1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን የጋራንግን ምትክ የሚጠብቅ ፈተና

ሰኞ፣ ነሐሴ 16 1997

ለረጅም ዓመታት የደቡብ ሱዳን ነፃአዉጪ ንቅናቄ /SPLM/ቡድን መሪ ጆን ጋራንግ ህይወታቸዉ በአደጋ ካለፈዉ ወዲህ በአገሪቱ ይፈጠራል ተብሎ የታሰበዉ ሰላም እንደተፈራዉ ባይናጋም ስጋት አልተለየዉም። የጋራንግ ሄሊኮፕተር አደጋ የተከሰተዉ የሱዳንን ምክትል ፕሬዝደንትነት ስልጣን ተረክበዉ ቃላ መሃላ በፈፀሙ በሶስተኛዉ ሳምንት እንደነበር ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/E0jZ

ስልጣናቸዉም በሰላም ስምምነቱ መሰረት ወደደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንትነት የሚያድግ ነበር። የእሳቸዉ ሞት ከተሰማ ከሰዓታት በኋላም የሱዳን መንግስትና የተባበሩት መንግስታት በጋራ የሞታቸዉ ምክንያት አደጋ መሆኑን ደጋግመዉ ተናግረዋል ህዝቡ ባይቀበለዉም። በምትካቸዉ የተሾሙት ከጦር ስልት በቀር በፓለቲካዉ እጅግም የሆኑት ሳልቫ ኪር ከጋራንግ ጋር የሚለያይ አቋም ነበራቸዉ። ጋራንግ የአንድነት ኪር የመገንጠል ሃሳብ አራማጆች። አሁን ግን ኪር ሌላ ገፅ ይዘዉ ታይተዋል።
ከጋራንግ ስርዓተ ቀብር በኋላ በሱዳን የተፈራዉ ግጭትና ዉጥረት ረገብ ማለቱ ነዉ የሚነገረዉ። በSPLM ዉስጥ የጋራንግ ምክትል የነበሩት ሳልቫ ኪርም በእግራቸዉ እንዲተኩ ወዲያዉ ነበር በሙሉ ድምፅ የተመረጡት ።
በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ቁጥር ካለዉ ዲንካ ከተሰኘዉ ከጋራንግ ጎሳ የተገኙት ኪር ታዋቂ የጦር መሪ ከመሆናቸዉ ዉጪ የፓለቲካ ግንዛቤያቸዉ አይታወቁም።
ዩናይትድ ስቴትስ ከተማሩት ጋራንግ ጋር ሲነፃፀሩም ካላቸዉ ወታደራዊ ዝና ሌላ በፓለቲካ ተሳትፎ የሌላቸዉ ጭምት አልክሆል የማይጠጡና ሲጋራም የማያጨሱ ናቸዉ ኪር።
የዩናይትስ ስቴትስ ልዑክ የሆኑት ሮጀር ዊንተር እንደሚሉት በቡድኑ ዉስጥ ተወዳጅነት አላቸዉ በሚሏቸዉ ኪር ላይ ከፍተኛ እምነት ጥለዋል።
በእርግጥ አሉ ዊንተር ኪር የጦር መሪነቱ ላይ ቢበረቱም በፓለቲካዉም ቢሆን የማይገባቸዉ የሚባሉ አይደሉም እንደዉም በጦሩ ዉስጥ በአቀራረባቸዉ በሁሉም ዘንድ ጥሩ ስም አትርፈዋል።
አያይዘዉም ምናልባት ኪር በፓለቲካዉ ዘርፍ ድጋፍ ቢያሻቸዉ ከእሳቸዉ የስራ አጋሮች ያንን ማግኘት እንደሚችሉ ነዉ የተናገሩት።
በጁባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የልማት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቤዴንጎ አኮ ካቹል ደግሞ ክፍተት ይኖራል የሚል ስጋት አላቸዉ።
ጆን አሉ በዲፕሎማሲዉ፤ በፓለቲካዉም ሆነ በአካዳሚዉ ዘርፍ ባላቸዉ እዉቀትና ልምድ ከኪር ይልቃሉ።
በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ያለዉ የእዉቀት ልዩነት ሰፊ ነዉ ግን ደግሞ ኪር በሰላም ስምምነቱ መሰረት ሊመሩ ይችላሉ ሲሉ ይገልፃሉ።
ከሁሉም በላይ ግን ከኑኤር ጎሳ የወጡት ሪክ ማቻር የኪርን ቦታ እንዲይዙ መደረጉ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ተከስቶ ባጠቃላይ በSPLM ዉስጥ ይፈጠር የነበዉን መከፋፈል አስቀርቷል የሚል እምነት አላቸዉ።
በሱዳን በተደረሰዉ የሰላም ስምምነት መሰረት ከሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት በኋላ ደቡብ ሱዳናዉያን የአንድነት ወይም የመገንጠል ዉሳኔያቸዉን በይፋ ማሳወቅ ይችላሉ።
በአጋጣሚ ግን የኪር የቆየ የመገንጠል አቋም ተለዉጦ የጋራንግን አንድ ሱዳን የሚል የፓለቲካ አጀንዳ ይዘዉ ብቅ ብለዋል።
ኪር በጋራንግ ቦታ የምክትል ፕሬዝደንትነት ስልጣን ለመረከብ ቃለመሃላ በፈፀሙበት ዕለት ስለሱዳን አንድነት የሚታገሉበት የመጨረሻ እድል መሆኑን ቢናገሩም ይህን እንቆቅልሽ ለወደፊት እንዴት እንደሚፈቱት ግልፅ አልሆነም።
ጋራንግ ከመሞታቸዉ አስቀድሞም በበሱዳን የተደረሰዉን የሰላም ስምምነት ሌሎች በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ቡድኖችን ያላከተተ በSPLMና በካርቱም መንግስት መካከል ብቻ የተደረሰ ስምምነት ነዉ በሚል ክፉኛ ተተችቷል።
በሰሜን ሱዳን የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የሱዳን ነፃአዉጪ ንቅናቄና የፍትህና እኩልነት ንቅናቄ እንዲሁም በዳርፉር በስፋት የሚንቀሳቀሱ አማፅያን፤ በዚያም ላይ ቁጥራቸዉ ቢያንስም የቤጃ ኮንግረስ የተሰኙት ቡድኖችና ሌሎችም ሁሉ አልተካተንንም የሚል ቅሬታ አላቸዉ።
ስምምነቱን አስመስልክቶ የተደረገዉ ጥናት እንደጠቆመዉ በአገሪቱ በሚመሰረተዉ ብሄራዊ መንግስት ከፍተኛዉን የስልጣን ቦታ የሚጋሩት SPLMና የፕሬዝደንት ዖማር አልበሽር ፓርቲ የሆነዉ ብሄራዊ ኮንግረስ በምህፃረ ቃሉ NCP ብቻ ናቸዉ።
በዚህ መሰረትም ከአገሪቱ ምክር ቤት 52በመቶ የሚሆነዉ መቀመጫ በNCP፤ 28በመቶዉ በSPLM የሚያዝ ሲሆን ሌሎች ፓርቲዎች ቀሪዉን 20በመቶ የሚሆን ድርሻ ነዉ የሚጋሩት። ይህም በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚዎችን ቁጣና ቅሬታ ቀስቅሷል።
በዚያም ላይ በአገሪቱ ዉስጥ ስልጣንና ጥቅምን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ግጭት በዘርና ጎሳ መካከል በቀላሉ ሲቀጣጠል የኖረበት ሁኔታ ነዉ የሚነገረዉ።
በተጨማሪም የሰሜኑ ሙስሊም መንግስት ከእስራኤል መንግስት ጋር የመስራትን ነገር አልቀበልም ሲል ክርስቲያኖች የሚበረክቱበት የደቡብ ሱዳን ደግሞ አብሮ የመስራት ፍላጎቱ አሳይቷል። ሌላ ልዩነት።
ከሁሉም በላይ በዳርፉር ያለዉን ቀዉስ ለመፍታት የሚታመን ጥረት የሞከሩት ጋራንግ ብቻ መሆናቸዉ ነዉ የሚነገረዉ።
ፕሬዝደንት አልበሽር ይህን ጥረት ማድረግ መጀመራቸዉን ከገለፁ በርካታ ወራት ቢቆጠሩም በበዓላት ላይ ከሚቀርብ ንግግር አልዘለለም በሚል እየተተቹ ነዉ።
በዚህ አጋጣሚ ኪር ብዙ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ግምት አለ ምክንያቱም ጆን ጋራንግን በጠላትነት ይመለከቱ የነበሩ ሁሉ ከእሳቸዉ ጋር ለመስራት ፈቃደኝነት አሳይተዋል።
አዲሱ ምክትል ፕሬዝደንት ኪርም ነገሮች በተሳከሩባት ሱዳን አመጣለሁ ብለዉ የተመኟት አዲሷ የአንዲት ሱዳን ጉዳይ መፈተኛቸዉ እንደምትሆን ከወዲሁ እየተነበዩ።