዋል። ነገር ግን እኔ ሁሌ አልፈለኩም ነበር። ከዛ ፕሬዚዳንት ጆቶዲያ ስልጣን ሲለቁ ዳግም ይህ ግፊት መጣ። ኋላም ከፈረንሳይም መጣ እንበለው ከሀገሬ ህዝብ፤ እኔ ለኃላፊነቱ ብቁ መሆኔን አረጋገጡ እና እንድወዳደር አበረታቱኝ።
ፕሬዚዳንቷ ስራ ከጀመሩም በኋላ በሀገሪቷ መረጋጋት አልሰፈነም። ፕሬዚዳንቷ ስራ በጀመሩ የመጀመሪያው ዕለት የሙስሊሞች የቀድሞ ሚኒስትር ጭካኔ በተሞላበት ጥቃት ተገድለዋል። ከሳቸውም ሌላ ክርስትያኞች እና ሙስሊሞች ተጋጭተው ሌሎች 9 ሰዎች ተገድለዋል። እንዲሁ ትናንት ደግሞ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ቀይ መስቀል አስታውቋል። በነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ለወራት ሰላም ለማስፈን ቢጣርም እስካሁን ውጤት ያላስገኘው ለምን እንደሆነ ለአዲሷ ፕሬዚደንት የቀረበላቸው ሌላኛው ጥያቄ ነው።
« በአሁኑ ሰዓት ለመቆጣጠር ከአቅማችን በላይ የሆኑ ኃይላት ናቸው ያሉት። በመላው የሀገሪቱ ክፍል እና ባንጊ ውስጥ በሙስሊም እና ክርስትያን ማህበረሰብ ዘንድ እርቅ ለማውረድ የሚጥሩ ተቋማት አሉ። ይሁንና እስካሁን እነዚህን ኃይላት ለማሸነፍ አልቻልንም። እኔ ስልጣን ከመጨበጤ በፊት ነው ሁሉ ነገር ከቁጥጥር ውጪ የሆነው። እንግዲህ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ሰላም የሚያስከብሩ የመከላከያ እና የጥበቃ ኃይላት እናዘጋጃለን። »
የአፍሪቃ ሕብረትና ፈረንሳይ ከአራት ሺሕ የሚበልጥጡ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ቢያዘምቱም ዘማቹ ጦር እስካሁን በተጨባጭ ያመጣዉ ዉጤት የለም። ስለሆነም የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ባለፈው ሳምንት ከአምስት መቶ እስከ አንድ ሺሕ የሚደርሱ ወታደሮች ለማዝመት ወስነዋል። ጀርመን ወታደሯን ባትልክም፤ እዚያ የሚገኙትን የፈረንሳይ እና የአፍሪቃ ህብረት ኃይሎች የመጓጓዣ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ሳምባ ፓንዛ ከጀርመን ከዚህም በላይ ይጠብቃሉ።
« በአውሮፓ ህብረት ትልቅ ሚና ካላት ጀርመን የምጠብቀው ከፍተኛ ትብብር ነው። በሰብዓዊ ዘርፍ ፣ የደህንነት እና የገንዘብ ድጋፍ ሊሆን ይችላል። ሌላ አዲስ ውጥረት እንዳይነሳ የፋይናንስ ርዳታ ያስፈልገናል። ወርሃዊ ደሞዝ እና ጡረታ መክፈል እንድንችል ማለት ነው። ምክንያቱም ስልጣኔን የማህበራዊ ውጥረት ኖሮ ከጀመርኩ በቅርቡ ሌላ ችግር ይነሳል። ጀርመን ለምሳሌ የራዲዮ ስርጭት በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች እንዲስፋፋ ልትተባበር ትችላለች። ባንጊ ውስጥ አንድ ጣቢያ ብትከፍት ጥሩ ነበር።»

Zentralafrikanische Republik Catherine Samba-Panza & Laurent Fabius 23.01.2014
ምስል Reuters
Catherine Samba-Panza Zentralafrikanische Republik 20.01.2014 Bangui
ምስል Eric Feferberg/AFP/Getty Images

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ