1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመንዲ በድሮን በተፈጸመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን ዕማኝ ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 3 2015

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በምትገኘው መንዲ በሰው አልባ አውሮፕላን በተፈጸመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኝ ተናገሩ። ጥቃቱ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ተሽከርካሪ ላይ ያነጣጠረ ነበር ተብሏል። በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የነበረችው መንዲ ተመልሳ ከመንግስት ኃይሎች እጅ መግባቷን የዐይን ዕማኙ ገልጸዋል

https://p.dw.com/p/4JQhq
መንዲ
በምዕራብ ወለጋ ዞን በምትገኘው መንዲ ከተማ ሁለት ጊዜ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት መፈጸሙን የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል DW/N. Desalegn

በመንዲ በድሮን በተፈጸመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን ዕማኝ ተናገሩ

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል መንግስት ሸነ ያለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ስር ነበረች በሚባለው መንዲ ከተማ በታጣቂዎቹ ተሽከርካሪዎች ላይ አነጣጥሮ በከተማዋ ዳለቲ ማዞሪያ በሚባል ስፍራ በተወሰደ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት በአከባቢው የነበሩ ሰላማዊ ዜጎችም ጭምር ሰላባ መሆናቸውን ነው ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት፡፡

በእለቱ እኩለ ቀን ከ7-8 በሚገመት ሰዓት በሁለት ተሸከርካሪዎች ወደ ከተማዋ በገቡ ታጣቂዎች ላይ ኢላማውን ያደረገው ጥቃቱ በአከባቢው የእለት ተእለት ስራቸው ላይ የነበሩትን ነዋሪዎችም በሰፊው ሰለባ ማድረጉን ነው ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ነዋሪ የተናገሩት፡፡ 

“ጥቃቱ የደረሰው እሮብ እኩለ ቀን ነበር፡፡ እለቱ የገበያ ቀን ስለነበር በርካታ ሰው በከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱም ነበር፡፡ ከተማዋ ለአንድ ሳምንት ያህል ገበያም አጥታ ስለነበር ብዙ ሰው ገበያ ወጥተው ነበር፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ ማዞሪያ ወይም ዳለቲ በመባል ይታወቃል፡፡ በአከባቢው ሰው በብዛት ይንቀሳቀሰር ነበር፡፡ በዚሁ ሳለ ነበር በሁለት ተሽከርካሪዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በስፍራው የደረሱት፡፡ ልክ እነሱ ሲቆሙ በደቂቃዎች መሃል ድሮን ቦንብ ጣለች” ብለዋል የአይን እማኙ አየሁ ያሉትን የተናገሩት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው በጥቃቱ በተሸከርካሪው ወደ ከተማዋ የገቡና በውስጡ የነበሩት ታጣቂዎች በዚያው ቢሞቱም በስፋት የተፈናጠረው ቦንብ ግን በብዛት በአከባቢው የነበሩትን ሰላማዊ ዜጎችንም ሰለባ አድርገዋል፡፡

ኦነግ
ኦነግ ጉዳዩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ 600ሜትር ራዲየስ ውስጥ በመንዲ ከተማ ዳለቲ በሚባል ስፍራ በተወሰደው የሰው አልባ ድሮን ጥቃት በአከባቢው ንጹሃን ተጠቅተው ንብረትም ወድሟል ብሏል፡

“የአየር ጥቃቱ በዋናነት ያነጣጠረው በዚያው ታጣቂዎች በያዙት ተሽከርካሪው ላይ ነው፡፡ ቁጥራቸውን የማላውቀው በመኪናው ውስጥ የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ጭራሽ አስከሬናቸውም አልተገኘም፤ ከተሽከርካሪው ጋር ነው የተቃጠሉት፡፡ ግን ደግሞ በአከባቢው ምግብ እና ሻይ ቤት ስለነበረ አገልግሎቱን የሚሰጡ እና ሲጠቀሙ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች በተፈናጠረባቸው ቦንብ ቢያንስ ከ7-10 የሚሆኑት በዚያው ነው የሞቱት፡፡ ጭንቅላታቸው፣ እጃቸው የተቆረጠ ነበሩ፡፡ 13 ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል ደርሰው መሞታቸውን ሰምተናል፡፡ ሌላው በከተማዋ መግቢያ ቄራ በሚባል ስፍራ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና የመንግስርት ታጣቂዎች ሲፋለሙ ሌላ የድሮን ጥቃት ተወስዶ ነበር፡፡ እኛ በዚያ ቦታው ላይ ደርሰን ማረጋገጥ ባንችልም እዚያ ሊጎዳ የሚችለው የታጠቀ ቡድን ብቻ ነው” ሲሉም አክለዋል አስተያየት ሰጪው፡፡

ባለፈው ሳምንት ውስጥ በታጠቂዎች ቁጥጥር ስር የሰነበተችው መንዲ ትናት ተመልሳ በመንግስት ወታደሮች ቁጥጥር ስር መግባቷንም እኚው ነዋሪ ገልጸውናል፡፡ “መንዲን ለአንድ ሳምንት ያህል የተቆጣጠራት የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሰራዊት ነበር፡፡ ከእሮቡ የድሮን ጥቃት በኋላ ደግሞ ትናንት የመንግስት ሰራዊት ሰብሮ ገብቶ ከተማዋን መልሶ ተቆጣጥሮአታል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ጦርነት ሲካሄድም ስለነበር ነዋሪዎች በብዛት ከተማዋን ለቀው ወደ ገጠር ቀበሌያት ሸሽተዋል፡፡”

ባለፈው ሳምንት ከመንዲ በተጨማሪ ላሎ አሰቢ፣ ለታ ሲቡ እና ነጆ በአከባቢ ያሉ ሶስት ወረዳዎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ገብተው እንደነበር የተነገረ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ ግን መንግስት አከባቢዎቹን መልሶ እየተቆጣጠራቸው መሆኑን ነው ነዋሪዎች በአስተያየታቸው ያመለከቱት፡፡ 

መንዲን ጨምሮ በነዚህ አከባቢዎች የባንክ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ጨምሮ ምንም አይነት መሰረታዊ አገልግሎቶች አለመኖራቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የድሮን ጥቃቱ ባለፈው ሳምንትም ሰኞ በመንዲ በታጣቂዎች ላይ በከተማዋ በሚገኘው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት አነጣጥሮ መወሰዱን ተነግሯል፡፡ ነጆ ከተማም ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ የአየር ጥቃቱን ማስተናገዷ ነው የተገለጸው፡፡ 

ስለነዚህ ጥቀቶች በመንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡ ዶይቼ ቬለ ከአከባቢው እና ከክልሉ ፀጥታ እና አስተዳደር እንዲሁም ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች መረጃውን ለማጣራት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡

በጥቅምት ወር በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ እና ጮቢ ወረዳዎች ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት በመንግስት ተወስዶ ሰላማዊ ዜጎችንም ሰላባ ማድረጉን ነዋሪዎች እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) መክሰሳቸውን ተከትሎ ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን ሰጥተው የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ፤ በኦሮሚያ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ኦፕሬሽን እየተወሰደ መሆኑን አረጋግጠው ጥቃቱ በድሮን የታገዘ ነው መባሉን ግን አስተባብለዋል፡፡ የአሁኑ የመንዲውን የሰው አልባ ድሮን ጥቃት ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ ግን የፖለቲካ ሰዎች እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጥቃቱ ሰላማዊ ዜጎችን ሰላባ አድርጓል በማለት አውግዘውታል፡፡

አቶ ጃዋር መሃመድ
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለስልጣን አቶ ጃዋር መሃመድ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ግጭት ትኩረት አልሰጠም ብለዋል፡ምስል Mulugeta Ayene/AP Photo/picture alliance

ኦነግ ጉዳዩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ 600ሜትር ራዲየስ ውስጥ በመንዲ ከተማ ዳለቲ በሚባል ስፍራ በተወሰደው የሰው አልባ ድሮን ጥቃት በአከባቢው ንጹሃን ተጠቅተው ንብረትም ወድሟል ብሏል፡፡ እርምጃውን ጭካኔ የተሞላበት ነው ያለው ኦነግ ከዚህ ቀደምም በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች በተመሳሳይ ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ አድርጓል ያለው የአየር ጥቃ አውግዟል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ጦር ዓለማቀፍ ቃልአቀባይ ኦዳ ተርቢ በፊናቸው በመንዲው የአየር ጥቃት ወደ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን በቲዊተር ጽፈዋል፡፡ አባሎቻቸው ስለመጎዳት አለመጎዳታቸው ግን ያሉት ነገር የለም፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ በተደጋጋሚ ተወስዷል በተባለው የድሮን ጥቃት በርካቶች ሰላባ መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡ በዚሁ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ቢላ ከተማ ባለፈው ሳምንት የተመሳሳይ ጥቃት ሰለባ መሆኗ ነው የሚነገረው፡፡

ዶይቼ ቬለ ተወስዷል ስለተባለው የድሮን ጥቃት እና የጉዳቱን መጠን ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት ባወጣው መግለጫው ግን በመንዲው የእረቡዕ ጥቃት ብቻ 100 ሰዎች ሰላባ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለስልጣን አቶ ጃዋር መሃመድ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ግጭት ትኩረት አልሰጠም ብለዋል፡፡ ፖለቲከኛው በማህበራዊ መገናኛ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለይቶ ለአንድ አካል ብቻ ማልቀሱ ለኢትዮጵያ መረጋጋት መፍትሄ አይንም ነው ያሉት፡፡
ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ከሰሞኑ በጠነከረው አለመረጋጋት ባለፈው እሁድም የምስራቅ ወለጋ ዋና ከተማ ነቀምቴ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ውስጥ ግብታ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ 

ስዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ