1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሊያ የተቀሰቀሰው ውጊያ

ሰኞ፣ የካቲት 14 2003

የሶማሊያ መዲና መቅዲሾ የሳምንቱን የዕረፍት ቀናት ቅዳሜና ዕሁድን በጦርነት አሳልፋለች። ዛሬ ጠዋትም በአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ስትናጥ አርፍዳለች።

https://p.dw.com/p/R2p7
ምስል AP

ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ የአፍሪካ ህብረት ሰራዊትና አሸባብ ከባድ ውጊያ አድርገዋል። በውጊያው ሁለቱም ወገኖች ድል እንዳደረጉ ይገልጻሉ። የአሸባብ ጠንካራ ምሽግን ደርሼበት አጥቅቼዋለሁ፤ 6 የሌሎች ሀገራት ዜጎች የሆኑ ሽብርተኞችን ገድያለሁ በማለት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል መግለጪያ ሰጥቷል። አሸባብ በበኩሉ ወራሪው የክርስቲያን ጦር ሊያጠቃኝ ሞክሮ ከባድ ጉዳት አድርሼበት ወደመጣበት ተመልሷል ሲል ገልጿል። በሁለቱ ቀናት ውጊያዎች 15 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ዛሬ በተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት 12 ሰላማዊ ሰው ህይወቱን አጥቷል። መሳይ መኮንን ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሀጂ አብዲኑርን በማነጋገር ተከታዩን ዘገባ አሰናድቷል።

ውጊያው በእርግጥ የተለመደ ነው። ዛሬ የተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃትም እንደዚያው። ጋብ ብሎ የከረመው የሶማሊያ ግጭት እንደአዲስ ተቀስቅሷል። የሳምንቱን የዕረፍት ቀናት በከባድ ውጊያ ዛሬን ድግሞ በቦምብ ጥቃት ስትታመስ ሰነብታለች።  እንደ ልማድዋ አሸባብና የአፍሪካ ህብረት ሰራዊት ሲፋተጉባት ፤ ሰላማዊ ሰው ሲገደሉባት ሁለቱም ወገኖች የድል ምግለጪያ ሲያሰሙባት ነው ያለፉትን ሶስት ቀናት የቆየችው-መቅዲሾ። የሰሞንኛው ውጊያ መነሻው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በመቅዲሾ መሃል አንድ ጠንካራ የአሸባብ ምሽግ አገኘሁ ብሎ ባጠቃ ጊዜ እንደሆነ ዘገባዎች አመላክተዋል። የአጃንስ ፍራንስ ፕሬሱ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሃጂ አብዲኑር ስለሰሞኑ የመቅዲሾ ውጊያ ሲገልጽ

«ይህ ውጊያ የተጀመረው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት አሸባብ ወደተቆጣጠራቸው በርካታ አከባቢዎች በሚገሰግስበት ጊዜ ነው። በእርግጥ ግስጋሴው ይህን ያህል የተጠናከረ አልነበረም። ሆኖም ወደ አሸባብ ይዞታ ሲመሩ ከታጣቂዎች ብርቱ መከላከል ገጠማቸው። ታጣቂዎቹ ከይዞታቸው ሆነው የተቃጣባቸውን ጥቃት ለመከላከል ሲሞክሩ ነበር። እናም ጦርነቱ ላለፉት ሶስት ቀናት ቀጥሎ ነበር።»

Somalia Kämpfe in Mogadishu AU Panzer
ምስል AP

የሰሞኑ የሶማሊያ ግርግር የ27 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። 15ቱ በቅዳሜና ዕሁዱ ውጊያ ሲገደሉ፤ 12ቱ ደግሞ ዛሬ ጠዋት መቅዲሾ በሚገኝ አንድ የፖሊስ ማሰልጠኛ አጠገብ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ህይወታቸውን አጥተዋል። ያለፉት ቀናት ውጊያ በተለይ መሃል መቅዲሾ ባሉት የሆዳንና ሆልዋዳግ መንደሮች የተደረገ ነበር። የአሸባብ ምሽግ እንዳለ መረጃ ደረሰኝ ያለው የአፍሪካ ህብረት ስራዊት በወሰደው የማጥቃት እርምጃ 6 የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ወታደራዊ አዛዦችን መግደሉን አስታውቋል። የህብረቱ ሁለት ወታደሮች በውጊያው እንደተገደሉም የሆስፒታልና የደህንነት ምንጮች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።

«የሆስፒታል ምንጮችና የዓይን እማኞች እንደገለጹት አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ 18 ሰዎች በውጊያው ተገድለዋል። በአፍሪካ ህብረት ሰራዊትና በአሸባብ በኩልም ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአፍሪካ ህብረት ሰራዊት ሃላፊዎች እንደገለጹት ከተለያዩ ሀገራት ማለትም ከየመን ከፓኪስታን ከኬንያና ከሌሎችም የመጡ ስድስት ታጣቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰርጎ ገቦችን በውጊያው ተገድለዋል። የህብረቱ ሁለት ወታደሮችም እንደሞተባቸው ሃላፊዎቹ ተናግረዋል።»

ሁለቱም ወገኖች በለስ እንደቀናቸው እየገለጹ ነው። የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊትና የሽግግሩ መንግስት ጦር ጠንካራውን የአሸባብ ምሽግ ደምስሰናል ሲሉ አሸባብ በበኩሉ መክቼዋለሁ። ምሽጉንም አልተነጠኩም ብሏል። የአሸባብ ቃል አቀባይ ሼክ አብዱላሲስ አቡ ሙሳብ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ወራሪው የክርስቲያን ጦር ክፉኛ ተመቶ ተመልሷል።

በሁለቱ ሃይሎች ውጊያ ቅዳሜና ዕሁድን ስትናጥ የሰነበተችው መቅዲሾ ዛሬም በአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ታምሳለች። ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሀጂ አብዲ ኑር

«ዛሬም የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሟል። የሶማሊያን የፖሊስ ሃይል ዒላማ ያደረገው ይኸው ጥቃት የ11 ሰዎችን ህይወት ሲያጠፋ 35 የሚሆኑትን አቁስሏል። ከተገደሉትና ከቆሰሉት መሃል አብዛኞቹ ፖሊሶች ናቸው። በደቡባዊ መቅዲሾ በሚገኝ የፖሊስ ካምፕ በስልጠና ላይ ያሉ ምልምል ፖሊሶች ላይ ነው ከፍተኛው ጉዳት የደረሰው።»

የሶሞኑ ውጊያና የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ለጥቂት ሳምንታት እፎይ ብላ የሰነበተችውን መቅዲሾ ወደለመደባት ቀውስ ከተዋታል። ደካማውን የሽግግር መንግስት እየጠበቀው ያለው የአፍሪካ ህብረት ሰራዊት አሁንም ሶማሊያን ለማረጋጋት እንደተሳነው አለ።  

 መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ