1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እስካሁን ያልጠሩ ነገሮች እንዳሉ ማሳያ ነው»

ቅዳሜ፣ መስከረም 15 2014

ሱዳን የሽግግር መንግሥት የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን በተመለከተ ባወጣው መግለጫው የመፈንቅለ መንግስት ሴራውን የወጠኑት ከሁለት ዓመት በፊት ከመንበረ ሥልጣናቸው ከተወገዱት  ኦማር አልበሽር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንደሆኑ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/40qCs

ትኩረት በአፍሪቃ

ባለፈው ማክሰኞ በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከተሞከረ በኋላ መክሸፉ ተነግሯል። የሱዳን የሽግግር መንግሥት የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን በተመለከተ ባወጣው መግለጫው የመፈንቅለ መንግስት ሴራውን የወጠኑት ከሁለት ዓመት በፊት ከመንበረ ሥልጣናቸው ከተወገዱት  ኦማር አልበሽር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንደሆኑ ገልጿል። ነገ እሁድ የሚደረገው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን አሰናብቶ በይፋ አዲሱን መራኄ ወይንም መራኂተ መንግስት ሊቀበል በይፋ ድምፅ ይሰጥበታል። የአንድሮው የጀርመን ምርጫ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ለሚኖራት ቀጣይ ግንኙነት ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን? ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በሁለት ርዕሰጉዳዮች ላይ ያተኮረው የዕለቱ የትኩረት በአፍሪቃ መሰናዷችን ተጀምሯል። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ መልካም ቆይታ !
መሸጋገሪያ 
ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ የሱዳን ብሔራዊ የቴሌቪዝን ጣቢያ በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ መክሸፉን ይፋ አደረገ። በዕለቱ ከካርቱም የወጣውን ዜና በርካታ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በፍጥነት ሲቀባበሉት፤ ከሸፈ የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት በእርግጥም ስለ መክሸፉ በጥርጣሬ የተመለከቱትም አልጠፉም። አሁን በሽግግር ሂደት ላይ ያለው የሀገሪቱ መንግሥት በራሱ የመጣው በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግስት ነውና ። በመፈንቅለመንግሥት ሙከራው ወታደሮቹ በናይል ወንዝ ላይ የተዘረጋ አንድ ድልድይን  እና የሀገሪቱን ብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ ለመቆጣጠር ጥረት አድርገው እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል። የሀገሪቱ መንግሥት ሙከራውን ካከሸፈ በሆላ በሴራ ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ የተባሉ ወታደራዊ መኮንኖች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ሲገልጽ  ቆይቷል። በእርግጥ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ጠንሳሽ አሁንም ድረስ በይፋ አልተገለጸም። ይህ ደግሞ ሱዳን የሽግግር ጊዜዋን ሊያራዝምባት የሚችል ሁኔታ እንዳለ ማሳያ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው። ለሱዳን ወቅታዊ አለመረጋጋት ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር በድንበር ይገባኛል እና አሁንም ድረስ መቋጫ ያላገኘው የህዳሴው ግድብ ጉዳይ፤ በጎሳዎች መካከል የሚደረግ ግጭት እንዲሁም መቆሚያ ያጣው ኢኮኖሚያዊ ድቀት ተጠቃሾች ናቸው።
የካርቱም ከተማ ነዋሪው ሙአሚን ሀሰን እንደሚለው በሀገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት ወደላይ እንጂ መቀነስ እያሳየ እንዳልሆነ  ነው። 
«ባለፈው ዓመት የቁሳቁሶች ዋጋ ዝቅተኛ ነበር፤ በዚህ ዓመት ግን  በእጥፍ ጨምሯል። ​​»
በሱዳን የሽግግር መንግስቱ ያመጣል ተብሎ ከታሰበለት ለውጥ አንጻር በጥርጣሬ የሚመለከቱ በርካቶች እንደሆኑ ይነገራል። ለምሳሌ ባለፈው ሰኞ ዕለት የወታደራዊ መፈንቅለመንግስቱ ከመደረጉ አንድ ቀን አስቀድሞ ማዕከላዊ የሀገሪቱን ክፍል ከምስራቃዊ ክፍል የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች ሃዳንዳዋ በተባሉ ታጣቂ ጎሳዎች አማካኝነት  ተዘግቶ እንደነበር ተገልጿል። 
የሱዳን መንግሥትን በመቃወም ተሳታፊ የነበረው መሐመድ ሀሰን እንደሚለው ዋናውን የፖርት ሱዳንን ወደብ ከማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚያገናኘውን ጎዳና ለተወሰነ ጊዜ ዘግተውት ነበር። 
«አምቡላንሶች፣ የጉብኝት አውቶቡሶች እና የግል መኪናዎች እንዲያልፉ ይፈቅዱላቸዋል። ነገር ግን ነዳጅ ፣ ሲሚንቶ ወይም ሌሎች የንግድ ቁሳቁሶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች  በአካባቢው እንዳያልፉ አግደዋቸዋል።»
በሱዳን ተሞክሮ የከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሱዳን ከታዩ ማኅበረ-ፖለቲካ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንጻር አዲስ ክስተት ወይም የማይጠበቅ እንዳልሆነ የሚናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ስትራቴጂካዊ  ጉዳዮች ተቋም በተመራማሪነት የሚሰሩት ዶ/ር ዳርእስከዳር ታዬ ናቸው። መፈንቅለ መንግስቱ መሞከሩ በራሱ ራሱን የቻለ አንድምታ አለው ባይ ናቸው።   
በሱዳን በተለይም የውስጥ ችግር ተደርገው ከሚወሰዱ ጉዳዮች  በጎሳዎች መካከል ከሚደረጉ ግጭቶች እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጣጣዎች ከሚያሳድሯቸው ተጽዕኖዎች በላይ  የሽግግር መንግሥቱን በጥምረት በሚመሩት የሲቪል አስተዳደር ተወካዮች እና የወታደራዊው ክንፍ ባለሥልጣናት  መካከል አለመተማመን መኖሩን የሚያመላክቱ ጉዳዮች መታየታቸው አንዱ ማሳያ እንደሆነ ዶ/ር ዳርእስከ ዳር ይናገራሉ። 
የቀድሞውን አምባገነን ኦማር አልበሽርን ለሦስት ዐሥርተ-ዓመታት ከተቆናጠጡበት መንበረ ስልጣናቸው ያሰናበተው የሱዳን አብዮት ወታደሩን ከሲቪሉ አጣምሮ የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ አስችሏል። ሂደቱ በደርዘን ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ሱዳንን ከምዕራባውያን አስታርቆ ቀደም ሲል ከተፈረጀችበት ሽብርተንነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እንድታገኝ አስችሏታል። የሰሞንኛውን የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሙከራውንም ተከትሎ የዩናይትድስቴትስ ባለስልጣናት ድርጊቱን ተቃውመውታል። ይህ ደግሞ ምዕራባውያን አሁንም ድረስ በሱዳን የሽግግር መንግስት ላይ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚነገረው። የስትራቴጂያዊ  ጉዳዮች አጥኚ ባለሞያው ግን  የሱዳን የሽግግር መንግስት ከምዕራባውያን ጋር በደረሰው መግባባት ልክ የሚያከናውናቸው ተግባራት በሀገር ውስጥ የተወጠፉበትን የቤት ሥራዎችን ካላጠራ የትም አያደርስም ባይ ናቸው ።
ሱዳን ውስጥ በየትኛውም መልኩ የሚከሰት አለመረጋጋት ለጎረቤት ሀገራት መትረፉ ስለማይቀር አሳሳቢ ነው የሚሉት ዶ/ር ዳር እስከ ዳር በሱዳን የሚቃጡ አለመረጋጋቶች በቀጥታ ተጽዕኖ ከሚደርስባቸው  ሀገራት ኢትዮጵያን በቀዳሚነት ተጠቃሽ አድርገዋል። 
በሱዳን ከተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑን መንግሥታዊው የዜና ምንጭ ሱና ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዖማር አል በባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሱዳን ውስጥ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች መደረጋቸውን ሲገለጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣው ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅት ለማስተጓጎል ነው የሚሉ ትችቶችም ይደመጣሉ። 
በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል። በእርግጥ ይሳካ ይሆን ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። 

Äthiopien | Bahir Dar Universität | Beziehungen Sudan
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Sudan | nach Putschversuch | Kabinettsversammlung
ምስል AFP/Getty Images
Libyen Sirte | Früherer sudanesischer Präsident | Omar Hassan al-Baschir
ምስል Photoshot/picture alliance
Sudan Port Sudan | Hafenblockade
ምስል Ibrahim Ishaq/AFP/Getty Images
Sudan | Khartum nach dem gescheiterten Putschversuch
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images
Sudan | Khartum nach dem gescheiterten Putschversuch
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images
Sudan | Soldaten ARCHIV
ምስል Hussein Malla/AP Photo/picture alliance

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ማን እንደሚተካቸው ለማወቅ ትንፋሼን ውጬ እጠብቃለሁ የምትለው የዶይቼ ቬለዋ ሚሚ ሜፎ ቀጣዩ የጀርመን መራኄ አለያም መራኂተ መንግሥት ከአፍሪቃ አንጻር የሚከተሏቸው የውጭ ፖሊሲዎች በስጋት ተመልክታለች። 
ሚሚ ሜፎ አፍሪቃዊ እንደመሆኔ መጠን ምርጫውን በአንክሮ እከታተላለሁ ትላለች።  ይህን የማደርገው ጀርመን ውስጥ ስላለሁ ብቻ አይደለም ፤ ይልቁኑ ሃገሪቱ ከአፍሪቃ ጋር ላላት ግንኙነት ምን ማለት እንደሆነ የሚገለጥበት ጭምር ስለሆነ ነው የሚል ሐሳብ ሰንዝራለች። 
የጀርመን ፖለቲከኞች ለምርጫ መከራከርያነት ይዘዋቸው ከቀረቡ ዋና ዋና ጭብጦች ውስጥ እስካሁን ድረስ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደሩ ባለው ጉዳት ላይ አተኩሯል። ይህ ማለት በአውሮጳ ኅብረት መጻዔ ጊዜ ላይ እምብዛም ትኩረት አልተደረገም ማለት ነው የምትለው ሚሚ፤ ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ጀርመን አፍሪቃን በተመለከተ የምታራምደው ፖሊሲን በተመለከተ መራጮችም ሆኑ አዲሱ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች ውስጥ አይካተቱም በማለት ስጋቷን ትገልጣለች።
እንደ ሚሚ ሐሳብ፦ ጀርመን ዓለማቀፍ ግንኙነቶችን ችላ የማለት አቅም አይኖራትም። ምክንያቱም አጽናፋዊ ትስስር ወይንም በግሎባላይዜሽን ውስጥ የሀገራት ኢኮኖሚ በሚኖራቸው ዓለማቀፍ የግንኙነት ሁኔታ ላይ ይመሰረታል። 
ጋዜጠኛዋ የጀርመን ምርጫ በስደት እና በኢኮኖሚ ላይ ግልፅ ትኩረት ማድረጉን በተመለከተ ባነሳችው ሃሳብ አውሮጳ በስደተኞች ጎርፍ ከተጥለቀለቀችበት የጎርጎርሳውያኑ 2015 በፊት ጀርመን በዓለማቀፍ ጉዳዮች ላይ እምብዛም ከፊት አትታይም ነበር። ነገር ግን  አፍሪቃውያን እና እስያውያን ፍልሰተኞች ወደ አውሮጳ በተለያዩ መንገዶች በመግባት ጥገኝነት መጠየቅ ሲጀምሩ ሁኔታዎችም በዚያው ልክ እየተቀየሩ መኼዳቸውን በአንክሮ ትገልጣለች።  
ጋዜጠኛዋ አያይዛ፦ አዲሱ የጀርመን መንግሥት ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል የምላቸው ሁለት መስኮች አሉ ትላለች።  እነርሱም ኢኮኖሚ እና ፍልሰት ናቸው። ኢኮኖሚ ሲባል የጀርመንን የራሷን ኢኮኖሚ ለማለት ሳይሆን በዓለም ላይ ለድህነት ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው የምትለው። 
በቅርቡ በርሊን ላይ ተደርጎ በነበረው የጀርመን አፍሪቃ ጉባኤ መራኂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከአፍሪቃ ጋር ሊኖር ስለሚገባው ጥብቅ ግንኙነት አድርገውት  የነበረው ተስፋ ሰጭ ንግግር እጅጉን መስጧት እንደ ነበር ሚሚ ገልጣለች። 
ነገር ግን ከዚያ በኋላ በነበሩ የተወዳዳሪ ፖለቲከኞች የምርጫ ንግግሮች የመራኂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን ተስፋ የሚያስቀጥሉ ምልክቶች አልታዩም ባይ ናት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጀርመን በአፍሪቃ የምታደርገው ኢንቨስትመንት እየጨመረ ቢመጣም መራኂተ መንግስቷን ለመተካት የሚወዳደሩት  ፖለቲከኞች የእርሳቸውን ፈለግ ስለማስቀጠላቸው ምልክት አላሳዩም ስትልም ትሞግታለች። እናም ምናልባት የአንጌላ ሜርኪል የስልጣን ዘመን ማብቃት ወደ አፍሪቃ ይሄድ የነበረው ኢንቨስትመንት ፍሰት ለመቀዛቀዙ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይታየኛል ስትልም ስጋቷን አክላለች። 
በሌላ በኩል ከጸጥታ እና የደሕንነት ስጋቶች አንጻር ግን ነገሮች ሌላ መልክ ሊኖራቸው እንደሚችል  ጋዜጠኛዋ ታነሳለች። አፍጋኒስታን ውስጥ የታሊባን መልሶ በትረስልጣኑን መቆጣጠር ፤ በኢትዮጵያ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ እየተደረገ ያለው ጦርነት፣ በካሜሩን እና በምስራቅ ናይጄሪያ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ክልሎች ለነጻነት የሚያደርጉት ፍልሚያ ፤ በአጠቃላይ በአፍሪቃ ወታደራዊ ኃይሎች መንግሥታዊ ሥልጣን እየተቆጣጠሩ መምጣታቸው አውሮጳ በጎርጎርሳያኑ 2015 ከገጠማት በባሰ ሁኔታ በፍልሰተኞች ጎርፍ ዳግም ልትጥለቀለቅ እንደምትችል ስጋቷን አስፍራለች።
በመሆኑም ትላለች ጋዜጠኛዋ መጪው የጀርመን መንግሥት አፍሪካን ቀዳሚ ሊያደርጋት እንደሚችል ጥቂት ተስፋ በመሰነቅ  የጀርመን ሰላምና ብልጽግና ከሌሎች አንጻር እየተቃኘ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ አካሄድ መውሰድ አለበት። ስትል የምትመክረው ሚሚ ለአፍሪካ ቅድሚያ መስጠት ለአዲሱ ማራሄ ወይም መራሒተ መንግስት የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል፤  ብላለች ። የአህጉሪቱን ችግሮች ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ለጀርመን ኢኮኖሚም የሚኖረውን አዎንታዊ ሚና የገለጠችበትን ሃሳቧን ቋጭታለች።  
 

ARD Schlussrunde I Wahlen 2021 I Armin Laschet
ምስል Clemens Bilan/Pool/Getty Images
Schweden | European Intervention Initiative Treffen in Stockholm
ምስል Claudio Bresciani/TT/picture alliance
Symbolbild Abschied der Bundeskanzlerin Angela Merkel
ምስል Sean Gallup/Getty Images