1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶሪያ የ ተ መ ድ ታዛቢዎች መከልከላቸው

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2004

ሶሪያ ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ታዛቢዎች ማዕከላዊ ሶሪያ የሚገኙ መንደሮች እንዳይገቡ የሶሪያ ጦርና የአካባቢው ነዋሪዎች መከልከላቸው ተዘገበ ። የቡድኑ አባላት ወደ መንደሮቹ ለመግባት ሲሞክሩ እንደተተኮሰባቸው ተገልጿል ። ታዛቢዎቹ ማዝራትና

https://p.dw.com/p/15AJz
ምስል picture-alliance/dpa

ሶሪያ ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ታዛቢዎች ማዕከላዊ ሶሪያ የሚገኙ መንደሮች እንዳይገቡ የሶሪያ ጦርና የአካባቢው ነዋሪዎች መከልከላቸው ተዘገበ ። የቡድኑ አባላት ወደ መንደሮቹ ለመግባት ሲሞክሩ እንደተተኮሰባቸው ተገልጿል ። ታዛቢዎቹ ማዝራትና አል ኩቤር በሚባሉት መንደሮች በሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ታማኝ ሚሊሽያዎች ተፈፅሟል የተባለውን የ 78 ሰዎች ግድያ ለማጣራት ወደ ስፍራው ቢያቀኑም እስከ ዛሬ ከሰዓት ድረስ ወደ መንደሮቹ መግባት እንዳልቻሉ አንድ የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል ። ታዛቢዎቹ ወደ አልኩቤር ከገቡ ለደህንነታቸው አስጊ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ያስጠነቅቁ እንደነበር የታዛቢው ቡድን መሪ ሜጀር ጀነራል

Syrien UN Robert Mood
ሮበርት ሙድምስል Reuters

ሮበርት ሙድ ተናግረዋል ። የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች ሻቤሃ የሚባሉት የደማስቆ መንግሥት ደጋፊ ፈጥኖ ደራሽ ሚሊሽያዎች ሃማ ክፍለ ሃገር ውስጥ በሚገኙት በአል ኪቤርና በማዛራት መንደሮች ትናንት በቅርብ ርቀት ተኩሰው ሴቶችና ህፃናትን መግደላቸውን ከገደሉት ውስጥም የ12 ቱን አስከሬን ማቃጠላቸውን ተናግረዋል ። በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግምት ሃማ ውስጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 140 ደርሷል ከመካከላቸውም 50 ያህሉ ሴቶችና ህጻናት ናቸው ። ይህ ግን በሌላ ነፃ ምንጭ አልተረጋገጠም ።

Syrien UN Generalversammlung
ምስል dapd

የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶሪያ መንግሥት ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስድ እያሳሰቡ ነው ። ከተቃዋሚው ብሄራዊ ምክር ቤት ራድዋን ዝያድ
«የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ነገ ይነጋገራል ብለን እንጠብቃለን ።
የፀጥታው ምክር ቤት ለሲቪሎች ጥበቃ ማድረግን በሚመለከትው የውሳኔ አዋጅ አንቀጽ 7 እንደተደነገገው ጠንካራ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ የሚያደርግበት ብቸኛው መንገድ ነው ። ይህ ካልሆነ ግን የሶሪያ ህዝብ እለት በእለት ክጭፍጨፋና ከግድያ ስጋት ጋር ይኖራሉ ። »
የተባበሩት መንግሥታትና የአረብ ሊግ የሶሪያ ልዩ ልዑክ ኮፊ አናን ስለ ሶሪያ ሁኔታ ዛሬ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሰጡት ገለፃ ወደ ርስበርስ ጦርነት የምታመራውን ሶሪያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፋጣኝ እንዲታደግ ተማፅነዋል ። ። አዲሱ የሶሪያ ግድያ በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ተወግዟል ።