1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሞሮኮ የወጣቶችን ፍልሰት ለመቀነስ የተነቃቃ ጥረት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20 2008

ሞሮኮ ወደ አውሮጳ ለመሄድ ከሚፈልጉባቸው ኢትዮጵያን ከመሳሰሉ አፍሪቃውያት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ወጣቶቹ ሀገር ለቀው ለሚወጡበት ድርጊት አዘውትረው የሚሰጡት ምክንያት በሀገራቸው ደህና የወደፊት እድል የለም የሚል ነው።

https://p.dw.com/p/1Iegy
Marokko Jugend
ምስል DW

[No title]

የወጣቶች ፍልሰት በተለይ ካዛብላንካን ከመሳሰሉ ትላልቅ የሞሮኮ ከተሞች ወጣ ብለው በሚገኙት ሕዝብ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ይታያል። ወጣቶችን በመደገፍ እና ለነርሱም አዲስ እድል በመፍጠር ፍልሰትን ማስቀረት ይቻል ይሆን? ወጣቶች እንዳይቦዝኑ እና እንዳያፈልሱ ሲዲ ሙሜን በተባለ ችግር የበዛበት የካዛብላንካ ሰፈር አንድ ማዕከል ተከፍቶዋል።

« ወጣቶቹ የሚውሉበት፣ የሚሄዱበት ቦታ የለም። የሚሄዱበት ቦታ ሲያጡ ደግሞ የትም ይሄዳሉ። »


የሚሉት የወጣቶቹን ችግር የተረዱት ቡባከር ማዞዝ በሲዲ ሙሜን ወጣቶች የሚገናኙበት አንድ የባህል ማዕከል ከፍተዋል። የት እንደሚውሉ አያውቁም። ክራያቸው ውድ ያልሆኑ መንግሥት በችኮላ ያስገነባቸው ረጃጅም ህንፃዎች በቆሙበት ሲዲ ሙሜን የዕፀ ሱስ ዝውውር፣ ወንጀል እና ፅንፈኝነት ተስፋፍቶ የሚታይበት ችግር የበዛበት ትልቅ ጎስቋላ ሰፈር አለ። በዚሁ ቦታ ሰርተው እና ገንዘብ ይዘው የተሻለ የወደፊት ሕይወት መምራት የሚፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። ማዞዝ በከፈቱት ማዕከል ወጣቶች ስፖርት ሊሰሩ ወይም ሙዚቃ ሊለማመዱ ፣ መጽሐፍ ሊዋሱ ወይም ፈረንሳይኛ ቋንቋ ሊማሩ ይችላሉ። ወደ ማዕከሉ ለሚመጡት ልጃገረዶች እና ወጣት እናቶችም የልብስ ስፌት መኪኖች አዘጋጅተዋል።

ሙህሲን ባዳር የባህል ማዕከሉን ያወቀው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነበር። በሲዲ ሙሜን ያደጉት ሙህሲን ባዳር በዚያ መኖር ቀላል እንዳልነበረ ያስታውሳል።
« አስደሳች የልጅነት ጊዜ አልነበረም። ሲዲ ሙሜን ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት ቦታ ነው። ትምህርት ቤት ደርሶ መመለሱ ራሱ ብዙ ፈተና አለው፣ ሱስ አስያዥ ዕፅ ነጋዴዎች በየቦታው ያጋጥሙሀል። ይሁንና፣ ሲዲ ሙሜን አንዳንድ ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩ ብዙ ጥሩ ሰዎችም ያሉበት ቦታ ነው። »
ለሙህሲን የባህል ማዕከሉ ከለላ ያገኘበት፣ ከሌሎች ወጣቶች ጋር የተገናኘበት እና ተረጋግቶ መማር የቻለበት ቦታ ነው። አሁን በማዕከሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያስተምረው ሙህሲን በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በሞሮኮ ጥሩ የወደፊት እንዳለውም ያምናል።
« እርግጥ ነው ሞሮኮን ለቀው የሄዱ፣ ወደፊትም ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉም ብዙ ጓደኞች አሉኝ፤ የሚወጡትም በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው፣ እነሱም ክብር እና ኤኮኖሚ ይሰኛሉ። »
ወጣቶቹ ማንነታቸውን አስከብረው እና ጥሩ ሕይወት መምራት የሚያስችላቸው ስራ ይዘው መኖር እንደሚፈልጉ ነው ሙህሲን ያስረዳው። ቡበከር ማዞዝም ወጣቶቹ ይህንኑ ፍላጎታቸውን እዚያው ሞሮኮ ውስጥ ማሟላት እንዲችሉ ለመርዳት ነው የባህሉን ማዕከል የከፈቱት።
« እነዚህ ወጣቶች እውቅና ማግኘት ይፈልጋሉ። አብሯቸው መጓዝ፣ እንሱን መደገፍ ያስፈልጋል። እንዲሁ ልንተዋቸው አንችልም። »
የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ አሊን የመሳሰሉ ወጣቶች የባህል ማዕከሉ በመከፈቱ ደስተኞች ናቸው። በዐረቡ ዓለም የታወቀ ሙዚቀኛ መሆን ነው የሚፈልገው። አሊ የራፕ ሙዚቃውን በማዕከሉ ይለማመዳል። በሙዚቃው ስለችግሮች ብቻ ሳይሆን ስለመፍትሕያቸውም ያነሳል። በማዕከሉ የሚገናኙት የሲዲ ሙሜን ወጣቶች ስለዕለታዊ ችግራቸው መነጋገር ቢችሉም፣ እነርሱ ግን ወደፊት መሆን ስለሚፈልጉት መወያየቱን ነው የሚመርጡት።

Marokko Casblanca Müll
ምስል dapd
Karte Marokko Englisch

የንስ ቦርቸርስ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ