1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉባኤው የአፍሪካ እቅድ ተግባራዊነት አጠራጥሯል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 2009

በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ባለፈው  ሳምንት መጨረሻ የተካሄደው የቡድን 20 ሃገራት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ጉዳይ ከፍተኛ ቦታ ያገኛል የሚል ቅድሚያ ግምት ነበር፡፡ ጀርመን ለአፍሪካ ያዘጋጀችው እቅድ የጉባኤው ዋና መወያያ ጭብጥ እንዲሆን ፍላጎት ነበራት፡፡ በሁለቱ ቀናት ጉባኤ ግን የአፍሪካ ጉዳይ ወደ ጎን መገፋቱ በገሃድ ታይቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2gMR1
Deutschland G20 Gipfel Familienfoto
ምስል Reuters/A. Schmidt

African Issues Overshadowed on G20 Summit - MP3-Stereo

ቡድን 20 በሚል መጠሪያ የሚታወቁት በሀብት የበለጸጉ ሃገራት በተለምዶ ለጉባኤ ሲቀመጡ አጽንኦት የሚሰጧቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ነው፡፡ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እና የገንዘብ ገበያ ቁጥጥር በጉባኤው በአጀንዳነት መቅረብ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የወቅቱ የቡድን 20 የመሪነት ሚና የተረከበችው ጀርመን ግን በመሰል ጉባኤዎች እምብዛም ትኩረት ከማያገኙ ጉዳዮች ጀርባ የዓለም ኃያል መሪዎችን ለማሰለፍ አቅዳ ነበር፡፡ ከእቅዷ ዋንኛውን ድርሻ ወስዶ የነበረው ደግሞ የአፍሪካ ጉዳይ ነው፡፡ የጀርመን መራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም በስብሰባ መክፈቻ ንግግራቸው ይህንኑ አስታውሰዋል፡፡ 

“እዚህ ያልተገኙ እኛ ሥራችንን በአግባቡ እንድንከውን ቢሹ ትክክል ነው፡፡ በዚህም መሠረት በጀርመን በኩል ከኢኮኖሚ እና ንግድ ባሻገር እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኃይል ፖሊሲዎች ያሉ ጉዳዮች የመወያያ አጀንዳ እንዲሆኑ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ጀርመን በአፍሪካ ላይ ትኩረት አድርጋለች፡፡ ምክንያቱም እኛ አውሮጳውያን አፍሪካን የምንመለከተው እንደ ጎረቤት አህጉር ነው፡፡ ወደፊት እንድትጓዝም ሁሉንም ማድረግ አለብን” ብለዋል ሜርክል፡፡

 መራሔተ መንግሥት ሜርክል  ከጉባኤው ቀድመው ይፋ ባደረጉት “ኮምፓክት ፎር አፍሪካ” በተሰኘ እቅዳቸው የግል ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለሚስቡ ሃገራት 300 ሚሊዮን ዮሮ መመደባቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ እቅዱን የተቀበሉ ሰባት የአፍሪካ ሃገራት የግል መዋዕለ ንዋይን ለመሳብ የሚጠበቅባቸውን ማሻሻያ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ሃገራት በጀርመን በኩል ሙያዊ እገዛ እንደሚደረግላቸውም ተነግሯል፡፡ 

በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ለአፍሪካ ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ያመጣል የተባለ እቅድ ተቀባይነት ቢያገኝም በሌሎች አንገብጋቢ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በመሸፈኑ የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት አልሳበም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ በፓሪስ ከተፈረመው ስምምነት ለመውጣት ባሳለፈችው ውሳኔ መጽናቷ የጉባኤው ዋነኛ መነጋገሪያ ነበር፡፡ የአፍሪካ ነገር ወደ ጎን መገፋቱ በታዛቢዎች ተተችቷል፡፡ “ዋን” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት የቡድን 20 ዳይሬክተር ፍሬዴሪካ ሩደ አንዷ ናቸው፡፡ 

G20 Angela Merkel Jacob Zuma
ምስል Getty Images/AFP/O.Andersen

“መራሔተ መንግሥት ሜርክል አፍሪካ የቡድን 20 ጉባኤ አስኳል እንዲሆን ፈልገው ነበር፡፡ አፍሪካን የአጀንዳቸው ቁንጮ ለማድረጋቸውም በቂ ምክንያት አላቸው፡፡ እንደምናውቀው ከ50 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አፍሪካ ውስጥ የሚኖረው ወጣት በሁሉም የቡድን 20 ሃገራት ካሉት በላይ ይሆናል፡፡  ለአፍሪካ እና ለመላው ዓለም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅሞች ለሚያመጣው ለዚህ የወደፊት ሁነት በአስቸኳይ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን አሁን ያየነው ነገር ውስጣዊ ሽኩቻዎች እና ክፍፍሎች ቡድን 20ን ከዚህ ከርዕይ መንገድ እንዳናጠቡት ነው፡፡ እንዳለመታደል አፍሪካ ዋና አጀንዳነት መሆን ቢገባትም ያንን ቦታ እምብዛም አላገኘችም” ይላሉ ፍሬዴሪካ፡፡        

ሜርክል የቡድን 20 መሪዎች ከአፍሪካ ጋር በኢንቨስትመንት ላይ የተመሰረተ አዲስ አጋርነት ለመመስረት መስማማታቸው የጉባኤው አዎንታዊ ውጤት አድርገው ይወስዱታል፡፡ ፍሬዴሪካም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ህልሙ እና ተነሳሽነቱ በወረቀት ብቻ የተቀመጠ ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡ “አሁን ያሉ ችግሮችን እና የወደፊቱን ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቡድን 20 የጋራ ቁርጠኝነት ይጎድለዋል” ይላሉ ፡፡

የታንዛንያው የፓለቲካ ተንታኝ ጄነራሊ ኡሊምዌንጉ የቡድን 20ን ተነሳሽነት በተለየ መልኩ ነው የሚመለከቱት፡፡ “የአፍሪካ ችግር በቡድን 20 ጉባኤ አይፈታም” ባይ ናቸው፡፡

“ከአፍሪካ ድህነት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሀምቡርግ፣ ዋሽንግተን ወይም ሻንጋይ ሊፈቱ አይችሉም፡፡ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በአፍሪካውያን መሪዎች ጥረት እና ዕውቀት ነው፡፡ በሀገራቸው ያለውን ችግር በራሳቸው ሊረዱት እና እንዴት መፍታት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል፡፡ እንደ ጀርመኖች አንጌላ ሜርክል ይህንን ሲናገሩ ጌርድ ሙለር ደግሞ ያንን ሲናገሩ አድምጬያቸዋለሁ፡፡ እነርሱ የራሳቸው ችግር አለባቸው፡፡ የአፍሪካ ድህነት እነርሱ ላይ ተጽእኖ ማምጣቱን እና በርካታ ስደተኛም ወደ ሀገራቸው መግባቱን ላይወዱት ይችላሉ፡፡ የአፍሪካ ድህነት ከሚያሳድርባቸውን ተጽእኖ ራሳቸውን ለመጠበቅ መወሰድ ያለበትን ሁሉ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ትንሽ ድጋፍ በማድረግ ህዝቡ በፋብሪካ እንዲቀጠር እና ድሀዎችም እንዲረዱ በማድረግ ይሆናል፡፡ ሆኖም ለአፍሪካ የድህነት ችግሮች ከውጭ የሚመጣ መፍትሄ የለም” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ