1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በበርሊን ዘዋሪ-የለሽ ተሽከርካሪ መሠራቱ፣

ረቡዕ፣ ጥቅምት 17 2003

በአውሮፓ፣ እ ጎ አ በ 1740 እና 1760 ዓ ም መካከል ፣ 200 ሚሊዮን ያህል ከብቶች በደስታ በሽታ ካለቁ በኋላ፤ በፈረንሳይ አገር በ Lyon ከተማ በዓለም ውስጥ የመጀመሪያው የከብቶች ሀኪሞች ማሠልጠኛ ጣቢያ መቋቋሙ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/PqNC
ያለዘዋሪ የምትሽከረከረው በበርሊን የተሠራችው MIG የተባለችው አውቶሞቢል፣ምስል AutoNOMOS

ደስታ በሽታ ፣ ከ 2 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ መጥፋቱ ፣ በዓለም አቀፉ የእንስሳት ህክምና ነክ ድርጅት ከተመሠከረ ወዲህ ፣ በሚመጣው ግንቦት ፤ በአጠቃላይ ከገጸ ምድር ስለመጥፋቱ ብሥራቱ ይነገራል ተብሎ የሚጠበቅበትን ሁኔታም አያይዘን ባለፈው ሳምንት ፣ በኢትዮጵያ የግብርና ሚንስቴር፣ የእንስሳትና እጽዋት ጤናና ቁጥጥር አመራር፣ ዋና ኀላፊ ዶ/ር በርሀ ገ/እግዚአብሔር ጋር ያደረግነውን ፤ ክፍል ፩ ቃለ ምልልስ ማሰማታችን ይታወስ ይሆናል ። በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ 2ኛውን ክፍል እናቀርባለን ፤ በቅድሚያ ግን ጥቂት ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ጉዳዮች----

የተፈጥሮን ኅልውና ለመጠበቅ የሳይንቲስቶች ትግል፣

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰው የተፈጥሮ ብዝበዛና ብክለት እነዚህ 3ቱ በዱር እንስሳትና ዐራዊት ኅልውና ላይ ብርቱ የጥፋት አደጋ እንዲያንዣብብ ማድረጉን በዛሬው ዕለት ይፋ የሆኑ የተለያዩ የጥናት ውጤቶች ጠቆሙ። ከለንደኑ «ሮያል ሶሳይቲ፣ እንደተነገረው፣ ሳይንስ ፣ ከእንስሳት እስከ አትክልቶችና ጥቃቅን ነፍሳት፣ በተሟላ ሁኔታ ሁሉንም መዝግቦ ሳያውቃቸው፣ በተፋጠነ ሁኔታ ይጠፉ ይሆናል። ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም የተነሣ ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት 2010 «የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን» ተብሎ እንዲታሰብ ያወጀው። እስከፊታችን ዓርብ ፣ ናጎያ ፣ ጃፓን ውስጥ፣ ሁለት ሳምንት ሙሉ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የመንግሥታት ጉባዔ እንስሳት፣ዕጽዋትና ጥቃቅን ነፍሳት፣ የሚጠበቁበት እርምጃ እ ጎ አ እስከ 2020 ዓ ም፤ እንዲራዘም ለመስማማት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው። አንደኛው እጅግ አሳሳቢ ይዞታ የሞቃት አካባቢዎች ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ይዞታ ነው። ካለፈው ምዕተ ዓመት መግቢያ ወዲህ ከሞላ ጎደል ግምሽ በግማሽ ተመንጥረው አልቀዋል።

እናም ከመጀመሪያው የተፈጥሮ ደን ምንጠራ በኋላ ፣ በዚያ ቦታ እንደገና ዛፍ መትከሉ ፤ የቀድሞ እንሳስትን መልሶ ማስገኘት መቻል አለመቻሉን ሳይንቲስቶች በሚገባ አያውቁትም።

ሌላው አሳሳቢ የውቅያኖሶች ይዞታ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ በአሦች ላይ በሰፊው ያልተለመደ ሁኔታ እያስከተለ ነው። በሞቃት የዓለም ክፍሎች፣ ከባህሮች ሙቀት መጨመር የተነሣ፤ የአሦች ኅልውና ብርቱ አደጋ ላይ ወድቋል።

በፕላኔታችን ኅልውና ላይ በማትኮር በየጊዜው ሰፋ ያለ ተጨባጭ ዘገባ በማቅረብ የታወቀው Living Planet በዘንድሮው የጥናት ውጤቱ ላይ እንዳሠፈረው ከሆነ፣ ሰዎች በተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ፍልጎታቸው ከምጊዜውም ይልቅ ባሻቀበበት በአሁኑ ወቅት፣ የሞቃት አገሮች እንስሳትና እጽዋት መመናመን እጅግ የሚያሳስብ ነው። እንደ Living Planet ዘገባ፣ በአሁኑ ዘመን ሰዎች ተፈጥሮ ከሚቻላት በላይ 50 ከመቶ የተፈጥሮ ሀብቷን በመቦጥቦጥ ላይ ይገኛሉ። እናም በዚህ ዓይነት አካሄድ እ ጎ አ በ 2030 ዓ ም፤ የምንገለገልባቸው ሁለት ፕላኔቶች እስከሌሉ ድርስ በዝች ብቸኛ ፕላኔት

ኅልውናን ማረጋገጥ እጅግ ይከብዳል።

ያለዘዋሪ በጎዳና የሚሽከረከር አውቶሞቢል፣

አንድ የጀርመን ሳይንቲስቶች ቡድን፣ ብዙ መኪናዎች በሚሽከረከሩበት ሰዓም ቢሆን ያላንዳች ሳንክ የትራፊክ መብራትንና ህግጋትን አክብሮ፣ ያለነጂም ሆነ ዘዋሪ፣ በተፈለገው መስመር መውጣት መግባት፣ መሽከርከር የሚችል ተሽከርካሪ ሠርቶ ማቅረቡ ተነገረ። በጀርመን የተሠራ (ሜድ ኢን ጀርምኒ)ለማለት በአኅጽሮት MIG ወይም ሚግ ተብሎ የሚጠራው ተሽከርካሪ፣ ወደፊት ነጂ የሌላቸው ተሽከርካሪዎችም በየጎዳናው መሠማራት የሚችሉበትን ሁኔታ በይፋ አሳይቷል።

3 የቪዲዮ ካሜራዎች፣ ብርሃን በማጠራቀም መቆጣጠር በሚችሉ መሣሪያዎችና ራዳር አማካኝነት በአውቶሞቢሉ ውስጥ የሚቀመጠው ኮምፑዩተር፣ ጎዳናውን ከሦስት አቅጣጫ መቆጣጠርና የትራፊኩንም ይዞታ መገምገም ይቻላል።

ያለዘዋሪ የምትሽከረከረውን አውቶሞቢል፣ በተንቀሳቃሽ iPad ን በመሰለ መሣሪያ መቆጣጠርም ይቻላል። ያለ ነጂ በጎዳና መሽከርከር የምትችለው መኪና፣ በበርሊኑ ነጻ ዩኒቨርስቲ (ፍሪ ዩኒቨርስቲ ኦፍ በርሊን) በኮምፒዩተር ሳይንስ ፕሮፌሰር ራውል ሮሃስ ተቆጣጣሪነት ነው የተሠራችው።

ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚ የተባሉ የዚህ ዓይነት ተሽከርካሪዎች ወደፊት በሰፊው በጎዳና እንዲሠማሩ እየታሰበ ሲሆን፣ ከተንቀሳቃሽ መሣሪያ በሚተላለፍ ጥሪ መሠረትም ያለዘዋሪ የሚሽከረከሩት አውቶሞቢሎች፤ የታክሲ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ማድረግ እንደሚቻል ነው የሚነገረው። ከአውቶቡስና ባቡር አገልግሎት ጋር በመጣመር ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎቹ ነጂ የለሾቹ ተሽከርካሪዎች፣ ዶክትር ራውል ሮኻስ እንደሚሉት ፣ በርሊንን የመሳሰሉ ታላላቅ ከተሞች፤ አሁን ካሏቸው የመኪናዎች መጠን፣ እጅግ ዝቅ ባለ አኀዝ፤ 1/5 ኛው ብቻ ይሆናል የሚያስፈልጋቸው።

--------

በኢትዮጵያ የከብት እርባታ አያያዝ ፣ ከብቶች የሚያድሩበት ቦታ ፣ በረት፤ ጋጥ፤ መኖ የሚያገኙበትም ቢሆን ፣ የንፅህና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ አይመስለንም። ይህ ደግሞ፣ ከኑሮ ደረጃ፣ ወይም ከኤኮኖሚ ችግር ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። የከብት እርባታን፣ አያያዝን ፤ ለማሻሻል ምን የተደረገ አለ? የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የከብቶች አያያዝ ፣ በአሁኑ ጊዜ ምን ይመስላል?

ዶ/ር በርሀ ገ/እግዚአብሔር----

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ