1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሸንጎዉ ቀነ ገደብና የሰላም ድርድር በአፍሪቃ ቀንድ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 1999

የሶማሊያዉ እስላማዊ ሸንጎ ሶማሊያ ገብተዋል የሚላቸዉ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ካልወጡ ጥቃት እከፍታለሁ ያለበት ቀነ ገደብ እያለቀ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E0ha

በዚህ መካከል ስለወታደሮቹ መዉጣት ከገለልተኛ ወገንም ሆነ ከሚመለከታቸዉ የተሰማ ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የሽግግር መንግስቱና ሸንጎዉ ሱዳን ላይጀምረዉ አቋርጠዉት የነበረዉ የሰላም ስምምነት ዉይይት በየመን በኩል ተሞክሯል። የሸንጎዉ ቀነ ገደብም ሆነ ዉይይቱ የሚካሄድበት ዕለት ደግሞ ገጥሟል። የተሰጋዉ ግጭት ሳይቀሰቀስ መፍትሄ ይገኝ ይሆን? ናይሮቢ የሚገኙት በአፍሪቃ ቀንድ ዙሪያ ምርምር ያካሄዱት ማት ብራይደን ሁኔታዉን ሲያስረዱ።

በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ አደገኛና ያልተረጋጋ ሁኔታ አለ የሚሉት በአፍሪቃ ቀንድ ነባራዊ ሁኔታ ምርምር ያካሄዱት ማት ብራይደን በሶማሊያ ያለዉ ግጭት ወደ መሳሪያ ዉጊያ ተሸጋግሮ አጎራባች ሀገራትንም ሊያነካካ መቻሉን ያሰምሩበታል። በተለይ በጋራ ድንበራቸዉ ሳቢያ የሚወዛገቡት ኢትዮጵያና ኤርትራ ይህን አጋጣሚ እንደሌላ የፍጥጫ መድረክ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እስላማዊዉ ሸንጎ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ካላስወጣች አጠቃለሁ ይላል፤ ከኢትዮጵያም ወገን ለተሰነዘረዉ ማስተንቀቂያ ምላሽ ተሰጥቷል።

ብራይደን ይህን በሁለቱም አቅጣጫ የቃላት እንካ ሰላንቲያ ብቻ ነዉ ይሉታል። ሸንጎዉ በመሰረቱ ሶማሊያ ዉስጥ ያሉትን የኢትዮጵያ ወታደሮች ነዉ አጠቃለሁ ያለዉ። ኢትዮጵያን እወራለሁ አላለም። ኢትዮጵያም ያዉ በጣት የሚቆጠሩት አሰልጣኞች በቀር ሶማላያ ዉስጥ ወታደሮች የሉኝም ብላ አስተባብላለች። ብራይደን አያይዘዉም፤

«ሆኖም ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች አሁን በርካታ ሺ ወታደሮች ድንበር አልፈዉ ሶማሊያ ዉስጥ መኖራቸዉን ያምናሉ። ኢትዮጵያም አሉ የተባሉት ወታደሮች በሽግግር መንግስቱ ጥሪ የገቡ ናቸዉ ትላለች። እዚህ ጋ ነጥብ የሽግግር መንግስቱ ዉይይት እንዲካሄድ ከለላ ያስፈልገዋል ወይ ነዉ። ይህ ግን ምናልባት ሊሳካ የሚችለዉ አግባብ ባለዉ የተኩስ አቁም ስምምነትና የሽግግር መንግስቱን ደህንነት በሚያረጋግጥ ዓለም ዓቀፍ ማስተማመኛ ይሆናል።»

ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ በሽግግር መንግስቱ ቃል አቀባይና በሸንጎዉ መካከል ዉይይት ተካሂዶ እንደነበር ዘገባዎች አሳይተዋል። የተጀመረዉ ዉይይት ከመነሻዉ የሽግግር መንግስቱን መሪዎች ይሁንታ ያገኘ ባይመስልም አሁን ግን ወደዚያዉ መቃረባቸዉንና የመለሳለስ ሁኔታ መታየቱ ተነግሯል ይህ ሁኔታዉን የሚለዉጥ እንደሁ ሲያስረዱ።

«በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ግጭቱ በርካታ ደረጃዎጭ አሉት፤ ግለሰባዊ፤ የአመለካከት፤ የፖለቲካና የመሳሰሉት ነገሮች ስላሉበት የሰላም ስምምነቱ ላይ ለመድረስ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን በየመን ፕሬዝደንት የተጀመረ አዲስ ነገር አለ። ይህም አዲስ የዲፕሎማሲ መስኮት ከፍቷል ምናልባት ሶማሊያ ዉስጥ ሰፋ ያለ ግጭት ከመነሳቱ በፊት እንደማስበዉ የመጨረሻ እድል ይመስለኛል።»

የየመን ወደሽምግልናዉ መግባት አዲስ ለዉጥ ያመጣል የሚል ሃሳብ ያላቸዉ ብራይደን ሱዳን በመንግስታቱ ድርጅት የተላለፈዉን የአካባቢዉ ሀገራት ወታደሮች ወደሶማሊያ ይግቡ የሚል ዉሳኔ በመቃወሟ የሽግግር መንግስቱ ሱዳንን ለሰላም ዉይይቱ አመቺ ስፍራ አይደለችም ማለቱን ጠቅሰዋል። ሱዳንም በበኩሏ የኢትዮጵያና የኬንያ በሰላም ስምምነቱ መሪ መሆንን አልተቀበለችም። ስለዚህ ለዉይይቱ ሌላ ስፍራ ያስፈልግ ነበር፤ እናም እዚህ ጋ የመን እንደ ገለልተኛ አካል ልትወሰድ ትችላለች፥

«እንዳልኩት ይህ አዎንታዊ እድገት ነዉ። እዚህ ጋ የመን እንደገለልተኛ አካል ልትወሰድ ትችላለች። ምንም እንኳን በፊት ከሽግግር መንግስቱ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ቢኖራትም። ሸንጎዉ ሁኔታዉን ሊሞክር ያሰበ ይመስላል። ይህ አዲስ እድገት ነዉ። በዚህ አጋጣሚ እነዚህ ወገኖችን አቀራርቦ ማነጋገር ካልተቻለ ግጭቱ የማይቀር ይመስለኛል።

እንደሚታወቀዉ እስላማዊዉ ሸንጎ የሰጠዉ የጊዜ ገደብ እያለቀ ነዉ። በዛሬና በነገ መካከል አዲስ ነገር ተከስቶ ሁኔታዉ ሊሻሻልና ከስጋት ሊላቀቅ ይችል እንደሆንም ሲገልፁ። ይሄ አንዱና ዋነኛዉ ጥያቄ መሆኑን በመጠቆም ሸንጎዉ ይህን ቢልም ወዲያዉ ጥቃት ላይከፍት ይችላል። ምናልባትም ወታደራዊ ፍጥጫዉ ሊኖር ይችላል።

«የሽግግር መንግስቱና የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንገት ጥቃቱ ቢከፈት ብለዉ በተጠንቀቅ ሊቆሙ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ በተባለዉ ቀን የሰላም ዉይይቱ የሚጀምርበት ቀን ነዉ። አዎንታዊ ተስፋ ይዘን ለመጠበቅ እንሞክራለን የሸንጎዉ ሰዎችን በቅርቡ የመን አይተናቸዋል። የዲፕሎማሲዉ ጥረት ዉጤት ካሳየ ከወታደራዊ እርምጃ እነዚህ ወገኖች ይታቀቡ ይሆናል። አለበለዚያ ግን ከዉይይቱ ምንም ካልተገኘ ይህ ወር ከማለቁ በፊት ጦርነቱ ካልተነሳ እገረማለሁ።»