1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶስት የግል መፅሔቶች ላይ የተላለፈው ብይን እና ውግዘቱ

ሐሙስ፣ መስከረም 29 2007

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሶስት የግል መጽሄቶች ባለቤቶች ላይ በሌሉበት ውሳኔ ማሳለፉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ከአዲስ አበባ ዘግቧል። እንደዘገባዉ ፍርድ ቤቱ መጽሔቶቹ ሎሚ፤ አዲስ ጉዳይ እና ፋክት የተሰኙት ሲሆኑ ውሳኔው በአለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/1DSnp
Zeitungen Äthiopien
ምስል DW

ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳት፣ ሀሰተኛ ወሬዎችን በህትመት መልክ በማሰራጨትና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር' በሚል በኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር ከተከሰሱት አምስት መጽሄቶችና አንድ ጋዜጣ መካከል በሶስቱ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።መስከረም 27 ቀን 2007 .. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፋክት መፅሔት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፋጡማ ኑርዬ በሶስት ዓመት ከአስራ አንድ ወር፤ የሎሚ መፅሔት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ እና የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ በሶስት ዓመት ከሶስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።የሶስቱ አሳታሚዎች ንብረትም በመንግስት እጅ እንዲቆይ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያው ዘግቧል።

Logo Reporter Ohne Grenzen englisch

በሶስቱ የመፅሔት ሥራ አስኪያጆች ላይ በሌሉበት የተወሰነው ብይን ጉዳይ በቅርበት ሲከታተሉ ለነበሩት የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ሲፒጄ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ቶም ሮድስ እንግዳ አይደለም።

Tom Rhodes
ምስል Tom Rhodes

''እንደ አለመታደል ሆኖ ከረጅም ጊዜ በፊት የተነበይነው ነው አሁን የተፈጠረው። በዚህ አመት መጀመሪያ ሰባት መጽሄቶች ህዝብን የማነሳሳት ስራ ይሰራሉ የሚል አቋም የነበረው በመንግስት ድጋፍ የወጣ ጥናታዊ ጽሁፍ ነበር። መፅሔቶቹ ከተቃዋሚ ቡድኖቾ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚልም ይከሷቸዋል። ይህ የጥናት ወረቀት ይፋ ከሆነና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከዘገቡት በኃላ እነዚህ መፅሔቶች ችግር እንደሚገጥማቸው አውቀን ነበር። የእኔ ፍርሃት በሚቀጥለው አመት በሚካሄደው ምርጫ ምንም አይነት ነጻ ፕሬስ አይኖሩም የሚል ነው።''

የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችና ነጻውን ፕሬስ የሚያስተናግድበት መንገድ ..ጄን ከመሳሰሉ አለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ ሲሰነዘርበት ቆይቷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ያሉበትን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ቶም ሮድስ መንግስት ይህን እርምጃ ለምን እንደሚወስድ አላውቅም ሲሉ ይናገራሉ። እንደሳቸው አባባል ከሆነ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃን መጪው ጊዜ መልካም አይሆንም።

''ይህ ከምርጫው በፊት በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ አሸናፊነት ለማረጋገጥ የሚወሰድ እርምጃ ነው። እርምጃው ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሁል ጊዜም መንግስትን ከመደገፍ ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ለመጠቆም የተወሰደም ይመስላል። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የለም ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት ነጻ መጽሄትና ጋዜጣ ነጻ ሬዲዮና ቴሌቭዥን የለም። በእኔ ግምት በቅርቡ ከምርጫው በፊት የመረጃ ፍሰቱንና ውይይቱን ለመቆጣጠር በርካታ መንግስትን የሚደግፉና በመንግስት ድጎማ የሚንቀሳቀሱ መፅሔቶች ይመጣሉ። ይህ አስጊ ነው።''

የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ትችታቸውን እያቀረቡ ቢሆንም በሌሉበት የተፈረደባቸው የሶስቱ መጽሄቶች ስራ አስኪያጆች በፖሊስ ተፈልገው እንዲያዙና ቅጣቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የፌደራሉ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉንም ብሄራዊ ቴሌቭዥኑ ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ