1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማንዴላ ሞት የአፍሪቃውያን መሪዎች አስተያየት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 28 2006

የተከበሩት ተወዳጁ የደቡብ አፍሪቃ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ እና ትልቅ አመለካከት ያተረፉት አንዱ የ 20ኛው ምዕተ ዓመት ዕውቅ ፖለቲከኛ ኔልሰን ማንዴላ ሐሙስ፣ ኅዳር 26 ቀን፥ 2006 ዓም በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ዜና በደቡብ አፍሪቃ፣ በመላ አፍሪቃ እና በዓለም ትልቅ ሀዘን አስከትሎዋል።

https://p.dw.com/p/1AUYq
Trauer um Nelson Mandela
ምስል Reuters

ከ 27 ዓመታት እስራት በኋላ በደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ሆነው እአአ በ1994 ዓም የተመረጡት እና ሀገሪቱን እስከ 1999 ዓም የመሩት ኔልሰን ማንዴላ ለረጅም ጊዜ ለሳምባ ሕመም በሀኪም ቤት እና ካለፈው መሰከረም ወርም በኋላ ጆሀንስበርግ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ህክምና ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ ነው ያረፉት።

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ተወዳጁ መሪ እና የዴሞክራሲያዊቷ ሀገር መሥራች አባት የሆኑትን የኔልሰን ማንዴላን ዜና ዕረፍት ያስከተለወን መሪር ሀዘን ለደቡብ አፍሪቃውያን እንዲህ ሲሉ ነበር በሀገሪቱ ቴሌቪዥን በይፋ ያስታወቁት።

Desmond Tutu ARCHIVBILD 2011
አቡነ ዴዝመንድ ቱቱምስል picture-alliance/dpa

« ሀገራችን ትልቁን ልጇን ፣ ሕዝባችን ደግሞ አባቱን አጥቶዋል። »

በመላይቱ ሀገር ከትናንት ጀምሮ 10 ቀን የሚቆይ ይፋ ሀዘን መታወጁን እና ሥርዓተ ቀብራቸውም እአአ የፊታችን እሁድ ታህሳስ 15፣ 2013 ዓም እንደሚፈፀም በማስታወቅ ሕዝቡ የርሳቸው ራዕይ ሙሉ በሙሉ እውን እንዲሆን የርሳቸውን ፈለግ ከመከተል እንዳይቆጠብ አሳስበዋል።

« ማዲባ ያከናወኑትን ምግባር እና ጥረታቸውን በቁርጠኝነት እንድንከተል እና በእውነት የተባበረች ደቡብ አፍሪቃ የመመሥረት፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች አፍሪቃ እና የተሻለ ዓለም የመፍጠር ራዕያቸው እውን እስኪሆን ድረስ ካላንዳች ዕረፍት እንድንሰራ እጠይቃለሁ። ማዲባ ሁሌም እንወድዎታለን። ነፍስ ይማር። እግዚአብሔር አፍሪቃን ይባርክ። ንኮሲ ሲኬሌሊ አፍሪቃ። »

የኔልሰን ማንዴላ የረጅም ጊዜ የትግል ጓድ አቡነ ዴዝመንድ ቱቱም ደቡብ አፍሪቃ አሳሳቢ በነበረው ታሪክ ወቅት ማንዴላን የመሰለ ትልቅ እና ትሑት መሪ በማግኘቷ እግዚአብሔር ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። ማንዴላ በቀድሞ ጨቋኞቻቸው አንፃር ቂም በቀል በመያዝ ፈንታ የተለያዩ የቆዳ ቀለም ባለው ሕዝብ መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ያደረጉበት ርምጃቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አክብሮት አስገኝቶላቸውየኖቤል ሰላም ተሸላሚም ሆነዋል።

Stimmen und Reaktionen zum Tod Nelson Mandelas
የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማምስል Reuters

የማንዴላን ዜና ዕረፍት ተከትሎ የአፍሪቃ ህብረት እና የዓለም መሪዎች ለኒሁ ታላቅ መሪ ያላቸውን ክብር እና አድናቆት በመግለጸ ላይ ይገኛሉ።

የአፍሪቃ ህብረት በኔልሰን ማንዴላ ሞት የተሰማውን ሀዘን ለደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ እና ለደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ገልጾዋል። የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ምክትል ኤራስቱስ ምዌንቻ፣ አፍሪቃውያን እኒሁ ታላቅ መሪ በሕይወት ዘመናቸው የጀመሩትን እና ያልጨረሱትን ትግል መቀጠል እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

« በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድን ማብቃት ተሳክቶላቸዋል። በጣም ተከፋፍላ እና ጭቆና በበዛባት ሀገር ውስጥ ፍትሕ እና መተሳሰብ እንዲሰፍን አድርገዋል። ተግዳሮቶችን እንዴት መወጣት እና አጋጣሚዎችንም እንዴት መፍጠር እንደሚቻልም አሳይተውናል፣ አበረታተውናል። ከዜና ዕረፍታቸው የምንወሰደው መልዕክት እሴቶቻቸውን መከተል፣ እንዲሁም፣ በአህጉሩ ብልፅግናን እና ክብርን ለማስገኘት በሕይወት ዘመናቸው የጀመሩትን እና ገና ሊጨርሱ ያልቻሉትን ትግላቸውን መቀጠል የተሰኘውን ነው። »

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ጠቅላይ ሚንስትሩ በኔልሰን ማንዴላ ሞት ጥልቅ እና መሪር ሀዘን እንደተሰማቸው ለደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ እና ለደቡብ አፍሪቃውያን በሙሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ለአፍሪቃ እና ለፈረንሳይ መሪዎች ጉባዔ በፓሪስ የተገኙት የጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።

የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታም ፣ ማንዴላ በእኩልነት እና በፍትሕ የሚያምኑ ልዩ መሪ ነበሩ ሲሉ አክብሮታቸውን እና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።#

Uhuru Kenyatta Ansprache Rede
የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታምስል John Muchucha/AFP/Getty Images

« ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ የሚደነቅ ችሎታ እና ጠንካራ እሴቶች የነበሩዋቸው ልዩ፣ ቀያሪ መሪ ነበሩ። በእኩልነት፣ በፍትሕ፣ በአብሮነት እና በመንግሥት ተግባር ውስጥ ማሳተፍ በተሰኙት የተከበሩ መመሪያዎች ያምኑ ነበር። ነፃ፣ የተባበረች እና የበለፀገች ደቡብ አፍሪቃ በመመሥረቱ የሕዝባቸው ቸሎታ ላይ ፅናት እና እምነት ነበራቸው። »

የኬፕ ቬርዴ ፕሬዚደንት ኾርጌ ካርሎስ ፎንሴካም የነፃነት አርበኛው ኔልሰን ማንዴላ የዓብዮታዊነትን መመዘኛ ሰቅለውታል ሲሉ ነበር አድናቆታቸውን የገለጹት።

« በኔልሰን ማንዴላ ሞት በዓለም ካሉት የ20ኛው ምዕተ ዓመት ታዋቂ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ከዓለም ተነጠሉ። ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ ትግል አርበኛ እና የእኩልነት ታጋይ ነበሩ። በተለይ ግን የዓብዮታዊነትን መመዘኛ ሰቅለውታል። ከዚህ በተጨማሪም ስብዕና የተሞላቸው እና የነፃነት ታጋይም ነበሩ። በዚህም የተነሳ ነፃነትን ለምንወድ፣ ሰብዓዊነትን ለምናከብር እና ለፍትሕ፣ ለሰላም እና ለነፃነት ለምንታገል ሁሉ ዋነኛ እና ወሳኝ ውርስ ትተውልን ነው ያለፉት። ኔልሰን ማንዴላ ለአፍሪቃ እና ለመላው ዓለም ተተኪ የማይገኝላቸው አብነት ናቸው።»

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ