1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡሽ የአስተዳደር ዘመን የፈጸመው አከራካሪው ቁም-ስቅል ማሳያ እርምጃ፣

ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2001

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት፣ የስለላው ድርጅት ተግባር መርማሪ ኮሚቴ፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ፣ ባቀረበው ሰነድ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ የብሔራዊ ፀጥታ ጉዳይ አማካሪ የቀድሞዋ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮንዶሊሳ ራይስ ፣

https://p.dw.com/p/HdoF
የቀድሞዋ የአሜሪካ ው ጉ ሚ፣ ኮንዶሊሳ ራይስ፣ምስል AP

ውሃ ውስጥ በመድፈቅ መቅጣትንና የመሳሰለውን ቁም ስቅል ማሳያ እርምጃ መፍቀዳቸውን አጋልጧል። ይህ የሆነው እ ጎ አ በሃምሌ ወር 2002 ዓ ም ነው። ራፍ ሲና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከዋሽንግተን ለላከው ዘገባ ጥንቅር፣--- ተክሌ የኋላ ----

በተጠቀሰው ወቅት፣ ከያኔው የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ኀላፊ፣ ጆርጅ ቴነት ጋር የተገናኑት የቀድሞዋ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮንዶሊሳ ራይስ፣ ውሃ ውስጥ በመድፈቅ የማሰቃያው እርምጃና ሌሎችም እንዲከናወኑ ፈቃድ መስጠታቸው ይነገርላቸዋል። የአሁኑ አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር፣ በወንጀል ከተጠረጠረ ሰው፣ በግድ መረጃ ለማግኘት በማሰብ ይወሰድ የነበረው እርምጃ፣ ህገ ወጥ መሆኑን አስታውቋል። ጥያቄው፣ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የፖለቲካ ኀላፊነት የነበራቸው የቡሽ መንግሥት ባልደረቦች እስከምን ድረስ በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ነው።

ራይስ በበኩላቸው፣ CNN ለተባለው የቴሌቭዥን ድርጅት በሰጡት ቃል፣ አገራቸው፣ የተባለውን እርምጃ፣ የማትፈቅደው ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት።

«ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቁም-ስቅል የሚያሳይ የግፍ እርምጃ አትወስድም። አትፈቅደውም፣ ሠራተኞቿም፣ ይህን እንዲያደርጉ አትጠብቅም።»

ይሁን እንጂ፣ ታዋቂው ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስትና ሌላው ታዋቂ የዩናይትድ ስቴትስ ራዲዮ ጣቢያ ("Democracy Now")ኮንዶሊሳ ራይስ ፣ ቁምስቅል ማሳያውን፣ አካራካሪውን የመቅጫ እርምጃ ስለመፍቀዳቸው አይጠራጠሩም። «ዴሞክራሲ ናው»----

«የብሔራዊ ፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ኮንዶሊሳ ራይስ ቁም-ስቅል ማሳያ እርምጃዎችን፣ ውሃ ውስጥ መድፈቅን ጭምር በ 2002 ዓ ም፣ ፈቅደዋል።»

የስለላውን ድርጅት ተግባር የሚመረምረው፣ የአሜሪካ ም/ቤት ኮሚቴ፣ እ ጎ አ በ ግንቦት ወር፣ 2002 ዓ ም፣ ራይስ ፣ ከዚያም ዘጠኝ ቀናት ዘግየት ብሎ የያኔው የህግና ፍትኅ ጉዳይ ሚንስትር፣ ጆን አሽክሮፍት፣ CIA፣ «ስላስፋፋው የምርመራ ዘዴ» ተነግሮአቸው ነበር። ከራይስና አሽክሮፍት ሌላ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዲክ ቸኒም ፣ የአሸባሪው የኧል ቓኢዳ መረብ ዐበይት ተጠርጣሪ አባላት ውሀ ውስጥ እየተደፈቁ እንዲመረመሩ ማበረታታቸው ነው የሚነገርላቸው። ከቡሽ አስተዳደር አባላት በጣም ጥቂቶች ናቸው ድርጊቱን በመቃወም ሃሳባቸውን የሰነዘሩ። ከአነርሱም መካከል የህግ ጠበቃና የኮንዶሊሳ አማካሪ Philip Zelikow ይገኙበታል።

«መሠረታዊ መመሪያ አለ፣ ሰዎችን በጭካኔ ወይም ተገቢ ባልሆነ፣ ኢሰብአዊ መንገድ ማስተናገድ አይገባም የሚል!»። ዘሊኮቭ፣ አቋማቸውን ይፋ ሲያስታውቁ ለአለቃቸው ኮንዶሊሳ ራይስ እንግዲህ፣ በጸረ አሸባሪነት ጦርነት ጊዜም ቢሆን ሰዎችን ኢሰብአዊ በሆነ ይዞታ ማስተናገድ የአሜሪካ ህግ አይፈቅድም ነው ያሉት። ለረጅም ሰዓታት ክንዶችን ማንጠልጠልና አዘውትሮ እንቅልፍ መከልከልን የመሳሰሉት፣ ውሃ ውስጥ ከመደፈቅ ጋር የተቆራኑ የምርምራ ዘዴዎች ፍጹም ተቀባይነት የላቸውም።

ዘሊኮቭ እንዳሉት በዚህ አባባል CIA ፈጽሞ አይስማማም ነበር።

«CIA ይቃወማል፣ የበለጠ የምናውቅ እኛ ነን። መርኀ-ግብሩን የማናካሂድ እኛው ነን። መመሪያው ደግሞ ይሠራል።» ነበረ የሚሉት።

የቡሽን ንግግር ያዘጋጁ የነበሩት ማርክ ቲሰን ግን፣ ቁም ስቅል ማሳየትን የሚቃወሙትን የዋሆች አድርገው ነበረ የሚመለከቱት።

«የዋህነት ምን ማለት እንደሆነ ልንገራችሁ። ያለነዚህ ቴክኒኮች መረጃ መሰብሰብ ይቻላል ብሎ ማሰብ ራሱ ሞኝነት ነው።»

ማርክ ቲሰን ከዚህ ጋር በማያያዝም ፣ በምርመራ ዘዴው ሳቢያ፣ በዛ ያሉ ጥቃቶች እንዳይደርሱ ለመግታት ተችሏልም ባይ ናቸው።

ራልፍ ዚና/ተክሌ የኋላ/አርያም አብርሀ

►◄