1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የተሳተፉ ወጣቶች

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2012

ዕሮብ ዕለት በተካሄደው የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ላይ የተሳተፉ አብዛኛቹ ወጣቶች እንደገለፁልን ምርጫው ነፃ እና ገለልተኛ ነበር። በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ላይስ ወጣቶቹ ምን አይነት ተስፋ አላቸው?

https://p.dw.com/p/3TWqP
Äthiopien: Sidama stimmen über Autonomie ab
ምስል AFP/M. Tewelde

በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የተሳተፉ ወጣቶች

ዕሮብ ኅዳር 10 ቀን፣ 2012 ዓም በተካሄደው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ላይ በርካታ ወጣቶች ለመምረጥ ጎዳናዎች ላይ ተሰልፈው ታይተዋል። ምንም እንኳን ድምፅ መስጠት የተጀመረው ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ቢሆንም የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ብርሃኑ እንደገለፀልን ሰው ድምፅ ለመስጠት ወረፋ መያዝ የጀመረው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አንስቶ ነው።  « ወረፋ ይኖራል ብዬ ሰግቼ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው ከቤት የወጣሁት እዛ ስደርስ ብዙ ሰው ነው ተሰልፎ ያገኘሁት። ምንም ችግር በሌለበት በሰላማዊ ሁኔታ ነው    ምርጫው የተከናወነው።» ይላል ብርሃኑ።

ከሲዳማ ዞን ወንዶ ገነት ወረዳ ድምጿን የሰጠችው ወጣት እምነትም ምርጫው ሰላማዊ ብቻ ሳይሆን ድልም የሚያቀዳጀን ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብላናለች። በምርጫ ስትሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው።  « እንደጠበኩት እና እንደሰጋኹት ሳይሆን በሰላም እና በፍትኃዊ ሁኔታ ነው የተካሄደው። » ትላለች። የሲዳማ ሕዝብ በክልል እንዲደራጅ ድምፅ ለመስጠት ቀኑን እንደ እምነት በጉጉት ስትጠባበቅ የነበረችው ሌላዋ መራጭ አልማዝ ትባላለች። « አስር ሰዓት ተኩል ላይ ነው ከቤት የወጣነው። ድባቡ ከጠበቅነው በላይ ነበር። »

Äthiopien Sidama stimmen über Autonomie ab
ምስል AFP/M. Tewelde

ብንመርጥም ባንመርጥም ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ ነበር የሚለው ሌላው ወጣት ደግሞ ፍቃዱ ነው።  የምርጫ ሒደቱ ከመጀመሪያውም ጫና ነበረበት  « ምንም ነፃ ምርጫ ነው የሚያስብል ነገር የለም።» ይላል። ከዚህ በፊት በሀገራዊ ምርጫ ተካፍሎ የሚያውቀው ፍቃዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ አሠራር አሁንም ብዙ እንደሚቀረው ነው የሚናገረው። መጪውም ሀገር አቀፍ ምርጫ ቢዘገይ ይመርጣል። « በፊትም የነበሩ ምርጫዎች ፍትኃዊ አልነበሩም አሁንም ያለው ምርጫ ፍትኃዊ አይደለም። ችግሩ ከምዝገባ ጀምሮ የነበረው እና ቅስቀሳው ላይ ነው።  ምርጫውን ከጥቅማ ጥቅም ጋር የማያያዝ ነገር አለ። አልመረጣችሁ አትኖሩም አይነት» ነው የሚለው።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዱን ግን አፈፃፀሙ «ፍፁም እና ምሉእ» እንዳልነበር፣ ወደፊትም «መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንደሚኖሩ» ተናግረዋል። ለሀዋሳ ነዋሪው ብርሃኑ ምርጫው ከፍተኛ መሻሻል የተደረገበት ነፃ እና ገለልተኛ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለውም ምርጫ ቦርዱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ስለተወጣ ነው ይላል። « አስፈላጊ ነገሮችን አሟልቶ፣ ሰራተኛ አሰልጥኖ አሰማርቶ ነበር። ምርጫ ቦርዱ እስከ መጨረሻ ድረስ ያደረገው ጥረት በቀጣይ ምርጫ አካሄድ ላይ ተዓማኒነት እንዲኖረው የራሱን ድርሻ ተወጥቷል።»

Äthiopien Yirgalem Sidama Referendum
ምስል DW/S. Wegayehu

በዚህ ህዝበ ውሳኔ ላይ በርካታ ሴቶች ድምፃቸውን ለመስጠት ተሰልፈው ታይተዋል። ወጣት እምነት ራሳቸውን ከምርጫ እና ከፖለቲካ የሚያገሉት ሴቶች ከቤት እመቤትነት ሌላ አብሮ የመወሰን መብት እንዳላቸውና በዚህ ምርጫ እንዲሳተፉ ብዙ የማሳመን ስራ እኛ ወጣቶች ሰርተናል ትላለች። « በእኛ ጥረት የተነሳ ቅድም አያቶቻችን ራሱ ውጪ ለመውጣት በቅተዋል። እኛ እንዲህ ነው ብለን ባሳመናቸው እኛን ደግፈው ወጥተዋል።» በአጠቃላይ በወጣቱ ዘንድ የነበረውን የሕዝበ ውሳኔ ተሳትፎ የሚያደንቀው ብርሃኑ ይህ ለመጪው ምርጫም ትምህርት የሚሆን ነው ይላል። « ከአዋቂዎች በላይ ወጣቶች የራሱ ሚና ተወጥቷል።»

 

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ