1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባሕርዳር ታስረው የከረሙ ተፈቱ

ረቡዕ፣ መጋቢት 26 2010

ታስረው ዛሬ ከተፈቱት መካከል አምስት የዩኒቨርሲቲ መምህራን፤ ጠበቃ እና ጋዜጠኞች ጭምር ይገኙበታል።  አስራ ስምንቱ ግለሰቦች የሚያቋቁሙት ብሔርተኛ የፖለቲካ ፓርቲ በሚያዝያ ወር በጎንደር ከተማ በይፋ ይመሰረታል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2vVBp
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በአማራ ክልል በባሕርዳር ከተማ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. የታሰሩ 19 ግለሰቦች በዛሬው ዕለት ከእስር ተለቀቁ። የአማራ ብሔርተኛ ድርጅት ለመመስረት በዝግጅት ላይ የነበሩት ግለሰቦች በእስር ቢቆዩም ክስ እንዳልተመሰረተባቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና አራማጅ የሆኑት አቶ እንዳላማው ክንዴ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ታስረው ዛሬ ከተፈቱት መካከል አምስት የዩኒቨርሲቲ መምህራን፤ ጠበቃ እና ጋዜጠኞች ጭምር ይገኙበታል።  
አስራ ስምንቱ ግለሰቦች የሚያቋቁሙት ብሔርተኛ የፖለቲካ ፓርቲ በሚያዝያ ወር በጎንደር ከተማ በይፋ እንደሚመሰረት አቶ እንዳላማው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ የተጠረጠሩ 1107 ሰዎች መታሰራቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚመረምረው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ባለፈው ሳምንት አስታውቀው ነበር። እሁድ መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለቀድሞ እስረኞች በተዘጋጀ የምሥጋና መርኃ-ግብር መገባደጃ ላይ በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የታሰሩት 11 ሰዎች ዛሬም አልተፈቱም።  በወቅቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ፖለቲከኛው አቶ አንዷዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኞቹ እስክንድር ነጋ እና ተመስገን ደሳለኝ፣  ጦማሪያውያኑ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማኅሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ወርቅአገኘሁ ይገኙበታል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲው መምሕር አቶ ስዩም ተሾመ እና የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታየ ደንደአ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገች በኋላ የታሰሩ ሲሆን እስካሁን አልተፈቱም።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ