1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በባቲ ወረዳ ታጣቂዎች 3 ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2014

በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ከሳር ግጦሽ፣ ስርቆት እና ግድያ ጋር በተያያዘ የሚከሰትን ችግር ለመፍታት ለእርቅ በተቀመጡ ሰዎች ላይ ባለፈው ቅዳሜ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 3 ሰዎች መገደላቸውን እና የቆሰሉም እንዳሉ የአፋር እና የአማራ ክልል አዋሳኝ ወረዳ ኃላፊዎች ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4BMjY
Äthiopien Konflikt im Norden
ምስል Seyoum Getu/DW

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳና በአፋር ክልል አዳአር ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ከእንስሳት ሰርቆት፣ ከሳር ግጦሽና አልፎ አልፎ ከሚፈጠር ግድያ ጋር በተያያዘ በአዋሳኝ አካባቢዎች ረዘም ያለ የሰላም ችግር እንደነበር የሁለቱም ወረዳ አስተዳዳሪዎች ለዶይቼ ቬለ አመልክተዋል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ተከታታይ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የነገሩን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል ሀሰን የዚህ አካል የሆነ ውይይት በባቲ ወረዳ ልዩ ሰሟ “ጨኮርቲ” ተካሄዶ ውይይቱ ካበቃ በኋላ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የባቲ ወረዳ የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ተገድሏል፣ የወረዳው ሚሊሺያ ጽ/ቤት ኃላፊም ቆስሏል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የባቲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሰኢድም ይህንኑ አረጋግጠውልናል፡፡
በአፋር ክልል የአዳአር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ኑር በበኩላቸው ታጣቂዎች በሁለቱ ወረዳ ተወያዮች ላይ በፈፀሙት ጥቃት በአፋር በኩል ሁለት ሰዎች መሞታቸውን 4 መቁሰካቸውን ተናግረዋል፡፡
የድርጊቱ ፈፃማዎች ማንነት አስካሁን ባታወቅም የአፋርንና የኦሮሞን ህዝቦች አንድነትና መተሳሰብ የማይፈልጉ ኃሎች መሆናቸውን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊው አቶ ጀማል ሐሰን አመልክተዋል፡፡ አጥፊዎችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባቲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መሐመድ ሰኢድ አረጋግጠዋል፡፡ በአፋርና አማራ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ከሳር ግጦሽና ከእንስሳት ሰርቆት ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደነበር ታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ