1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከታሰሩት ውስጥ የሆቴሎች ባለቤቶች ይገኙበታል

ሐሙስ፣ ነሐሴ 11 2009

በአማራ ክልል ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከታዩ አድማዎች እና ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው እየተነገረ ነዉ፡፡ በባህር ዳር እስከ 200 የሚጠጉ ግለሰቦች መታሰራቸውን የአካባቢው ሰዎች እና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ ሰዎች መታሰራቸውን የሚቀበለው የአማራ ክልል አስተዳደር በበኩሉ ቁጥሩ “የተጋነነ ነው” ይላል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2iQMv
Brasilien Handschellen der Gefängnisinsassen vor dem Hauptquartier der NGO Acuda
ምስል Reuters/N. Doce

ከታሰሩት ውስጥ የሆቴሎች ባለቤቶች ይገኙበታል

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በባህር ዳር የተጠራው የሥራ ማቆም አድማ ከተማዋን አሽመድመዷት ነበር የዋለው፡፡ አድማው የተጠራው ከአንድ ዓመት በፊት በዚያው ቀን በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለመዘከር በሚል ነበር፡፡ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እና በመልዕክት ልውውጥ በተዘጋጀው አድማ ከሱቅ እስከ መደብር፣ ከካፌ እስከ ሆቴል በራቸውን ዘግተዋል፡፡ የከተማዋ ደም ስሮች የሆኑት ነጭ ሰማያዊ ባጃጅ ታክሲዎችም ከመንገድ ጠፍተው ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላ ነበር፡፡ 

የአድማው ዕለት እና ማግስት የከተማዋ አስተዳደር ሰዎች እና የጸጥታ ኃይሎች በየአካባቢው እየዞሩ የንግድ ተቋማት እንዲከፈቱ በማስጠንቀቃቸው፣ የተወሰኑትንም ማሸግ በመጀመራቸው አገልግሎት ሰጪዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ተመልሷል ቢባልም በአድማው ተሳትፈዋል የተባሉ ሰዎች ግን በቀጣይ ቀናት እንደታሰሩ የባህር ዳር ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው ተወላጅ እና የፖለቲካ አራማጅ እስሩ አሁንም ቀጥሏል ይላሉ፡፡ 

“ለምን ሥራ አቆማችሁ? ወይም ደግሞ ሰማዕቶችን ለምን አሰባችሁ? በሚል ነው እንግዲህ ቤት ለቤት እየገባ ወጣቶችን ከማፈስ ጀምሮ ትላልቅ የሆቴል ባለቤቶችን፣ አደባባይ ላይ የሰማችሁትን በሙሉ፣ በጅምላ የማፈስ ተግባር ውስጥ የተገባው፡፡ እስካሁን ከዚያ ባለኝ ተጨባጭ መረጃ ከመቶ በላይ ወጣቶች ታፍሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ ፍርድ ቤት የቀረቡ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በየጣቢያው ያስቀመጧቸው አሉ፡፡ ምክንያቱም የሚያስከስ ነገር የለም፡፡ አንድ አሽከርካሪ ደስ ባለው ሰዓት ላይ ማቆም ይችላል፤ ደስ ሲለው ደግሞ መስራት ይችላል፡፡ ለምን አቆማችሁ ብሎ ሊያስጠይቅ የሚችል የሕግ አግባብም የለም፡፡ ወንጀልም አይደለም፡፡ እና ምንም ዓይነት የሕግ አግባብ በሌለው ሁኔታ ነው እንግዲህ የበቀል መንገዱ እየተወሰደባቸው ያለው” ይላሉ የአካባቢው ተወላጅ፡፡

“አድማው በመንግሥት እና በገዢው ፓርቲ ላይ ያመጣበት ኪሳራ ከፍተኛ በመሆኑ በቁጭት የተወሰደ እርምጃ ነው” ሲል የፖለቲካ አራማጁ እስሩን ይቃወማሉ፡፡ ሪፖርተር የተሰኘዉ የሀገር ዉስጥ ጋዜጣ በባለፈው እሁድ እትሙ በባህር ዳር ከተማ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ ከ200 በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች እና ወጣቶች መታሰራቸውን ዘግቦ ነበር፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል በከተማዋ ውስጥ “ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ፣ በሆቴል እና ትልልቅ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ” ግለሰቦች እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡ 

Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

በባህር ዳር ታስረው ከሚገኙ ሰዎች መካከል የድብ አንበሳ እና የወትር ፍሮንት ሆቴሎች ባለቤቶች አቶ ሽባባው የኔአባት እና አቶ መሠረት ገረመው እንደሚገኙበት ለግለሰቦቹ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ ሁለቱ የሆቴል ባለቤቶች “በአድማዉ ቀን ሆቴላቸውን ዘግተዋል” በሚል ከሳምንት በፊት እንደታሰሩ የቅርብ ሰዎቻቸው ተናግረዋል፡፡ በባህር ዳር አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት አቶ ሽባባው ከሌሎች 13 ሰዎች ጋር ከትላንት በስተያ ነሐሴ 9 ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡   

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ በቀለ በባህር ዳር ሰዎች መታሠራቸውን አልሸሸጉም፡፡ ወደ 200 ገደማ ሰዎች ታሥረዋል የሚባለው “በጣም የተጋነነ” ነው የሚሉት አቶ ጸጋዬ ቁጥራቸውንን እና የእስራቸውን ምክንያት እንዲህ ይገልጻሉ፡፡ 

“ቁጥሩ በእርግጥ በየጊዜው ተለዋዋጭ ነው፡፡ እስካሁን ባለኝ መረጃ ወደ 30 ናቸው፡፡ የከተማውን ጸጥታ የሚያውክ ተግባር ስለነበረ፣ በዕለቱ የሰው ህይወት ባይልፍም ነገር ግን ደግሞ በመንገድ ላይ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል፡፡ እንደገና ደግሞ በማግስቱ ሱቆችን የመዝጋት እና የትራንስፖርት፣ የባጃጅና የታክሲ ተሸከርካሪ የማቆም እንቅስቃሴ ነበረ፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እያደር የሚለይ ቢሆንም ዋናው ነገር ጸጥታውን በማወክ ተባባሪ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ኃይሎች ናቸው፡፡ ጥርጣሬው ትክክለኛ የሆኑ በፍርድ ቤት ይታያሉ፣ ጥርጣሬው ስህተት የሆነው ደግሞ እየተለቀቁም ጭምር ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ የአዝዋ ሆቴል [ባለቤት] ተለቅቀዋል፡፡ አሁን ዋናው ነገር እያጣሩ፣ የሚገባው ይገባል፣ የሚወጣው ይወጣል፡፡ አሁንም ያለቀለት ነገር አይደለም” ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ጸጋዬ ገለጻ ሐምሌ 30 በባህር ዳር ቦምብ በፈነዳበት ዕለት አምስት ሰዎች የተያዙ ሲሆን በማግስቱ ሱቆች እንዲዘጉ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ አራት ተይዘዋል፡፡ ከንግድ ማህበረሰብ ጋር በተያያዘ ደግሞ 24 ሰዎች መታሠራቸውን ገልጸዋል፡፡ የታሸጉ ሱቆቹን ሕግ ሳይፈቅድ መልሰው በመክፈት ዘጠኝ ሰዎች መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ጸጋዬ ተያዙ ያሏቸው ሰዎች ድምር 42 ይደርሳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረባቸውን እንደማያውቁ የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ የማጣራት ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው ፖሊስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ አማራ ክልል እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ አየነው በላይ “ስብሰባ ላይ ነኝ” የሚል ምላሽ ከሰጡን በኋላ እርሳቸውን በድጋሚ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡ የአዝዋ ሆቴል ባለቤትን ጉዳይ ለማጣራት የደውልንላቸው የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ “ምላሽ መስጠት አልፈልግም” ሲሉ በቁጣ መልሰውልናል፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ