1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፉ ዛሬም ቀጥሏል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 13 2013

በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃና ግፍ ይቁም የሚሉ የተቃውሞ ሰልፎች ዛሬም ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተካኼዱ። በባሕር ዳር ከተማ ሱቆች ተዘግተውና የገበያ እንቅስቃሴ በከፊል በተቋረጠበት ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ተካኺዷል።

https://p.dw.com/p/3sLKY
Äthiopien Bahir Dar | Proteste gegen Ermordung und Vertreibung von ethnischen Amharas
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃና ግፍ ይቁም የሚሉ የተቃውሞ ሰልፎች ዛሬም ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተካኼዱ። ዛሬ ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ፣ ጋሸና፣ ኮንና ፍላቂት ከተሞች ይገኙባቸዋል። በሰሜን ሸዋ ዞንም የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የሰልፉ ተሳታፊዎች በስልክ ለዶይቸ ቬለ(DW)ገልጠዋል። በደብረብርሀን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በአጣዬና በሌሎች አጎራባች ከተሞች የተፈፀመውን ግድያ እና መፈናቀል ማውገዙን ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ ጤናው አዘነ ተናግረዋል።

«አጣዬ፣ ኤፍራታ፣ ሸዋሮቢት፣ ካራቆሪየ የተደረጉት ጦርነት ወረራ ነው። ወረራው ደግሞ አማራን ለማፈናቀል የተደረገ እና ይኼን ዓልሞ የተሠራ ነው። ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ አማራ ላይ አነጣጥሮ እየተከናወነ ያለው የዘር ማጽዳት ወንጀል ሃይ ሊባል ይገባዋል፤ መንግሥት በዚህ ያሳየው ዳተኝነት መንግሥታዊ ድጋፍ የተሰጠው የዘር ማጽዳት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው የሚል ነው።»

ላሊበላ ውስጥ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት አቶ ቸኮለ ታዘበውም ለዶይቼ ቬለ (DW)በስልክ እንደተናገሩት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ስሜታቸውን በተለያዩ መፈክሮች ሲገልፁ አርፍደዋል።

«ላሊበላም ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር። በሰልፉ ላይ የተለያዩ መልእክቶች የተላለፉበት ነው። የአማራን አጠቃላይ በክልሎችም ያሉ በክልሉ ውስጥም በአጣዬ እና በእዚህ በሰሜን ሸዋ አካባቢ የተከሰቱትን የሞቱ እና የንብረት መውደም አደጋዎች መንግሥት ችላ በማለት ላይ ነው ያለው አሁንም ከዚህ በኋላ የአማራን ሞት መታደግ መቻል አለበት ከማንም በፊት መንግሥት የሚል ነው የተላለፈው መልእክት።»

ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሰዓት በፊት ሱቆች ተዘግተውና የገበያ እንቅስቃሴ በከፊል በተቋረጠበት ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ተካኺዷል። በዛሬው ሰልፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል ተሰማርቶ ጥበቃ ሲያደርግ እንደነበር መመልከቱንም የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ዘግቧል። በአማራ ላይ የሚደርሰውን ግፍ በመቃወም ትናንትና በደሴ፣ በኮምቦልቻ በወልዲያ፣ በደብረማርቆስና በባህርዳር ከተሞች ሰልፎች ተካሂደዋል። በተያያዘ ዜና፦ በአማራ ክልል ትናንት የተደረጉ ሰልፎች በሰላም በመጠናቀቃቸው የክልሉ መንግስት አመስግኗል። በአማራ ክልል በአራቱም አቅጣጫዎች የጥፋት ኃይሎች ያሏቸው አካላት ጥቃት ለመፈፀም እየሞከሩ ነው ሲሉ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። በባሕር ዳር ከተማ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች እና ሆቴሎችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አሁንም ለአገልግሎት ክፍት አለመሆናቸውን ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ