1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማሊ ሆቴል ላይ የተፈጸመው ጥቃትና እገታ

Eshete Bekeleዓርብ፣ ኅዳር 10 2008

በማሊ በተጠርጣሪ እስላማዊ ታጣቂዎች የተፈጸመው እገታና ጥቃት ተጠናቋል። የመንግስት ባለስልጣናት «በጥቃት ፈጻሚዎቹ የተያዙ ታጋቾች የሉም።» ሲሉ አስታውቀዋል። የአልቃኢዳ ታጣቂ ቡድን የማግረብ አካባቢ ክንፍና አጋሩ አል-ሙራቢቱም ታጣቂ «ጥቃቱን ፈጽመናል» ማለታቸው ተዘግቧል። እስካሁን 18 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/1H9fH
Mali Geiselnahme Radisson Blu Hotel in Bamako
ምስል picture-alliance/dpa

ሆቴሉን የሚያስተዳድረው ሬዚዶር ሆቴል ግሩፕ ጥቃት ፈጻሚዎቹ 140 ደንበኞች እና 30 ሰራተኞች አግተው እንደነበር አስታውቋል። እንደ አገሪቱ ፖሊስ ከሆነ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የእስልምና አክራሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።ከአጋቾቹ መካከል የተወሰኑት የዲፕሎማቲክ ሰሌዳ በለጠፉ ተሽከርካሪዎች ቀሪዎቹ ደግሞ በእግራቸው ወደ ሆቴሉ ማምራታቸውን የደህንነት ምንጮችና የማሊ ብሄራዊ ቴሌቭዥን አስታውቀዋል። ሶስቱ የጥበቃ ሰራተኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ከቆሰሉ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል። ወደ ሆቴሉ ያመሩት ጥቃት ፈጻሚዎች የመኝታ ክፍሎች በሮችን መክፈታቸውንና የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ተዘግቧል። ከታጋቾቹ መካከል ስድስት የቱርክ አየር መንገድ ሰራተኞች፤የፈረንሳይና ቻይና ዜግነት ያላቸው ሰዎች ይገኙበታል። የዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች የምዕራቡ አገራት ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። ማሊ በአክራሪ ታጣቂዎች ጥቃት ሲደርስባት የመጀመሪያዋ አይደለም። በማሊ የሚታየው የአሸባሪዎች ስጋት ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር አይገናኝም ሲሉ በአፍሪቃ ጸጥታ ጥናት ተቋም የምዕራብ አፍሪቃ አጥኚ ዊሊያም አሳንቮ ተናግረዋል። ዊሊያም አሳንቮ የማሊ ጸጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ስጋቶችን የመከላከል ብቃታቸው ደካማ እንደሆነም ይናገራሉ።

Mali Polizei in Bamako
ምስል H. Kouyate/AFP/Getty Images

«በሳህል አካባቢ የሚገኙ አገራት እጅግ ደካማ ናቸው። እንዲህ አይነት የጸጥታ ስጋቶችን የመመከት አቅማቸውም ውስን ነው።»

ሰሜናዊ ማሊ ከጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. መፈንቅለ-መንግስት በኋላ በእስላማዊ ታጣቂዎችና የአልቃኢዳ ታጣቂ ቡድን ተደጋጋሚ የጸጥታ ቀውስ ሲገጥመው ቆይቷል። የፈረንሳይና የአፍሪቃ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ታጣቂዎቹን ከአካባቢው በማስለቀቅ ማዕከላዊ መንግስቱን ወደ ስልጣን መመለስ ችለው ነበር።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ