በረሃማነትና ታላቁ አረንጓዴ ግንብ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:22 ደቂቃ
10.07.2018

ታላቁ አረንጓዴ ግንብ

በረሃማነት የዓለማችን ስጋት ከሆነ ሰነበተ። የዓለም የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ፤ የማገዶ ፍላጎትና የእርሻ ቦታ መስፋፋት የደን መመናመን እያስከተለ በረሃማነቱን እያባባሰው መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ። አፍሪቃ የሳህልና ሰሃራ አካባቢን በረሃ ተምሳሌታዊ በሆነ አረንጓዴ ግንብ የማካለል ሀሳብ ከተጠነሰሰ 10 ዓመታት አልፈዋል። እስካሁን ምን ተሠራ?

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ባለፈው ሳምንት ያወጣው እንደሚለው የዓለምን የደን ይዞታ የሚያሳየው ጥናት በአሁኑ ወቅት 7,6 ቢሊየን የሚገመተው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከ30 ዓመታት በኋላ 10 ቢሊየን እንደሚገባ ይጠበቃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዲያ የምግብ ፍላጎቴቱ በ50 በመቶ ያድጋል። ዋናው ጥያቄ ይህን ሕዝብ ለመመገብ እህል ማምረት የሚችል በቂ መሬት እና የኃይል አቅርቦቱ ከየት ይገኛል ነው። እዚህ ላይ ነው የዓለም የደን ሀብት አደጋ ላይ የሚወድቀው። ሙክታር ሴካንዴ በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO የዓለም አቀፍ በረሃማነትን የመከላከል ርምጃ አስተባባሪ ናቸው። በዓለም ደረጃ ወቅታዊውን የደን ይዞታ እንዲህ ይገልፁታል፤

«ባጠቃላይ የዓለምን የደን ይዞታ በሚመለከት የተገኘው መረጃ ያመለከተው፤ በበርካታ ቦታዎች የደን ውድመት በከፍተኛ ፍጥነት እየቀጠለ መሆኑን ነው። ይህም ማለት የደን ውድመቱ ሰዎች የየዕለት ፍላጎታቸውን ለማሟላት  የሚያደርጉትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች እየደረሰ ይገኛል።»

የደን ውድመቱ በተለያ የስፍራ የሚፈጸም ቢሆንም በተለይ በበረሃ አካባቢዎች ከድርቅ እና ከተፈጥሮ ይዞታው ጋር ተዳምሮ የከፋ መሆኑንም ያስገነዝባሉ ባለሙያው። በዓለማችን ትልቁ በረሃ የሚገኘው አፍሪቃ ውስጥ እንደሆነ እና እሱም የሰሃራ በረሃ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የአፍሪቃ ኅብረት በአህጉሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን በረሃማነት ለመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተጠቀሰውን በረሃማ አካባቢ የሚያካልል ታላቅ አረንጓዴ ግንብ የማበጀት ሃሳቡን ይፋ ካደረገ ከአስር ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ሙክታር ሳካንዴ ፕሮጀክቱ በአፍሪቃ ኮሚሽን አማካኝነት ሲታቀድ የሚታየውን ስጋት ይቀይራል የሚል መነሻ እንደነበረው ያስታውሳሉ። በሰሃራ እና ሳህል የአፍሪቃ አካባቢ የተፈጥሮ ሃብቱ ሁሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስተዋል የታቀደው ፕሮጀክት ትኩረቱ ምን እንደነበር ሲናገሩ፤

«ስለዚህ የአፍሪቃ ኅብረት ይህን ፕሮጀክት ይፋ ያደረገው በተጠቀሱት አካባቢዎች ያለው የተፈጥሮ ሀብት ተጠብቆ እንዲያገግም ማድረግን በማለም እና በስፍራው የሚኖረውን ማኅበረሰብ ለመርዳት ነበር። በዚህ ስፍራ የሚገኘው ኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዬ ከከብቶች እርባታ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብቱ ይዞታ እየተመናመነ በሄደ መጠን በዚያ ስፍራ የመኖሩ ነገር አስቸጋሪ እየሆነ መሄዱ አያነጋግርም። በዚህ ምክንያት ነው ይህ ሃሳብ የመጣው።»

ይህን ዕቅድ በተግባር ማዋሉ ግን ረዥም ጊዜ ወስዷል። በFAO የዓለም አቀፍ በረሃማነትን የመከላከል ርምጃ አስተባባሪ የሆኑት  ሙክታር ሳካንዴ እንደሚሉትም አሁንም በጉዳዩ ላይ በወጉ መወያየት እና ማቀድ አስፈላጊ ነው። እሳቸው እንደሚሉት ከመነሻው ታቅዶ የነበረው 15 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ስፍራ ላይ ፤ እንዲሁም ከጅቡቲ አንስቶ እስከ ሴኔጋል ድረስ 8000 ኪሎ ሜትር የሚያካልል ዛፎችን የመትከል ሀሳብ ነበር። ይህ በፖለቲከኞች የተቀመረው ዕቅድ ሲታይ የሚያጓጓ እና የሚያማልል ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን ችግር የሚያጣው አይመስልም። ባለሙያው ምክንያቱን ያስረዳሉ።

«ወደቴክኒኩ ስንገባ ይህ ተግባራዊ መሆን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በዚያ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ይዞታ ውስጥ ዛፎችን ማብቀሉ የማይሆን ነው። ስለዚህ ባለሙያዎቹ በአካባቢው የሚኖረውን ኅብረተሰብ እየረዳ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ማጥናት ቀጠሉ። ለምሳሌ የአካባቢውን ተፈጥሮ ለማሻሻል እና ምርታማ መሆን እንዲችል የሚረዱ የተፈጥሮ ክብካቤ እና ጥበቃ ሥራዎች መከናወን አንዱ ነው።»

FAO ታላቅ አረንጓዴ ግንብ የሚነካቸው የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሃገራት በየበኩላቸው ሊያደርጉት የሚችሉትን እንዲያጠኑ ሀሳብ ማቅረቡን ይናገራሉ ሳካንዴ። በዚህ ምክንያትም ያለውን የተፈጥሮ አካባቢ እየተንከባከቡ እንዲያገግም የማድረጉ ርምጃ ግንባር ቀደም የሆነውም ባይናቸው። ይህን ሥራ ላይ የሚያውል የገንዘብ ርዳታ በመያዝም ወደተግባር ተገባ።

«በአሁኑ ወቅት በረሀማነትን በመከላከሉ መርሃግብር ስድስት ሃገራትን በመደገፍ ላይ ነን። መርሃግብሩም በአካባቢው ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ኒዠር፣ ቡርኪና ፋሶ፤ ሴኔጋል እና ጋምቢያን ያጠቃልላል። በተመሳሳይ ሌሎቹን ሃገራትም ለመደገፍ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እየፈለግን ነው።»

ለመሆኑ በተግባር ምን እየተደረገ ይሆን?

«በዚህ አማካኝነት አጠቃላይ የማገገም ሥራ ነው የምናካሂደው። አካሄዱም እንዴት ማድረግ እንደሚኖርበት እና ሰው እና ተክሎች ያላቸውን ግንኙነት፤ እንዴት ያሉ የተክል ዝርያዎችን  ለምን ጉዳይ ይፈልጉታል፤ የሚለውን ኅብረሰቡን የማማከር ሥራ ይካሄዳል። በተጨማሪም እንዴት ያሉ መሬቶችን ከሰው እና እንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ እንደሚገባ፤ ዛፎች ባሉበት አካባቢስ ምን መሰራት ይኖርበታል የሚለውን ሃሳብ ይቀያየራል። በዚያም ላይ የትኞቹ የዛፍ ዝርያዎች በዚያ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ ማደግ ይችላሉ የሚለው ላይም ተነጋግሯል።»

በዚህ ሂደትም ለተባለው የአካባቢ ተፈጥሮ የማገገም እና ለበረሃው የሚሆኑ ተክሎችን የማማረጡ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ዘርዝረዋል። በዚህ በረሃማ አካባቢ ሙክታር ሴኬንዳ እንደሚሉት ዝናብ የሚገኘው በዓመት ባማካኝ ከ2 እስከ 4 ወራት ብቻ ነው። እናም እንዲህ ባለው አካባቢ የዝናብ ውኃን ጠብቆ ለማጠራቀም ተግባሩ ቀላል አይሆንም። የአካባቢው ኅብረተሰብ በዘልማድ የራሱ ውኃ የማጠራቀሚያ እና ማቆያ ስልት እንዳለው ግን ሳይገልፁ አላለፉም። በሰሃራ እና ሳህል በረሃ ላይ እንዲከናወን የታቀደው እና  ብዙ ሲባልልነት የነበረው የታላቁ አረንጓዴ ግንብ ሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ አፍሪቃን የሚያካልል ነው።

በታላቁ አረንጓዴ ግንብ አካባቢም 282 ሚሊየን  ሕዝብ እንደሚኖር ነው ሳካንዴ የሚናገሩት። የተመድ ዘላቂነት ያለው የልማት ግብ ለማሳካት ከተሠራ ደግሞ በFAO ቅኝት እና ጥናት መሠረት ደግሞ በየዓመቱ 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት እንዲያገግም ማድረግ ይፈለጋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ መጀመሩን የሚናገሩት ሙክታር ሴኬንዳ ሥራው ቀላል እንዳልሆነና እና ፈተናዎች እንዳሉት ሳይገልጹ አላለፉም። ከፈተናዎቹ አንዱ ደግሞ ለዚህ የሚውለው የገንዘብ ጉዳይ ነው። የተጠቀሰውን ታላቁ አረንጓዴ ግንብ እውን ማድረግ የየሃገራቱ መንግሥታት ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። እሳቸው እንደሚሉት አረንጓዴው ግንብ ከሚነካቸው ሃገራት መካከል ሴኔጋል ብቻ ናት ከጎርጎሪዮሳዊው 2007ዓ,ም አንስታ በበረሃማው አካባቢ ከሚኖረው ማኅበረሰቧ ጋር ሊደረግ የሚገባውን በመነጋገር የጀማመረችው። በሌሎቹ የሚታየው የአካባቢው ይዞታ ከግምት ሳይገባ አንዳንድ የዛፍ ችግኞችን መትከል ቢሆንም ያ ግን ውጤት አላመጣም ይላሉ ሳካንዴ።

«በመሬቱ ላይ በተግባር እንዳየነው በርካታ የአካባቢ ተፈጥሮ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንዳንድ የዛፍ ችግኞችን ከቦታው የአየር ሁኔታ ጋር መስማማታቸው ሳይጠና ተክለዋል። ይህ በመደረጉም የተመዘገበ ስኬት የለም። ስለዚህ በትክክል ምን መሠራት እንዳለበት ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን ተረድተናል። አሁን ባለንበት ደረጃም ከሚተከሉት የዛፍ አይነቶች አንስቶ በስፍራው መሬት ላይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን መርምረናል።»

የተካሄደው የቴክኒክ ጥናትም የትኛው የዛፍ ዘር በየት ቦታ፤ መቼ እና እንዴት መተከል አለበት የሚለውን ግልጽ አውጥቷል ይላሉ። በረሃማነትን ለመከላከል ከአውሮጳ ኅብረት በተሰጠ የገንዘብ ድጋፍም በFAO አማካኝነት በስድስት የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ 12,000 ሄክታር የሚሸፍን አካባቢን የተፈጥሮ ይዞታ እንዲያገግም ለማድረግ ከዛሬ 3 ዓመታት በፊት አንስቶ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል። እስካሁንም ቡርኪናፋሶ 5 ሺህ ሄክታር፣ 3 ሺህ ሄክታር ኒዠር፣ ሴኔጋል ተመሳሳይ 3 ሺህ፤ 2 ሺህ ሄክታር ናይጀሪያ በረሃማ መሬት መልሶ የማገገም ስራ እየተሰራበት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ትግራይ እና አፋር ክልሎች ውስጥ ተመሳሳይ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በያዝነው ዓመትም ወደ 18 ሺህ ሄክታር ላይ ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አመልክተዋል። ይህ ተፈጥሮ መልሶ እንዲያገግም የማድረጉ ሥራ በተጠቀሱት ሃገራት ገጠር ቀበሌዎች የሚከናወን ሲሆን እስካሁንም ከ200 በላይ የገጠር ቀበሌዎችን ማዳረሱንም ዘርዝረዋል።

አፍሪቃ ውስጥ እንጨት ዋናው የኃይል ምንጭነቱ ዛሬም በሌላ የኃይል አቅርቦት አልተተካም። ከሕዝብ ቁጥር እያደር መጨመር ጋር ተያይዞ ሲታይ ታዲያ አህጉሪቱን ለከፍተኛ የደን መራቆት እያጋለጣት መሆኑ ይነገራል። ይህ መሠረታዊ ችግር እና አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ያመለከቱት ሙክታር ሳካንዴ አማራጭ የኃይል አቅርቦቶች እስኪኖሩ ተጨማሪ ዛፎችን መትከሉ መተኪያ የለውም ነው የሚሉት። በየቦታው የሚተከለው የዛፍ ዘር የማገዶ ፍላጎትን የሚመልስ ብቻ ሳይሆን ለብዝሃሕይወቱ ስብጥርም የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ መሆኑንም አፅንኦት ይሰጣሉ።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ጽንሰ ሀሳብ በቅርቡ የመጣ ሳይሆን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለለ ታሪክ ነው። በጎርጎሪዮሳዊው 1952 የሰሃራ በረሃን ያቋረጠው ሪቻርድ ሴት ባርቤ ቤከር በአህጉሩ 48 ኪሎ ሜትር ገደማ በረሃውን የሚያካልል የዛፍ ችግኝ እንዲተከል ሃሳብ አቅርቦ ነበር። የዛሬ 16 ዓመት ንጃሚና ቻድ ላይ በረሃማነት እና ድርቅን ለመከላከል በተካሄደ ልዩ ጉባኤ ላይ ጥንስስ ሆኖ ቀረበ። ከሦስት ዓመታት በኋላ በሳህል እና ሰሃራ አካባቢ ሃገራት መንግሥታት ይሁንታ አገኘ። በተግባር የመግለፁ ሂደት ግን ባለሙያው እንዳሉት የገንዘብ አቅምን ጨምሮ ከፍተኛ ጥረትን እንደጠየቀ ባለበት አለ። ለሰጡን ማብራሪያ FAO የዓለም አቀፍ በረሃማነትን የመከላከል ርምጃ አስተባባሪን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ከማዕቀፉ ተጨማሪ ዘገባዎች