1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሩስያ የኮሮና ስርጭት ቀዉስና ኢትዮጵያዉን

ሐሙስ፣ ሰኔ 18 2012

«በአጠቃላይ በሩስያ ክልል ዉስጥ ወደ 7000 የሚሆን አፍሪቃዉያን የዲያስፖራ  አባላት ይገኛሉ። ኮሮና በአስከተለባቸዉ ሕመምሕይወታቸዉንም ያጡም አሉ። ከኢትዮጵያዉያን መካከል በኮሮና የታመሙ አሉ ። ከነቤተሰቦቻቸዉ ታመዉ ድነዋል።  አንድ በቤላሩስያ ሃገር የታመመ ኢትዮጵያዊ ጓደኛችን ነበር ሕይወቱን አጥቶአል።»

https://p.dw.com/p/3eLLu
Russlsnd Moskau Coronavirus
ምስል Getty Images/AFP/K. Kudryavtsev

በሩስያ የኮሮና ስርጭት ቀዉስና ኢትዮጵያዉን

 

«በአጠቃላይ በሩስያ ክልል ዉስጥ ወደ 7000 የሚሆን አፍሪቃዉያን የዲያስፖራ  አባላት ይገኛሉ። ኮሮና በአስከተለባቸዉ ሕመምሕይወታቸዉንም ያጡም አሉ። ከኢትዮጵያዉያን መካከል በኮሮና የታመሙ አሉ ። ከነቤተሰቦቻቸዉ ታመዉ ድነዋል።  አንድ በቤላሩስያ ሃገር የታመመ ኢትዮጵያዊ ጓደኛችን ነበር ሕይወቱን አጥቶአል።»

በሩስያ መዲና ሞስኮ ነዋሪ የሆኑት የዩንቨርስቲ መምህሩ ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ናቸዉ። እንደ ፕሮፊሰር ዘነበ ኑሮአቸዉን ሩስያ አድርገዉ ቤተሰብ መስርተዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ወደ 100 ይሆናሉ። ዩክሪይን ቤላሩስያ በአጠቃላይ በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ዉስጥ አጠቃለን ያየን እንደሆን ደግሞ ወደ 300 ኢትዮጵያዉያን እና ቤተሰቦቻቸዉ ይኖራሉ ብለዋል። በሩስያ ወደ 7000 የሚሆኑ አፍሪቃዉያን ይገኛሉ።

ከነቤተሰቦቻቸዉ ወደ 10 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎአል። በሩስያ የኮሮና ስርጭት ቀዉስ እና ጥንቃቄዉ እንዴት ይሆን? ኢትዮጵያዉያኑስ ? መዲና ሞስኮ በሚገኘዉ Peoples' Friendship University ማለትም የሕዝቦች ወዳጅነት ዩንቨርስቲ በመባል በሚታወቀዉ ሞስኮ በሚገኘዉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም «ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነት ትምህርትን የሚሰጡት ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ በሩስያ የአፍሪቃዉያን ሕብረት ሊቀመንበር ናቸዉ።  

Professor Zenebe Kinfu
ምስል Zenebe Kinfu

«ሩስያዉስጥ የሚኖሩ አፍሪቃዉያንን ለሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። አንደኛዉ የአፍሪቃ ዲያስፖራ የሚባለዉና እኔ የምመራዉን የኅብረተሰብ  ክፍል ነዉ። ሁለተኛዉ የአፍሪቃዉያን ቡድን ደግሞ ለትምህርት ከተለያየ የአፍሪቃ ሃገራት የመጡትን ነዉ። በብዛት ያየን እንደሆነ  በአጠቃላይ በሩስያ ዉስጥ ወደ ሰባት ሽህ አፍሪቃዉያን ይኖራሉ። ከነቤተሰቦቻቸዉ ደግሞ ወደ አስር ሽህ ይሆናሉ። ተማሪዎችን የተመለከትን እንደሆነ የማስትሪት ዲግሪን ለመያዝ የመጡት አምስት እና ስድስት ዓመት ይኖራሉ ከዝያም ወደ ሃገራቸዉ ይመለሳሉ። ዶክትሬት ከቀጠሉ ደግሞ ስምንት ዓመት ይኖራሉ። በአጠቃላይ አፍሪቃዉያን ተማሪዎች በሩስያ ወደ 16 ሺህ ይሆናሉ።  ኢትዮጵያዉያን ጥቂቶች ነን። በተለይ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲተያይ እጅግ ጥቂት ነን ማለት ይቻላል።

በሩስያ የሚኖሩ አፍሪቃዉያን በተለያየ ስራ ላይ ተሰማርተዉ ይገኛሉ። በአብዛኛዉ የተሰማሩት በንግድ ላይ ነዉ። ሁለተኛዉ ክፍል አፍሪቃዊ የተሰማራዉ ደግሞ ደግሞ በሕክምና በዩንቨርስቲ እና በተለያዩ ተቋማት ዉስጥ በማስተማር ነዉ። ከዚህ ዉጭ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪቃዉያን ሴቶች የፈጠሩት ስራ  ፀጉር መስራት የአፍሪቃዉያንን  ባህላዊ አልባሳትና  እቃዎችን በመሸጥ ነዉ።  

«ሌላዉ በ1990 ዎቹ ከአፍሪቃዉያን አባቶች እና ከሩስያዉያን ሴቶች የተወለዱት ክልሶቹ አፍሪቃ ሩስያዉያን አዲስ ትዉልድ እያደገ ነዉ። በርግጥ አብዛኞች አባቶች ወደየሃገሮቻቸዉ ተመልሰዋል። አልያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እነዚህ ከ 15 እና 20 ዓመት በላi የሆኑት ወጣት አፍሪቃዉያን ክልሶች በፊልም በሚዲያ ተሰማርተዉ ይገኛሉ። የቀዶ ጥገና ሃኪሞችም አሉ። እንደዉም ከኢትዮጵያዉያን የተወለዱ የቀዶ ጥገና ሃኮሞች አሉን።»    

ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2019 ዓመት መጨረሻ ታኅሳስ ወር ላይ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ከቻይና ቢጀምርም ሩስያ ቁጥጥር የጀመረችዉ መጋቢት መጀመርያ ላይ እንደነበር ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ተናግረዋል። በሽዎች የሚቆጠሩ ተጓዦች በምድር ባቡር፤ በአዉቶቡስ ብሎም በአዉሮፕላን ከጎረቤት ሃገር ቻይና ወደ ሩስያ ገብተዋል።  በአንፃሩ ከሩስያ ወደ ቻይናም ተጉዘዋል። ይሁንና ሩስያ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት የኮሮና ተኅዋሲ በዓለም እየተዛመተ ያለ ወረርሽኝ መሆኑን ከአወጀ በኋላ በኮሮና ላይ ዘመቻን መጀመርዋን  ዶ/ር ክንፉ ታፈሰ ተናግረዋል።     

Russland Moskau Coronavirus Desinfektion
ምስል picture-alliance/dpa/S. Fadeichev

በሩስያ በኮቪድ ቁጥጥር ዘግይቶአል፤ የሞተዉ ሰዉ ቁጥር ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነዉ ይባላል። በሌላ በኩል ሃገሪቱ የሟች ቁጥርን ሆነ በኮሮና የተያዘዉን  ሰዉ ቁጥር ትደብቃለች የሚባል ነገር ይሰማል ለሚለዉ ጥያቄ ፤ ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ተደበቀም አልተደበቀም አሁንም ቢሆን በየቀኑ ወደ ሰባት ሽህ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይፋ በመሆኑ ቁጥሩ ቀላል ነዉ ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።  በሩስያ የኮሮና ተኅዋሲ መዛመቱ ሳይታወቅ ሃኪሞች እንብዛም ጥንቃቄ ባለማድረጋቸዉ ሩስያ ብዙ የሕክምና ባለሞያዎችን ከፍተና ዶክተሮችን በኮሮና ምክንያት ሕይወታቸዉን እንዳጡም ተናግረዋል።  ከ 500 በላይ የሕክምና ባለሞያዎች ማለትም ወደ 7% ሃኪሞች ሕይወታቸዉን አጥተዋል።  ሃኪሞች በከፍተኛ ቁጥር በሩስያ መሞታቸዉ በዓለም ደረጃ ከፍተኛዉ ሳይሆን እንዳልቀረም ተናግረዋል።

በኮሮና ምክንያት ሩስያ ከአፍሪቃ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እጅግ መዳከሙን የተናገሩት ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ፤ በተለይ የአበባ እና የፍራፍሪ ንግድ መቆሙን ተናግረዋል። በዚህም አፍሪቃዉያን ተጎድተዋል ብለዋል።  

ሞስኮ በሚገኝ ዩንቨርስቲ መምህር እና በሩስያ የአፍሪቃዉያን ኅብረት ሊቀመንበር ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በ«DW» እያመሰገንን ፤ ሙሉዉን የቅንብር የድምጽ ማድመቻ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 

 አዜብ ታደሰ  

ኂሩት መለሰ