1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የቦሮ ዴምክራቲክ ፓርቲ ጠየቀ

ሐሙስ፣ መስከረም 13 2014

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል "ሁሉንም ፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ" የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የቦሮ ዴምክራቲክ ፓርቲ ጠየቀ። ፓርቲው ጥያቄውን ያቀረበው በክልሉ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምጽ ባልተሰጠባቸው አካባቢዎች መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሔድ የታቀደው ምርጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ዳግም ከተራዘመ በኋላ ነው። 

https://p.dw.com/p/40klh
Äthiopien Logo Boro Democratic Party
ምስል Boro Democratic Party

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የቦሮ ዴምክራቲክ ፓርቲ ጠየቀ

ከመስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገዥ ፓርቲ በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ክልላዊ የሽግግር መንግስት ወይም ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት እንዳለበት የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ገለጸ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን ተከትሎ መስከረም 24 ቀን 2014 መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ ባለመኖሩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሶስት አማራጮችን ማቅረባቸውን የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት በክልል ደረጃ እንዲቋቋም፣ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለባቸው በመተከል እና በካማሺ ዞኖች የፌድራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት የሚሉት ይገኙበታል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ትናንት ማምሻውን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ "ህዝቡ ባንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ ሳይደናበር የስልጣን መገኛ ምርጫና የህዝብ ድምጽ ብቻ መሆኑን በማወቅ ለአካባቢው ሰላም መታገል ይገባል" ብሏል፡፡  የቤኒሻጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ካሚል ሀሚድ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ሀገር አቀፍ መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ሀቀፍ ደረጃ አብላጫ ድምጽ ያገኘ መንግስት ይመሰርታል ብለዋል፡፡ ለቀጣይ ምርጫም የቦርዱን ውሰኔ እንደሚጠብቁ  ገልጸዋል፡፡ 

የቦሮ ዴሞክራክ ፓርቲ ትናንት ባወጣው መግለጫው በክልሉ ከዚህ ቀደም በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም የተላለፈው ምርጫ አሁንም በተለያዩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት እንደማይካሄድ እና በካማሺ እና መተከል ዞን የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ አለመቻሉን ገልጿል፡፡ 

Äthiopien | Kamil Hamid | Head of the Political Sector of Prosperity Party
የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ካሚል አሚድ ምስል Negassa Dessalegn/DW

የቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ካሚል አሚድ በምርጫ ቦርድ በሚወጡ የጊዜ ሰለዳ መሰረት ምርጫ ይካሄዳል ያሉ ሲሆን ከመስከረም 24 በኋላም አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መንግስት ይመሰርታል ብለዋል፡፡ መስከረም 20 ምርጫ አይካሄድም ሚል ሀሳብም ከምርጫ ቦርድ እንዳልደረሳቸው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአሶሳ ዞን በተካሄደውን ምርጫም የተፈጠሩት የቁሳቀሱ እጥረትና ስህተቶችም ከፓርቲው ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ሳይሆን ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ማስተካከል የሚችል ጉዳይ እንደነበርም አክለዋል፡፡
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ በበኩላቸው በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ በመስከረም 20 እንደማይካሄድ አስታውቀዋል፡፡ ምርጫ የሚካሄድበት ዕለትም ምርጫ ቦርድ ለወደፊት የሚወስን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛ ሀገር ሀቀፍ ምርጫ በአሶሳ ዞን በሁለት ምርጫ ክልሎች ባጋጠመው የድምጽ መስጫ ወረቀት እና የኮድ ስህተት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ለጊዜው መቋረጡን በበወቅቱ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወቃል፡፡ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምርጫ የማካሄድ እና ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ የሚራዘም ከሆነ መንግስትና የመንግስት መዋቅር አይኖርም በማለት አንድ አንድ የተባሉ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ግጭትና ሁከት ለመቀስቀስ  እየተዘጋጁ መሆናቸውን የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታን አስመልክቶ  በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው  ባማሰራጩት መረጃ አመልክተዋል፡፡ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ የህዝብ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም አክለዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ