1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

በሐምሌ ተግባራዊ የሚሆነው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች የትኞቹ ናቸው?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 2014

በሐምሌ ተግባራዊ የሚደረገው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች እየተለዩ ነው። ነባሩ አሰራር መንግሥትን በቢሊዮን ብሮች ከማሳጣቱ ባሻገር ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገሪቱ እንዲወጣ ማድረጉ ይገልጻል። ባለፈው ወር መንግሥት 13 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ወጪ ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታ ሐሰን መሐመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4DExD
Äthiopien | Warteschlagne vor Tankstelle in Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ወር ብቻ 13 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ወጪ ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታው አቶ ሐሰን መሐመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይኸ በየዓመቱ አገሪቱን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር አሳጣ የተባለ ድጎማ ብክነት እና የነዳጅ ኮንትሮባንድ አስከትሏል። አገሪቱ ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆን አሰራር ቀስ በቀስ የነዳጅ ድጎማን ለማስቀረት በዝግጅት ላይ ትገኛለች። መሳይ ተክሉ በድሬዳዋ በጉዳዩ ላይ ባለሥልጣናቱ የሰጡትን ማብራሪያ ተከታትሎ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ለረጅም አመታት ተገቢ ባልሆነ መልኩ ለነዳጅ ሲደረግ ነበር ባለው የድጎማ አሰራር ላይ ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ ለውጥ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። "የታለመለት የነዳጅ ድጎማ" በሚል ተግባራዊ በሚሆነው አዲሱ የድጎማ አሰራር ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች  በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ይሆናሉ። የግብይት ስርዓቱ ላይ ቁጥጥር ለማድረግም የክፍያ ስርዓቱ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ እንደሚፈፀም ተገልፆል።
ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ በስራ ላይ ይውላል የተባለውን የድጎማ አሰራር በተመለከተ ለድሬደዋ አመራሮች ማብራሪያ የሰጡት የቀድሞ የነዳጅ ቁጥጥር  ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ በድጎማው ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች እና አተገባበሩ ዝርዝር ተናግረዋል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ቀደም ሲል መንግስት ለነዳጅ ሲያደርግ የነበረው ከፍተኛ ድጎማ ብክነት እና ኮንትሮባንድን ማምጣቱን ተናግረዋል።
አሁን ባለው አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ ይህን አስራር መከተል ችግሩን ያባብሳል የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም ትክክል አለመሆናቸውን አቶ ሀሰን ጠቁመዋል።
"የታለመለት የነዳጅ ድጎማ" አሰራር የድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች በኢ ብር የክፍያ ስርዓት እንደሚገለገሉ የተናገሩት ሚንስትር ዲኤታው ይህም በጥቂት ተሽከርካሪዎች ተሞክሮ ስኬታማ መሆኑን አስረድተዋል።
 ከቀናት በኃላ በስራ ላይ ይውላል የተባለውን የነዳጅ ድጎማ አሰራር ለመተግበር በሀገሪቱ በድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑ የተሽከርካሪዎች መረጃ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል ። በድሬደዋም ተመሳሳይ ስራ እየተሰራ ነሆኑን ተመልክተናል።
መሳይ ተክሉ 
እሸቴ በቀለ