1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

ኤልዳና ወልዴ

ዓርብ፣ ሰኔ 2 2009

ወደ ጀርመን የመጡ አዳዲስ ጥገኝነት ፈላጊዎችን በቡና አዘገጃጀት ዘርፍ ማሰልጠንን ዋና አላማው ያደረገዉ « በመላ ቡና» „Bemela Coffee”የተባለ ድርጅት በዚህ ሳምንት እዚህ ጀርመን ሀገር ለሽልማት በቅቷል። 

https://p.dw.com/p/2eOMP
Deutschland Frankfurt - Eldana Wolde gewinnt in Frankfurt den „Social Impact Award“ für Bemela Coffee
ምስል A. Tesfamichael

በጀርመን ለሥራ ፈጠራዋ የተሸለመችዉ ኢትዮጵያዊ

እፀገነት በፍቃዱ ወልዴ ትባላለች። ሰው የሚያውቃት እና የሚጠራት ግን ኤልዳና ወልዴ በሚለው ስሟ ነው። ወጣቷ የጀርመኖቹ KFW ተቋም እና Social Impact ድርጅት በትብብር ባዘጋጁት የመጀመሪያው የሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ተሳትፋ ማክሰኞ ዕለት ከሦስት ተሸላሚዎች አንዷ ለመሆን በቅታለች። ይህም ከአንድ አመት ገደማ በፊት በመሠረተችው „Bemela Coffee” በተሰኘዉ ማሰልጠኛ ድርጅት አማካኝነት ነው። የስሙ ስያሜ መላ ወይም መፍትሄ መሆን እንደማለት ሲሆን መፍትሄ የሚሆነውም ለስደተኞች ነው።
« በመላ ቡና» በአሁን ሰዓት አምስት አባላት አሉት። የሚጠቀመው የኢትዮጵያን ቡና ሲሆን፤ ወደፊት የኮሎምቢያ እና የቬትናምንም ቡና የማስመጣት እቅድ አለው። የ 31 ዓመቷ ኤልዳና ኑሮዋን በጀርመን ካደረገች ስምንት አመታት ተቆጥረዋል። በዚህ መሀል ለአንድ አመት ወደ ታይላንድ በመሄድ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን የእንግሊዘኛ ቋንቋ እና የሥዕል ትምህርት በማስተማር ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጥታለች። ወደ ጀርመን ተመልሳም የሁለተኛ ዲግሪዋን  በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስተዳደር ማለትም NGO ማኔጅመንት አጠናቃለች። ከዚህም በተጨማሪ ኤልዳና ከውጭ ሀገር አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ እና ታይላንድ የሚጓዙ አገር ጎብኚዎችን በመላክ ዘርፍም እንደሠራች ትገልፃለች። በመጨረሻ ግን በቡና ንግዱ ለመፅናት ወስናለች። ልምዱን የቀሰመችው ደግሞ በተለያየ መንገድ ነው።
« በመላ ቡና»ን  ጨምሮ በመላው ጀርመን የሚገኙ የሥራ ፈጣሪዎች ሥራ የተገመገመው በዳኛ በመጨረሻም በኢንተርኔት በተሰጠ የሕዝብ ድምፅ ነው። ኤልዳና ሥራዋ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በጀርመናውያን ዘንድም ተቀባይነት እንዳገኘ አትጠራጠርም። የ Special Impact Award ፤ ማለትም የተለየ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሽልማት ተሸላሚ የሆነችው ኤልዳና የ 5000 € የገንዘብ ሽልማም አግኝታለች። ሌሎቹ ሁለት የሥራ ፈጠራ ተሸላሚ የሆኑት የሥራ ፈጣሪዎች እያንዳንዳቸው የ 20 000 € ባለቤት ሆነዋል። ኤልዳና ይህ ሽልማት እና እውቅና ማግኘት የበለጠ በሥራዋ እንድትገፋ እና ጥገኝነት ፈላጊዎች በአግባቡ እንዲሰለጥኑ በር ከፍቶላታል። « ስራም ጀምረናል» ትላለች።
ወደፊትስ « በመላ ቡና» እንዴት ይቀጥላል? ወጣቷ በተጓዘችበት ተመሳሳይ መንገድ መጓዝ የሚፈልጉ እና ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶችስ የሥራ ፈጠራቸውን የት እና እንዴት ማስተዋወቅ ይችላሉ?  የኤልዳና ወልዴን ምላሽ የድምፅ ዘገባውን ተጭነው ቢያዳምጡ ያገኙታል።
ልደት አበበ 
ሸዋዬ ለገሠ

Deutschland Frankfurt - Eldana Wolde gewinnt in Frankfurt den „Social Impact Award“ für Bemela Coffee
KFW ተቋም እና Social Impact ድርጅት በትብብር ያዘጋጁት የሥራ ፈጣሪዎች ውድድር እና ተሸላሚዎቹምስል A. Tesfamichael