1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመተከል የደረሰው ጥቃት 

ረቡዕ፣ መስከረም 6 2013

በቤኒሻንጉለ ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለንና ወንበራ በተባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች በሰላማዊ ህዝቦች ላይ ጉዳት እያደረሱ አንደሆነ ነዋሪዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች አመለከቱ። የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ኃላፊዎች በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ይናገራሉ።  

https://p.dw.com/p/3iYs3
Äthiopien Gilgel Beles Stadt
ምስል DW/N. Dessalegn

«ችግሩ የተከሰተበት ክልል ባለሥልጣናት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል»

በቤኒሻንጉለ ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለንና ወንበራ ወረዳዎች በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች ሰሞኑን በወረዳዉ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ህብረተሰቡን ለሞት፣ ለስደትና ለአካል ጉዳት እየዳረጉት እንደሆነ ነዋሪዎቹና ቤተሰቦቻቸው የተጎዱባቸው ግለሰቦች አመልክተዋል። ለሥራ በተንቀሳቀሱበት ባለፈው እሁድ 6 ዘመዶቻቸው እንደተገደባቸው በአማራ ክልል አዊብሔረሰብ አስተዳደር የጓዋንጓ አካባቢ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል። የግልገል በለስ ነዋሪ የሆኑና ለደህንነታቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በበኩላቸው «በመተከል ዞን ቡለንና ወንበራ አካባቢዎች የሚፈፀመው ጥቃት እጅግ ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ነው» ብለዋል፡፡ 
ግጭቱ እንዲባባስ ከመንግሥት መዋቅሩ መረጃ የሚያደርስ አካል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ለዚህም ምክንያታቸው ታጣቂው ኃይል ባለበት አካባቢ የፀጥታ ኃይሉ ሲንቀሳቀስ ቀድመው ከቦታው እንደሚሰወሩ አብራርተዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪና የአማራ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው «የአማራ ክልላዊ መንግስት ከክልሉ ውጪ ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን መብት እያስጠበቀ አይደለም» ሲሉ ይከስሳሉ። የአማራ ክልል የሰላምና ህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገደቤ ኃይሉ እንደገለፁት «ፀረ ሰላም» ያሏቸውን አካላት ለመደምሰስና በቁጥጥር ስር ለማዋል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።  ችግሩ የተፈጠረበትን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑን ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ለማነጋገር ብሞክርም «መረጃ በስልክ አንሰጥም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከባሕር ዳር ዓለምነው መኮንን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ