1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሲዳማ ሶስት አካባቢዎች 34 ሰዎች መሞታቸውን እማኞች እና ሲአን ገለጹ

እሑድ፣ ሐምሌ 14 2011

በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ሶስት አካባቢዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 34 መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ተቃዋሚው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ገለጹ። አንድ የዓይን እማኝ በሁላ ወረዳ ሀገረ ሰላም ከተማ 14 ሰዎች ሲገደሉ መመልከታቸውን ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/3MTZN
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሁላ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ከትላንት በስቲያ አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ወደ ፌደራል ፖሊሶች የሄዱ የከተማይቱ ነዋሪዎች ተኩስ ተከፍቶባቸዋል። በጥይት የተመቱት አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን የተናገሩት የዓይን እማኙ ወዲያውኑ ወደ ሁላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ቢወሰዱም አስራ አራቱ ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።  

“ከትላንት ወዲያ እዚህ ሆስፒታል አስገብተው ያወጧቸውን ወደ 14 ሰዎች ነው ያየሁት። ያው እነርሱ የሞቱት በፌደራል ፖሊስ ነው። ግጭት አልነበረም። ህዝቡ ለመጠየቅ ወደ እነርሱ ሲሄድ ወደ ህዝቡ ተኮሱ። በዚያ ሰዓት በመትረየስ ሲመቱ አስሩ በአንድ ጊዜ ወደቀ። ከዚያም [ሌሎችም] ወደቁ። አንዳንዶቹ ቆሰሉ። ወደ 14 የሆኑት ሞቱ” ብለዋል የዓይን እማኙ። 

የፌደራል ፖሊስ አባላት ሐሙስ ምሽት ወደ ሀገረሰላም መግባታቸውን የሚናገሩት ነዋሪው በነጋታው አንድ ወጣት ልጅ መገደሉን ተከትሎ ነዋሪዎች ለጥያቄ መሄዳቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። በከተማይቱ ፖሊስ ጣቢያ ሰፍረው የነበሩት ፖሊሶች ነዋሪውን ሲመለከቱ መተኮሳቸውን ገልጸዋል። 

“በዚህ የሆኑ ልጆች ሞተው ʻእኛ ሰላማዊ ነን። የጠየቅነው ጥያቄ አልተመለሰም። እኛ የፈለግነው ክልሉ ባለፈው የተጠየቀው እርሱ አልተመለሰም። እኛ ውጊያ አልፈልግንም። እናንተ በእኛ ላይ ለምንድነው የምትተኩሱትʼ እያሉ ለመጠየቅ ሲሄዱ ነው። ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ነበር። ባጃጆች የሚቆሙበት አለ። እነርሱም የቆሙበት እዚያ ነበረ። እዚያ ሆነው ሲተኩሱ እኔ እዚህ ዳር ላይ ስለሆንኩ ይታያል” ሲሉ አብራርተዋል። 

በሁላ የሞቱ ሰዎች የቀብር ስነ ስርዓት ትላንት እና ዛሬ መፈጸሙን የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል። በሀገረ ሰላም ዛሬ የተረጋጋ ሁኔታ እንደሚስተዋል እና በአካባቢው አሁንም የፌደራል ፖሊሶች እንዳሉ ጠቁመዋል። በአርቡ ተኩስ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ተለያዩ ቦታ መወሰዳቸውን የሚገልጹት የዓይን እማኙ ትክክለኛ ቁጥራቸውን ግን አላውቅም ብለዋል።

Äthiopien Stadtansicht Awassa
ምስል DW/S. Wegayehu

ዶይቼ ቬለ የሀገረ ሰላም ከተማ ባለሥልጣናትን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ዋና ጸሀፊ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ግን በሁላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እስካሁን ከሲዳማ ዞን ሶስት የተለያዩ አካባቢዎች ባሰባሰቡት መረጃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 34 መድረሱንም ገልጸዋል። 

“በሀገረ ሰላም ወይም በሁላ ወረዳ እስከ 18 ሞተዋል። በመልጋ 12 ሞተው ብዙዎች ቆስለዋል። የሞቱትን በትክክል አውቀናል፤ የቆሰሉትን ቁጥር በትክክል ማወቅ አልቻልንም። በሀዋሳ ላይ አራት ሰዎች እንደሞቱ ከተማ አስተዳደሩ ራሱ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው የተናገሩትን ነው። ሰባት ቆስለዋል፤ አራት ሞተዋል።  በአጠቃላይ ከ26 እስከ 30 ድረስ ይነገራል። በትክክል ግን ስናውቅ ነው አጠቃላይ መግለጫ የምንሰጠው።” ያሉት አቶ ለገሰ «ይርጋለም እና ለኩ፣ አለታ ወንዶ የሞቱትን አላገኘንም” ሲሉ አክለዋል። 

የደቡብ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ በዛሬው ምሽት ስርጭቱ በአለታ ወንዶ፣ አለታ ጩኮ እና ሀገረ ሰላም የደረሱ የንብረት ውድመቶችን አሳይቷል። ጣቢያው የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዊቻ እና የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ሶስቱን ከተማዎች ተዘዋውረው ሲመለከቱ በምስል አስደግፎ ለዕይታ አብቅቷል። 

ጉዳት የደረሰባቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች እምባ እየተናነቃቸው የደረሰባቸውን ጉዳት ለባለስልጣናቱ ዘርዝረዋል። በቴሌቪዥን ጣቢያው የተቃጠሉ ፋብሪካዎች፣ ቤቶች እና መኪናዎች የታዩ ሲሆን የክልሉ ባለስልጣናትም የባለንብረቶቹን ባለቤቶች ሲያነጋግሩ እና ሲያጽናኑ ተደምጠዋል። የክልሉ መገናኛ ብዙሃን በተለያዩ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ቢጠቅስም ቁጥራቸውን ሳይገልጽ አልፏል።

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ