1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ተራሮች የተነሳው ቃጠሎ አሁንም አልበረደም

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21 2011

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው ቃጠሎ አሁንም አልበረደም፣ የአውሮፕላን እርዳታ ከፌደራል መንግስት ቢጠየቅም አልተሳካም ተብሏል፡፡ትናንትና ረፋዱ ላይ እሳቱ የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶበት የነበረ ቢሆንም ባለው ደረቃማ የአየር ሁኔታና ነፋስ ታግዞ እሳቱ አገርሽቷል።

https://p.dw.com/p/3Fvqs
Bildergalerie Rote Liste des gefährdeten Welterbes (Nationalpark Simien)
ምስል picture alliance/Robert Harding

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሰሜን ጎንደር ዞን ይገኛል፡፡ ፓርኩ ጭላዳ ዝንጀሮን፣ ተኩላንና ድኩላን ጭምሮ የበርካታ
ብርቅዬ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው፡፡ ከፓርኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳው ከ50 በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ወፎችም
በፓርኩ ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታላቁ የዳሸን ተራራም በዚሁ የፓርክ ክልል ይገኛል፡፡

ባለፈው ሐሙስ አመሻሱ ላይ በፓርኩ የተለያዩ አቅጣቻዎች የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎችና
ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

ትናንትና ረፋዱ ላይ እሳቱ የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶበት የነበረ ሲሆን ባለው ደረቃማ የአየር ሁኔታና ነፋስ ታግዞ እሳቱ
ማገርሸቱን የደባርቅ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምርኩዝ ዋሴ ለDW Deutsche Welle ራዲዮ ተናግረው ነበር፡፡

ዛሬም ሌሊቱን ሙሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፀጥታ ኃይሉም ጭምር እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ሲደረግ ማደሩንና
አሁንም ቢሆን እሳቱ ሙሉ በሙሉ መጥፋት እናዳልቻለ አቶ ምርኩዝ በስልክ ተናግረዋል፡፡

Blutbrust-Paviane
ምስል picture-alliance/blickwinkel/C. Lundqvist

የሰሜን ተራሮች ፓርክ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው በበኩላቸው ከአጎራባች ወረዳዎች ጭምር የሰው ኃይል
እገዛ ቢያደርግም አሳቱ እየሰፋ መምጣቱን ከምክንያቱ ጋር ያብራራሉ።የአውሮፕላን እገዛ ቢጠየቅም ምላሽ እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ታደሰ 
እስካሁን በቃጠለው ከ340 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል መቃጠሉንም አመልክተዋል፡፡

220 ኪሎሜትር ካሬ ስፋት ያለው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እ . ኤ . አ በ1969 የተመሰረተ ሲሆን በ1978
ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የትምህረት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ