1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን ፕሬዚደንት ላይ የተላለፈው የእስር ማዘዣ

ረቡዕ፣ የካቲት 25 2001

በዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አል በሺር ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ የቀረበለትን ማመልከቻ በመቀበል ዛሬ የእስር ማዘዣ አወጣ።

https://p.dw.com/p/H5cP
ምስል AP

እንደሚታወሰው፡ የፍርድ ቤቱ ዋና ዓቃቤ ህግ ልዊ ሞሬኖ ኦካምፖ በዳርፉር ለተካሄደ የጎሳ ጭፍጨፋና በስብዕና አንጻር ለተፈጸመው ወንጀል ፕሬዚደንት በሺር ተጠያቂ ናቸው በሚል በአንጻራቸው የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ባለፈው ሀምሌ ወር ነበር ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ ያስገቡት። ይኸው የሱዳኑ ፕሬዚደንት እንዲታሰሩ የሚያዘውን ውሳኔ ያሳለፈበት ድርጊት ምን ሊያስከትል ይችላል?

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በዚሁ ግዛት በቀጠለው ጥቃት ላይ የሱዳን አየር ኃይል ባካባቢው ሲቭል ህዝብ አንጻር ጥቃት እንደሚያካሂድ አንድ ያይን ምስክር በዚሁ የቦምብ ድብደባው አንድ መንደር ሲያቃጥል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ስዕልን እንደመረጃ በማቅረብ አስታውቋል። በምዕራብ ዳርፉር በሚገኘው የካሞይ መንደር በተዋጊ አይሮፕላኖች መደብደቡንም አክሎ አስረድቶዋል።

ይህን የመሰለው እና ጥቃትም ነው ባለፈው ሀምሌ የዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ አርጀንቲንያዊው ልዊ ሞሬኖ ኦካምፖን በፕሬዚደንት በሺር ላይ በስብዕና አንጻር እና በጦር ወንጀል ተከሰው እንዲታሰሩ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ምክንያት የሆናቸው።

በሱዳን የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፡ ዲፕሎማቶች እና ታዛቢዎች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በስጋት ነበር የጠበቁት። በሱዳን በመዲናይቱ ካርቱም ዩኒቨርሲቱ የሰላምና ምርምር ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት የፕሬዚደንት በሺር የቅርብ አማካሪና በመንግስትና በዳርፉር ዓማጽያን መካከል የሚሸመግሉት ኤል ጣይብ እንደሚሉት፡ ፍርድ ቤቱ የዋና ዓቃቤ ህጉን ማመልከቻ ተቀብሎ ዛሬ ያስተላለፈው የእስር ማዘዣ አሳሳቢ መዘዝ ሊኖረው ይችላል።

« በኋላ ምን ሊፈጠር ይችላል? ችግሩ ያኔ ነው የሚጀመረው። የሱዳን መንግስት ክሱ ለመቀበል ካልፈለገ፡ ያኔ የተመ ጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ምናልባት በሱዳን ላይ ማዕቀብ ሊጥል ይችላል። ማዕቀቡ የሱዳን መንግስት ስራን ሊያሰናክልና የመላይቱን ሀገር መረጋጋት ሊያደፈርስ ይችል ይሆናል። ይህም በሱዳን ግጭቱ እንዲባባስ ሊያደርግና በሰሜንና በደቡብ ሱዳን፡ እንዲሁም፡ በዳርፉር የሰላም ሂደትም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል። »

ጀርመናዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ክርስቲያን ቶሙሻት ግን ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣው ተግባራዊ መሆኑን ይጠራጠሩታል።

« የእስር ማዘዣውን ትክክለኝነት አልጠራጠረውም። ጥያቄው ማዘዣውን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ነው? ከወጣስ ሰላም ለማስገኘት ያስችላል ወይ? ወይስ የእስር ማዘዣውን በኃይሉ ተግባራዊ ለማስደረግ በሚሞከርበት ሁኔታ ሁከት ይከተላል? ውሳኔውን በኃይሉ ተግባራዊ ማድረጉ የማይታሰብ ነው። ምክንያቱም ማን ነው ወደ ካርቱም በመሄድ አቶ በሺርን የሚያስር? ይህን ለማድረግ ዝግጁ የሚሆን ሰው አይኖርም። አንድ ግለሰብ ለማሰር ብለን ጦርነት የሚጀመርበትን ሁኔታ ልንፈጥር አንችልም »።

የሱዳን መንግስት የእስር ማዘዣውን ምክንያት በማድረግ የበቀል ርምጃ ወስዶ በሲብሉ ህዝብ፡ በርዳታ ሰራተኞች ወይም በዳርፉር በተሰማራው የተ እና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዳይጥል ዲፕሎማቶች ሰግተዋል።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በአንድ በስልጣን ላይ ባለ የሀገር መሪ ላይ እስራት ሲያዝ ፕሬዚደንት በሺር የመጀመሪያው ናቸው።

ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ባንድ በኩል የጦር ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ይፈልጋል፤ በሌላ በኩል ግን፡ ወንጀለኞች የሚላቸው ግለሰቦች የድርድር ተጓዳኞቹ ናቸው። እና ይህ ነው ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት አጣብቂኝ ሁኔታ ላይ የጣለው። ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አል በሺር እንዲታሰሩ የተላለፈውን ውሳኔ ይቃወሙታል። ዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት እአአ በ 2002 ዓም የተቋቋመበትን ውል አንድ መቶ ስምንት የዓለም ሀገሮች ቢያጸድቁትም፡ ሱዳን፡ ዩኤስ አሜሪካ፡ እስራኤልና ሊብያ አሁንም የፍርድ ቤቱን ስልጣን አልተቀበሉትም።

Stefanie Duckstein/Aryam Abraha/ZPR

Tekle Yewhala