1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የፀጥታ ኃይሉ ከነዋሪው ጋር ተፋጥጦ ውሏል»- የቆቦ ነዋሪዎች

ዓርብ፣ ጥር 18 2010

በሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው ቆቦ ከተማ ዛሬም ውጥረት እንደነገሰባት መዋሏን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ አመለከቱ። እንደነዋሪዎቹ ገለጻ በዛሬው ዕለትም የሰው ሕይወት ሳይጠፋ አልቀረም። የክልሉ ባለስልጣናት ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት ቆቦ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2raoY
Karte Äthiopien englisch

«ዛሬም የቆቦ ከተማ ዉጥረት አልተለያትም፤» ነዋሪዎች

የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ዛሬም ቆቦ በፀጥታ ኃይሎች ተከባ ነው የዋለችው። ሄሊኮፕተሮች ሳይቀሩ ዝቅ ብለው እየበረሩ ሲቃኙ መዋላቸውንም ይናገራሉ።

«መከላከያ ፌደራል ሁሉ ከህዝቡ ላይ ጥይት ደቅኖብናል በጣም ነው የተሰቃየነው። ዛሬም አራት ሰዓት አካባቢ ላይ።»

«አስፈሪ ድባብ ነው ያለው። ግለሰቦችን ትጥቅ እንዳትታጠቁ ብለው አስጠንቅቀዋል። ስምንት፤ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሄሊኮፕተሮች ይታዩ ነበር ከተማው ላይ። በተደጋጋሚ ለዓይን በጣም ቅርብ በሆነ ርቀት ከተማዋን ሲዞኑ ነበር። ፌደራል ፖሊስ እና አጋዚ ፖሊስ ሰላማዊውን ሰው ሲደበድቡ ነበር።»

ስለቆቦ ውሎ የገለፁልን በሙሉ ማንነታቸው እንዲገለፅ እንደማይፈልጉ፤ ድምጻቸውም እንዲለወጥ በጠየቁን መሠረት ለደህንነታቸው ሲባል ድምፃቸው መቀየሩን መግለጽ እንወዳለን። ሌላኛው በስልክ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ የፀጥታ ኃይሎች በየቦታው እየገቡ ነዋሪዎችን ደብድበዋል ይላሉ።

«የዛሬው ውሎ ያው ውጥረት የተሞላበት ነው መከላከያ ሰላማዊውን ሰው እንደበደበ ነው ያለው፤ እናቶች እያለቀሱ ነው ያሉት፤ ውስጥ ለውስጥ በአምቡላንስ እና በመኪናዎች እየገቡ እያፈሱ እየወሰዱ ነው ያሉት።»

ሕዝቡን ለማነጋገርም ሆነ ሁኔታውን ለማረጋጋት የክልሉ ባለስልጣንት በዛሬው ዕለት ወደቆቦ መግባታቸውን የገለፁልን የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የሕዝቡ ስሜት ነው እንዲህ ይገልጹታል።

«የዚህ የቆቦ ተወላጅ ናቸው አቶ አለምነው መኮንን፤ እሳቸው መጥተው ሕዝቡን ያረጋጉታል ተብሎ አይታሰብም።»

ስለሁኔታው ማብራሪያ ለማግኘት ወደክልሉ የሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለስልጣናትም ሆነ ወደሰሜን ወሎ ዞን የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ እንዲሁም ወደቆቦ ከተማ ከንቲ ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ ባለማግኘቱ አልተሳካም።

ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ በወልድያ እንዲሁም ከማክሰኞ ዕለት አንስቶ ደግሞ በቆቦ የሚታየውን የሰው ሕይወት የጠፋበት ግጭት እና ውጥረት አስመልክተው የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ለግጭቱ መንስኤ የሆነው በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከማቸ ቅሬታ እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ