1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካእስያ

የአፍጋኒስታን ወጣቶችና ሴቶች ተስፋ

ዓርብ፣ ነሐሴ 14 2013

የታሊባን ቡድን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ ሳምንት ሊሆነው ነው። ለመሆኑ የቡድኑ ስልጣን መያዝ ለአፍጋኒስታን ወጣቶች እና ሴቶች ምን ማለት ይሆን?

https://p.dw.com/p/3zCn6
Afghanistan Einmarsch der Taliban in Kabul
ታሊባኖች ካቡልን ከተቆጣጠሩ በኋላ አንድ የውበት ሳሎን ሰራተኛ ሳትሸፋፈን ያለችን ሴት ምስል በቀለም ያጠፋሉምስል Kyodo/dpa/picture alliance

የአፍጋኒስታን ወጣቶችና ሴቶች ተስፋ

የታሊባን ቡድን የአፍጋኒስታንን መዲና ካቡል ከተቆጣጠረ እና ስልጣኑን በእጁ ካስገባ በኋላ እንደተሰጋው ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ለውይይት ክፍት መሆኑን አሳይቷል። ይሁንና አፍጋኒስታንን እና ቡድኑን በሚገባ የሚያውቁ ታዛቢዎች ቡድኑ የሚለውን በፍፁም አያምኑም። ይልቁንስ ሀገሪቱ ከአለም አቀፍ ትኩረት ስትወጣ ቡድኑ አላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ባይ ናቸው።  ይህ ደግሞ የአፍጋኒስታንን ወጣቶች እና ሴቶች መብት ክፉኛ ይነካል። «የታሊባን ቡድን በፊት ከምናውቀው ቡድን ምንም የሚለየው ነገር የለም» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ቴሌቪዥን የተናገሩት ሳድ ሞህሴኒ «ሞቢ ግሩብ» የተባለ የአፍጋኒስታን የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ስራ አስኪያጅ ናቸው።«ሴቶች እና ልዳገረዶች እንደ 1990 ዓ ም መኖር ይጀምራሉ። ሴቶች ወንድ አብሯቸው ከሌለ ከቤት መውጣት አይችሉም። ልጃገረዶች ትምህርት ቤት መሄድ አይችሉም፤ ስራ መስራት አይፈቀድላቸውም። ክሊኒክ እንኳን ብቻቸውን መሄድ አይችሉም። ዘመድ የሆነ ወንድ አብሯቸው ከሌለ ማለት ነው።»

እጎአ ከ 1996 እስከ 2001 ዓ ም አብዛኛው የአፍጋኒስታን ክፍል በታሊባን ቁጥጥር ስር ነበር። ይህም በዩናይትድ ስቴትስ ተልኮ ሊከሽፍ ችሏል። እስከዛ ድረስ ታሊባን በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ሴቶች ሙሉ ለሙሉ ሳይሸፋፈኑ እና ከጎናቸው ወንድ ሳይኖር ጎዳና ላይ መታየት አይችሉም ነበር። ይህ አሁን ከ20 ዓመት ገደማ በኋላ የበርካታ የአፍጋኒስታን ሴቶች እጣ ፈንታ ሊሆን ይችላል። ሌላም ስጋት አለ። ቀደም ሲል ታሊባን ይቆጣጠርባቸው በነበሩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች እንደሚሉት ከሆነ ልጃገረዶች በግዳጅ ይዳራሉ። « እኔ መማር ነው የምፈልገው ነገር ግን ታሊባኖች ትምህርት ቤት እንድንሄድ አልፈቀዱልንም» ትላለች ታቻር ከሚባል አካባቢ ሸሽታ ካቡል የገባችው ልጃ ገረድ ለዶይቸ ቬለ። ይሁንና አሁን ምንም መሸሻ ቦታ የላትም።  ካንዳሀር ከሚባል አውራጃ ደግሞ የታሊባን ተዋጊዎች ባንክ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ዘጠኝ ሴቶችን ወደቤታቸው እንደላኩ ሌላኛዋ ወጣት ትናገራለች።  የተሰጣቸው ትዕዛዝ እቤት ውስጥ መቀመጥ ሲሆን አንድ የቤተሰቡ አባል የሆነ ወንድ የእነሱን ቦታ ተክቶ መስራት እንደሚችል ተነግሯቸዋል። « ታሊባኖች መስኪድ ውስጥ መጡና የእነሱ ተዋጊዎች ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች እና ልጃ ገረዶች እንደሚያገቡ ነገሩን»ለዚህም ነው ወደ መዲናዋ የሸሸነው ትላለች።

Kinderehe in Afghanistan
ልጃገረዶች በታሊባን ቡድን በግዳጅ ይዳራሉምስል Getty Images/P. Bronstein

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትዊተር ባሰራጩት መልዕክት ሴቶች እና ልጃገረዶች ለአመታት የታገሉበት መብታቸውን ሲነጠቁ « አሰቃቂ እና ልብ የሚሰብር ነው» ነው ያሉት። የታሊባንን ህግ የሚጥሱ ሴቶች ከዚህ ቀደም በአደባባይ ነበር የሚቀጡት። ይገረፋሉ፤ ሲከፋም ህዝብ ፊት በስታድዮም ውስጥ ይረሸናሉ። ይህ ዳግም እንዳይከሰት ለሴቶች መብት ሲሟገቱ የነበሩ ሴቶች ይናገራሉ።  
ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት የሟጋች የሆነችው ማሪያም አታኢ የዛሬ ሳምንት ዓርብ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ « ታሊባን ካቡልን የሚቆጣጠር ከሆነ » የእሷም ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን ገልፃ ነበር። እንዲሁ ካቡል ውስጥ በሚገኝ የዩናይትድ ስቴትስ ዮንቨርስቲ መምህር የሆኑትም ፕሮፌሰር ቪክቶሪያ ፎንታን « የሴት ተማሪዎቻቸው ጉዳይ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ለዶይቸ ቬለ TV ስጋታቸውን ገልፀው ነበር።  በዚህ መሀል ታሊባን መዲናዋን ተቆጣጥሯል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ዶይቸ ቬለ ሚሪያም አታኢን በስልክ ማግኘት አልቻለም። የፈረንሳይ ዜጋ የሆኑት ፕሮፌሰር ቪክቶሪያ ደግሞ ለጊዜው ከለላ አግንተው እዛው አፍጋኒስታን ውስጥ ተሸሽገው ይገኛሉ። ሀገራቸው ፈረንሳይ ዜጎቿን  የምታስወጣበት አይሮፕላን ማረፊያ ግን መሄድ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። 


አፍጋኒስታን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በርካቶች የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል። የ 36 ዓመቱ ቲም ፎክን ከእነዚህ አንዱ ነው። የጀርመን ልዑኩ ወታደር አፍጋኒስታን ውስጥ ህይወቱን ሁሉ ሊያጣ ደርሶ ነበር።« ከ 2010 ዓም ከጦር ባልደረቦቼ ጋር ተላክን። ከዛ ጥቅምት 17 ቀን ጠላት በተኮሰው ጥይት ቆሰልኩ። እንደ እድል ሆኖ ደፋር የሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ህይወቴን አተረፏት።» ቲም የግራ እጁ ላይ ነው የተመታው። ምንም እንኳን በርካታ ቀዶ ህክምና ቢደረግለትም እጁን ግን ማንቀሳቀስ አይችልም።  ዛሬ ቲም የጦር ጠመንጃውን በስፓርት ጠመንጃ ተክቶ በ25 ዓመቱ የደረሰበትን ጠባሳ ያክማል። « አሁን ሂንዱኩሽ ላይ ጀርመንን መከላከል ሳይሆን ተልኮዬ ለጀርመን ሜዳልያ ማስገኘት ነው። ይህ ብቸኛ እድሌ ነው። ይህም እውን እንዲሆን ያመቻቹልኝ በርካታ የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ። ቲም የሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ በሚጀምረው የአካል ጉዳተኞች የኦሎምፒክስ ውድድር ይሳተፋል።  ስፓርቱ ጦርነት ላይ የደረሰበትን የአካል እና የአዕምሮ ጉዳይ ለማከም እንደረዳው ይናገራል። 

ዛኪያ ኩዳዳዲ ሌላዋ በአካል ጉዳተኞች ኦሎምፒክስ ወይም ፓርኦሎምፒክስ መሳተፍ የምትፈልግ አፍጋኒስታናዊት ወጣት ናት። ታሊባን ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን ይህ ፍላጎቷ ህልም ብቻ ሆኗል። አሰልጣኝዋ ለሮይተርስ ዜና ምንጭ በሰጡት ቪዲዮ ላይ የ 23 ዓመቷ የቴኳንዶ ስፖርተኛ « ከቤቴ መውጣት አልቻልኩም። የምፈልገውን ነገር ለመግዛትም ሆነ ለመሰልጠን መንቀሳቀስ አልቻልኩም» ስትል ትደመጣለች።  ዛኪያ ተሳክቶላት ወደ ጃፓን ብትሄድ አገሯን ወክለው ከሚወዳደሩ ሁለት አካል ጉዳተኛ ሴቶች አንዷ ትሆን ነበር። ይሁንና እሷም ትሁን ለአትሌቲክስ ውድድር የታጨችው የሀገሯ ልጅ ሆሳይን ራሶሊ ታሊባን ካቡልን ከመቆጣጠሩ በፊት ሀገራቸውን መልቀቅ አልተሳካላቸውም። « ቤተሰቦቼ ታሊባን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ሄራት ከተማ ነው ያሉት። እኔ አሁን ካቡል ውስጥ የሚገኙ የሩቅ ዘመዶቼ ጋር ነው የምገኘው። ቤተሰቡ ልጆቹን እንኳን በአግባቡ መመገብ አይችልም። እኔ ደግሞ ሌላ ጫና ሆኜባቸዋለሁ።» 
ስትል ስፖርተኛዋ ዛኪያ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳት በቪዲዮ ትማፀናለች። በውድድሩ ላይ ግን የሚፈጥረው ለውጥ የለም። ሁለቱም ሴት ስፖርተኞች በውድድሩ እንደማይካተቱ ይፋ ሆኗል። ዛኪያ ስትወለድ ጀምሮ አንድ እጅ ብቻ ኖሯት የተወለደች አካል ጉዳተኛ ናት። ኤዚያን ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም ያለፈው ዓመት ይፋ እንዳደረገው ጥናት ከሆነ ደግሞ አፍጋኒስታን ውስጥ 14 በመቶ ያህሉ ከባድ አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው። በብሔራዊ አካል ጉዳተኛ ኮሚቴ ስር ከ 2000 በላይ አካል ጉዳተኛ አትሌቶች ይገኛሉ። 

ዋስላት ሀስራት ናዚሚ ጋዜጠኛ የዶይቸ ቬለ DW የአፍጋኒስታን ክፍል ኃላፊ ናት። ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ አንስቶ በተለይ አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኙ ባልደረቦቻችን ሁኔታ እጅጉን ያሳስበናል ትላለች። አፍጋኒስታን ውስጥ ቤተሰብ እና ዘመድ ያሏቸው የቦን ከተማ  ባልደረቦችም ስጋት ላይ ናቸው። « እነሱም ዛቻ ይደርስባቸዋል። አሰቃቂ ነገር ነው የምንሰማው። ታሊባኖች ቤት ለቤት ጋዜጠኞችን እያሰሱ እንደሆነ እንሰማለን። በማንኛውም ሰዓት የአንዳችንን ቤተሰብ ላይ የሆነ ጉዳት ይደርሳል የሚል ስጋት አለን። ስለሆነም ከፍተኛ የአዕምሮ ውጥረት ላይ ነን።  »
ዋስላት ይህን ባለች ማግስት ታሊባኖች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ አንዲት ጀርመን የምትገኝ የዶይቸ ክፍል ባልደረባን የቅርብ ዘመድ ገድለው የሰውየውን ልጅ አቁስለዋል።  የሌሎች ሶስት ለ DW የሚሰሩ ጋዜጠኞች ቤት ደግሞ ተበርብሯል። 

Waslat Hasrat-Nazimi
ዋስላት ሀስራት ናዚሚ ጋዜጠኛ የዶይቸ ቬለ DW የአፍጋኒስታን ክፍል ኃላፊምስል Fahim Farooq

በታሊባን ቁጥጥር ስር የዋለችው አፍጋኒስታን ሴቶች እና ወጣቶች እጣ ፈንታስ  ምን ይሆን? ዋስላት እንደምትለው ከሆነ የሴቶቹ መብት ከቦታ ቦታ ይለያያል።  «በአንዳንድ የአፍጋኒስታን አካባቢ የሚገኙ ልጃገረዶች ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። ሴቶችም ስራ ይሰራሉ። በተለይ ደግሞ በጤናው መስክ የተሰማሩ ሴቶች ተፈቅዶላቸዋል። በሌሎች አካባቢ የሚገኙ ሴቶች ደግሞ መስራት አይፈቀድላቸውም። ስለዚህ ግልፅ የሆነ አሰራር የለም። ገና መታገስ ይኖርብናል።»የሴቶችን መብት በተመለከተ በታሊባን ተዋጊዎች ዘንድ የተለያየ አገላለፅ ቢኖርም ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ ሁሉም በሻሪያ ህግ ስር እንደሚመሩ ምዕራብያንም ይሁኑ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ አፍጋኒስታውያን ጥርጥር የላቸውም።  ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቡድኑ ቃል አቀባይ የተናገሩትም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ነው።« የእስልምና ህግ በሚፈቅደው መሰረት ሴቶች እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል። ሴቶች የማህበረሰቡ ዋና አካል ናቸው። እናከብራቸዋል። ሴቶች በሚፈለጉበት የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ይኖራቸዋል። በሸሪዓ ሕግ ስር ሆነው ማለት ነው።» ታሊባን ወደፊት ለሴቶች ክብር ይሰጣል ብለው ግን በተለይ በቡድኑ የተጠቁ እና ከዚህም ሸሽተው የተሰደዱ ሴቶች ፍፁም አያምኑም። እኝህ ሴት የደረሰባቸውን ይናገራሉ።  « የታሊባን ታጣቂዎች ኬላ ላይ በጠመንጃ አስፈራርተው ፣ ወንድ ልጆቼን ገድለው ፣ ምራቶቼን በግዳች ለጋብቻ ወሰዷቸው። ከእያንዳንዱ ቤት ሦስት ወይም አራት ሴት ልጆችን ወስደው አግብተዋል። »ለዚህም ነው የተሰደድነው ይላሉ። ሌላዋ ሴት ደግሞ ታሊባኖች ንቅሳት ያለባቸውን ሴቶች እንደሚገድሉ መስማቷን ትናገራለች። ከሸበርጋን አውራጃ የተፈናቀለችው ራሂማ ደግሞ“ታሊባኖች ሰዎችን ይደበድቡ እና ይዘርፉ ነበር። ፣ በቤተሰብ ውስጥ አንዲት ወጣት ልጃገረድ ወይም ባሏ የሞተባት ካለች በግዳጅ ይወስዷቸዋል። እኛ ክብራችንን ለመጠበቅ ስንል ሸሽተናል።»

Afghanistan Binnenvertriebene Afghanen Frauen Burkas
ን ከታሊባን ጋር የሚደረገውን ውጊያ ሸሽተው ከሰሜን አፍጋኒስታ የተፈናቀሉ ሴቶች እና ህፃናትምስል Rahmat Gul/AP Photo/picture alliance

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ  400 000 የሚሆኑ አፍጋናውያን የታሊባን ቡድንን ሽሽት እዛው ሀገር ውስጥ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ። የምዕራብ ሀገራት ኃይሎች ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን በሚያስወጡበት በዚህ ወቅት የሚሄዱበት የሌላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ሲሞክሩ ይታያል። አንድም ሁኔታው አስገድዷቸው አልያም በታሊባን ስር ሁኔታው ምን እንደሚመስል ለመታዘብ ጎዳና ወጥተዋል። አብዛኞቹ ጎዳና ላይ የሚታዩት ወንዶች ናቸው። ከጥቂት ሴቶች አንዷ የሆኑት እኝህ ሴት ደግሞ ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት ይናገራሉ። « ብዙ ወጣቶች በሰማዕትነት መሞታቸውን ለወጣቶች ይህንን መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ልጄ ከእነሱ አንዱ ነው። ከእንግዲህ ደም መፋሰስ ይብቃ። አንዱ ልጄ የፖሊስ ባልደረባ ነበር። የዛሬ ሁለት አመት ተገድሏል። ሌሎቹ በህይወት ተርፈውልኛል።»
ገና ካቡል በታሊባን እጅ ስር ከመውደቋ በፊት በርካታ ሴቶች የመዲናዋ ጎዳኖች ላይ መታየት መቀነሳቸውን ታዛቢዎች ይናገራሉ።  ሌሎች የአፍጋኒስታን ሴት የጥበብ ሰዎች ገና ቀናት አስቀድመው በታሊባን ቡድን ሊደርስባቸውን የሚችለውን ቅጣት ፍራቻ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የለጠፉትን እና የፃፉትን አጥፍተዋል፤ አልያም የግል ገፃቸውን ሰርዘዋል። ሻምሰያ ሀሳኒ በግራፊቲ የጎዳና የጥበብ ስራዎቿ የምትታወቅ አፍጋኒስታናዊ ናት። ካቡል በታሊባን ቁጥጥር ስር እንደዋለች የማህበራዊ መገናኛ ገፆቿ ፀጭ ረጭ ብለው ነበር። ብዙዎች የወጣት አርቲስቷ ሁኔታ አስግቷቸው ነበር። የሻምሰያ ሀሳኒ ማናጀር ለ DW እንደተናገሩት አርቲስቷ የምትገኝበትን ቦታ ሳይጠቅሱ ደህና መሆኗን ተናግረዋል።  አርቲስቷ የወንዶች የበላይነት በሚያመዝንበት አፍጋኒስታን ውስጥ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን በጥበብ ስራዎቿ ላይ በማሳየት ትታወቃለች። 

 ልደት አበበ/ ያን ቫልተር/ጋዛፋን አዴሊ

አዜብ ታደሰ