1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቄስ ጉዲና በምን ይታወሳሉ?

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2005

የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮኣሒም ጋውክ ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓም የቄስ ጉዲና ቱምሳ መቃብርን ጎብኝተው የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸው ተዘግቧል። የመካነ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪ የነበሩት ቄስ ጉዲና በምን ይታወሳሉ?

https://p.dw.com/p/180By
ምስል DW/L. Schadomsky
Gauck in Äthiopien
ምስል DW/H. Schott

በደርግ ዘመነ-መንግስት የመካነ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪ ነበሩ ቄስ ጉዲና ቱምሳ። በወቅቱ ለሶስት ጊዜያት በተደጋጋሚ ለእስር እንደተዳረጉ ይነገራል። የቄስ ጉዲና የመጨረሻ ልጅ የሆኑት ወሮ ሌንሳ ጉዲናም አባታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ሲታሰሩ ለመጠየቅ በሄዱበት እስር ቤት ተይዘው ታስረው እንደነበር ገልፀዋል። ከውጭ በነበረው ጫና ለሁለተኛው ጊዜ ከታሰሩበት እስር ቤት ተለቀው ነበር። ከሶስተኛው እስር በኋላ ግን ዱካቸው ሳይገኝ ለ13 ዓመታት ቆይቷል። ያኔ የ16 ዓመት ታዳጊ የነበሩት ወሮ ሌንሳ ጉዲና አባታቸው ቄስ ጉዲና የሚታወሱበትን ጉዳይ እንዲህ ይጠቅሳሉ።

ምንም እንኳን ደርግ በወቅቱ የቄስ ጉዲና ቱምሳን ደብዛ መጥፋት ተከትሎ የሰጠው አንዳች መግለጫ ባይኖርም፤ የዚያን ዘመኑን የፖለቲካ ሂደት ይከታተሉ የነበሩ ግለሰቦች ግን የሚሉት ነገር አለ። የቄስ ጉዲና ቱምሳ ወንድም አቶ ባሮ ቱምሳ በወቅቱ የብሔር መገንጠል እንቅስቃሴን በህቡዕ ያራምዱ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር ቄስ ጉዲና ለወንድማቸው በማቴሪያልም በሀሳብም ድጋፍ ሳያደርጉ አይቀሩም የሚሉ አሉ። ይህን በተመለከተ የቄስ ጉዲና ቱምሳ የመጨረሻ ልጅ ወ/ሮ ሌንሳ ጉዲና መልስ አላቸው።

ወሮ ሌንሳ ጉዲና አያይዘውም ስለ ቄስ ጉዲና ማንነት ለመናገር አባታቸው ትተው ያለፏቸውን ጽሑፎች መመርመር ያስፈልጋል ብለዋል። የአባታቸውን ጽሑፎች ለህትመት እያበቁ እንደሆነ በመጥቀስ በፅሁፎቹ ውስጥ ቄስ ጉዲና ስለተጨቆኑ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው ይጠይቁ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ቄስ ጉዲና በደርግ ዘመነ-መንግስት የመካነ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪ የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ በወቅቱ በካቶሊክ፣ በኦርቶዶክስና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ጥምረት ተመስርቶ የነበረው ም/ቤት (ካውስንል)የመጀመሪያው ሊቀመንበርም ሆነው አገልግለዋል። ቄስ ጉዲና ቱምሳ በደርግ ታፍነው ተወስደው እንደተገደሉና አፅማቸው ከ13 ዓመታት በኋላ የተገደሉበትን ቦታ ያውቅ በነበረ ጠባቂ ግለሰብ ጠቋሚነት እንደተገኘ ልጃቸው ወ/ሮሌንሳ ጉዲና ገልፀዋል። የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ በጀመሩት ጉብኝት
ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓም የቄስ ጉዲና አጽም ወዳረፈበት መካነ-መቃብር በመሄድ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውና ንግግር ማድረጋቸው ይታወቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ