1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ አፍሪቃ የተዛመተው የኤቦላ ወረርሽኝ

ሐሙስ፣ ሰኔ 26 2006

የሰውነት አካላትን እያደማ ለሞት የሚዳርገው የኤቦላ ተኀዋሲ (ቫይረስ) ሥርጭት በምዕራብ አፍሪቃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ። በጊኒ በላይቤሪያ እና በሴራልዮን 467 ሰዎች በኤቦላ ተይዘው መሞታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ «ዳብል ዩ ኤች ኦ» አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1CVHI
Symbolbild Ebola
ምስል Cellou Binani/AFP/Getty Images
Ebola-Virus in Guinea
ምስል picture alliance/AP Photo

በነዚህ ሃገራት ኤቦላ በፍጥነት በመዛመት ላይ መሆኑን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ድርጅት አሳስቧል ። በጀርመን የድርጅቱ ተጠሪ ታንክሬድ ሽቶበ በሽታው ከሚዛመትባቸው ምክንያቶች አንዱ ተገቢ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አለመውሰድ መሆኑን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል ። የኤቦላ ወረረሽኝ በምዕራብ አፍሪቃ ከተከሠተበት ጊዜ አንስቶ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችም ሆኑ የጤና ባለሞያዎች የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ስርጭቱን መግታት አልቻሉም ። ይልቁንም በበሽታው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የሄደው ። በአሁኑ ጊዜ በጊኒ በላይቤሪያና በሲዬራ-ሊዮን ወደ 760 የሚጠጉ ሰዎች በበቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ። በጀርመን የድንበር የለሽ ሐኪሞች ድርጅት ተጠሪ ታንክሪድ ሽቶበ የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር ያልተቻለበትን ምክንያት እንዲህ ያብራራሉ ።

«በምዕራብ አፍሪቃ የምናየው ይህ ዓይነቱ ቫይረስ መድሃኒት የለውም ። ያ ማለትበቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ለሞት ሊዳረጉ የሚችሉበት እጣ ፈንታ ከፍተኛ ነው ። ሌላው ምክንያት ደግሞ በምዕራብ አፍሪቃ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ አለ ። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ድንበሮችን ተሻግረው ስለሚንቀሳቀሱ በቀላሉ ሊደረሱባቸው ወደ ማይችሉ አካባቢዎችም ቫይረሱን ያዛማታሉ ። እዚያ ያሉት የጤና ባለሞያዎች ደግሞ በበሽታው የተያዙትን በሙሉ ማግኘትም ሆነ ማከም አይችሉም ።»

Ebola-Virus Guinea
ምስል Seyllou/AFP/Getty Images

እስካሁን በጊኒ 303 በላይቤሪያ 65 እንዲሁም በሴራልዮን 99 ሰዎች በኤቦላ ቫይረስ መሞታቸው ተረጋግጧል ። የኤቦላን ስርጭት መግታት በሚቻልበት መንገድ ላይ ትናንት ጋና አክራ ውስጥ በመከረው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የጤና ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንደተነገረው በሽታውን መቋቋም ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት የገንዘብ አቅም ማነስ ነው ። ሌላው ችግር ደግሞ የህዝቡ ባህልና ስለ በሽታው ያለው አመለካከት መሆኑም ተወስቷል ። ለምሳሌ በላይቤሪያ ትልቁ ችግር ህብረተሰቡ በሽታው አለ ብሎ አለማመኑ መሆኑን ባለስልጣናት ይናገራሉ ። በዚህም ምክንያት ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙና በሽተኞቹንም ህብረተሰቡ ደብቆ ማስታመሙና መቅበሩ የኤቦላ ቫይረስ እንዲዛመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ነው የተገለፀው ። በኤቦላ የተያዙ ሰዎች ሲሞቱ አስከሬናቸው በጤና ባለሞያዎች እንዲቀበር ባለሥልጣናት ቢያሳስቡም ህብረተሰቡ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም ። ይህም በሽታው እንዲሰራጭ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ

ዋነኛው መሆኑን ሽቶይበ ተናግረዋል ።

«ቫይረሱ በዋነኛነት ሰውነት ውስጥ በሚገኙ ፈሳሾች አማካይነት ነው የሚተላለፈው ።በኤቦላ የሞተ ሰው ቀብር ከመካሄዱ በፊት ሰዉ አስከሬኑን ማጠብ እንዲሁም ማቀፍ ይፈልጋል ። ያን ጊዜ ነው በሽታው የሚተላለፈው ። ይህን ልምድ እንዲተዉ ማደረግ ከባድ ነው ። ሰዎች ስለ ቫይረሱ በዘልማድ የሚባለውን እንዳይከተሉ እና እንዳይረበሹ ከዚያ ይልቅ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በትክክል እንዲገነዘቡ መረጃ የመስጠት ሰፊ ዘመቻ ማካሄድ ያስፈልጋል ።ሟቹን ሲሰናበቱ ከአስከሬኑ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ መደረግ የለበትም ።»

Ebola Virus Virion
ምስል picture-alliance/dpa

በኤቦላ ለተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ የሚሰጡ የጤና ባለሞያዎች ስራቸውን የሚያከናውኑት በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ። በሌላ በኩል በሽታው በተከሰተባቸው ሃገራት የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ድርጅትን የመሳሰሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞች ለጥቃት መዳረጋቸው አልቀረም። ስራቸውን የሚያከናውኑበት ሁኔታም አስቸጋሪ ነው ።ሽቶይበ

«ሠራተኞቻችን እጆቹን ዘርግቶ የተቀበላቸው የለም ። ብዙ ጥርጣሬ አለ ። ከዚህ ሌላ የህክምና ባለሞያዎች የሚወስዷቸው የንፅህና አጠባበቅ እርምጃዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው ። ያ ማለት አድካሚ በሆነው በኃይለኛው ሙቀት በፕላስቲክ የህክምና ልብሶች ነው መሥራት ያለባቸው ። ያን ሁሉ እርምጃም ብንወስድ በሽታው መዛመቱ አንገታችንን እያስደፋን ነው ። »

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ኤቦላ ወደ ሌሎች ሃገራትም ይዛመታል የሚል ሥጋት አለ ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ