1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአርሶ አደሮች የሚከናወኑ የምርጥ ዘር ብዜት ስራና ውጤታቸው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2013

የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምሕጻሩ የፋኦ መረጃ እንደሚያመለክተው  በዓለማችን በዋናነት ከሚመረቱ የሰብል ዓይነቶች ከሚሸፍኗቸው የመሬት ስፋት አንጻር የበቆሎ ምርት ከሩዝ እና ከስንዴ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ነገር ግን  ከሚያስገኘው የምርት ብዛት  አንጻር ቀዳሚ መሆኑን ነው መረጃው የሚያመለክተው።

https://p.dw.com/p/3kEOg
Äthiopien Addis Ababa | Bauern | Mais Produktion
ምስል Tamirat Dinssa/DW

የበቆሎ ምርጥ ዘር የማዳቀል ስራ እና አርሶ አደሩ

የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምሕጻሩ የፋኦ መረጃ እንደሚያመለክተው  በዓለማችን በዋናነት ከሚመረቱ የሰብል ዓይነቶች ከሚሸፍኗቸው የመሬት ስፋት አንጻር የበቆሎ ምርት ከሩዝ እና ከስንዴ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ነገር ግን  ከሚያስገኘው የምርት ብዛት  አንጻር ቀዳሚ መሆኑን ነው መረጃው የሚያመለክተው።  ኢትዮጵያ በበቆሎ ምርት ከምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ቀዳሚ ስትሆን ከአፍሪቃ ደቡብ አፍሪቃን ተከትላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ምርቱ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የሚመረት እንደመሆኑ እና ተፈላጊነቱም በዚያው ልክ እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ምርት ይገኝ ዘንድ  የግብርና ምርምር ማዕከላት  አራት አስርት ዓመታትን የተሻገሩ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ከመልክዓ ምድር እና የአየር ሁኔታ ጋር የተዛመዱ እንዲሁም የተሻለ ምርት የሚያስገኙ የተለያዩ የበቆሎ ዝርያዎች ተገኝተዋል። የመጠቀሚያ ጊዜአቸው አልፎ ከገበያ የወጡ እና አሁንም ድረስ አርሶ አደሩ እየተገለገለባቸው የሚገኙ ዝርያዎች እንዳሉም ይታወቃል። በዛሬው ዝግጅታችን በኢትዮጵያ በተለይ በምርምር የተገኙ እና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ የበቆሎ ዝርያዎች በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚከናወን  የዘር ብዜት ምን ያህል ውጤታማ ነው ስንል እንጠይቅበታለን። በእርግጥ ነው አርሶ አደሩ የምርጥ ዘር ብዜትን በማሳው ላይ ማከናወን ከጀመረ ውሎ አድሯል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከግብርና የምርምር ማዕከላት ውጭ ባሉ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የዘር ብዜት ስራው በስፋት መከናወን የተጀመረው እጎአ ከ2008 ዓ/ም አካባቢ ጀምሮ እንደሆነ ነው።  የዘር ማዳቀል እና ብዜት ስራው ወደ አርሶአደሩ ቄዬ እንዲመጡ ካስገደዱ ጉዳዮች አንደኛው ደግሞ ፈቃድ ወስደው በዘር ብዜት ስራው ላይ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች ለዘር ዝግጅቱ የሚሆን በቂ መሬት ለማግኘት ሲባል እንደሆነ ከባኮ ብሔራዊ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የዘር ብዜት ስራው ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ የሚከናወን እንደ መሆኑ መጠን   ብርቱ ጥንቃቄ እና የባለሙያዎች የቅርብ ክትትል የሚሹ ተግባራትንም ይጠይቁ ነበር። በባኮ ብሔራዊ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በየነ አበበ ቴክኖሎጂውን ወደ የአርሶ አደሩ ማሳ ማምጣት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ ፤አርሶአደሩ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ ቄዬው ድረስ መምጣቱ በሁለት መንገድ ጠቅሞታል። አንድም ቴክኖሎጂውን በቅርበት የመተዋወቅ ፤ ብሎም በየወቅቱ  በባለሞያ የሚደረግለት ድጋፍ ለውጤቱ ያግዘዋል። አለፍ ሲልም ሌሎች መሰል በግብርና ቴክኖሎጂ የማስፋፋት ስራ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን መንገድ ይከፍትለታል። በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ብዜቱ በመደበኛ ግብርና ከሚያመርተው ምርት የተሻለ ውጤት ያስገኝለታል ። ገቢውም በዚያው ልክ መሰረታዊ ልዩነት እንዳለው በመስኩ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ይናገራሉ ። በባኮ የምርምር ማዕከል ስር በማዳቀል በሚገኝ ምርጥ የበቆሎ ዘር በማባዛት ስራ ላይ በርካታ አርሶ አደሮች ተሰማርተዋል። ከእነዚሁ መካከል በኦሮሚያ ክልል  ጢሮ አፈታ ወረዳ በደቻ ነዺ ቀበሌ   የበቆሎ ዘር በማባዛት ስራ ላይ የተሰማሩት አርሶ  አደር አባ ጂሃድ ሀጂ  ምርጥ ዘር ማባዛት ከጀመሩ ወደ አስር ዓመታት ገደማ መድረሳቸውን ይናገራሉ።  

Äthiopien Addis Ababa | Bauern | Mais Produktion
ምስል Tamirat Dinssa/DW

«  አባ ጂሃድ ሃጂ እባላለሁ አርሶ አደር ነኝ። የምርጥ ዘር የሚባዛው እዚህ እኛጋ ነው። ይህን ዘር ማባዛት ከጀመርን ውለን አድረናል። አሁን ወደ አስር አመት ገደማ ሆኖናል። ዘሩን ስናባዛ በተከታታይ ከሶስት ዓመታት በላይ በመሬቱ ላይ መቀጠል አንችልም ። ምክንያቱ ደግሞ የመሬቱ ለምነት ስለሚቀንስ ነው። የመሬቱ ለምነት ሲመለስ እና የአየሩ ሁኔታ ጥሩ ሲሆን እንመለስበታለን። ከጥቅሙም አንጻር ብናየው ከየትኛው የእርሻ ስራችን ዘር ማባዛት ነው እኛን እየጠቀመን ያለው።»

Äthiopien Addis Ababa | Bauern | Mais Produktion
ምስል Tamirat Dinssa/DW

በኢትዮጵያ ከ26 በላይ ሀገር በቀል የግል የዘር አባዥ ድርጅቶች እንዳሉ  ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። እነዚህ ድርጅቶች አብዛኞቹ በተዳቀለ የበቆሎ የዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን የሚጠቅሰው መረጃው ኢትዮጵያ ከበቆሎ ውጭ ያሉ የጥራጥሬ ምርጥ ዘሮችን በውጭ ዘር አቅራቢ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ መሆኗን ያመለክታል። እንደዚያም ሆኖ የግል ዘር አባዥ ድርጅቶች በተለይ በአርሶአደር ማሳ ላይ ላይ የሚደረግ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት የጥራት ችግር እንደሚገጥማቸው ነው የሚነገረው ። የባኮ ብሔራዊ የበቆሎ  ምርምር ማዕከል ዳይሬክተሩ አቶ በየነ አበበ ሲናገሩ ።የተሻሻሉ የበቆሎ ዘሮች በኢትዮጵያ የተሻለ ምርት በማስገኘት ረገድ ውጤታማ እንደነበሩ የሚገልጹት አቶ በየነ ጊዜአቸውን ያጠናቀቁ ምርጥ ዘሮች በገበያ ላይ መቆየታቸው ሌላው የግብርና ምርምር ውጤትን ለማሸጋገር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች  አንደኛው  እንደሆነ ይገልጻሉ። BH660, BH661, 545, QPM ;እና በመሳሰሉ መጠርያዎች የሚታወቁ የበቆሎ ዝርያዎች የተወሰነ እና የተፈቀደላቸው ጊዜ ሲያበቃ ከገበያ መውጣት እንዳለባቸው ያስረዳሉ።መልክዓ ምድርን ፣ የአየር ሁኔታ እና ሌሎች ከበቆሎ ምርት ውጤታማነት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ታሳቢ በማድረግ የሚዘጋጀው ምርጥ ዘር የምርታማነቱ የቆይታ ጊዜው የተወሰነ ነው። በዚህም ጊዜው ሲያበቃ ከገበያ ወጥቶ በሌላ አዲስ ዝርያ ካልተተካ በአርሶ አደሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ።ለማሳያነትም ቢኤች 660 የተባለው የበቆሎ ዝርያ ጊዜው በማብቃቱ ቢኤች 661 በተባለዝርያ መተካቱን በማሳያነት ያነሳሉ።

ምርጥ ዘርን ከማባዛት እና ከማዳረስ ባሻገር በኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በመንግስት የግብርና ምርምር ማዕከላት እና በተለያዩ ዓለምአቀፍ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት በምርምር የተገኙ የግብርና  ውጤቶች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ሲሞከሩ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ አሁን ምርታማነታቸው የተረጋገጡ የበቆሎ ዝርያዎች በአማካይ በሄክታር 40 ኩንታል ምርት የሚያስገኙ ናቸው። ነገር ግን ሙሉ የእርሻ ግብዓት ተጠቅመው በባለሞያዎች የዘወትር ክትትል በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እስከ 120 ኩንታል ምርት ማምረ,ት እንደሚቻል ከአመታት በፊት በአንድ  የአርሶአደር ማሳ ላይ የተደረገ የሙከራ ስራ ያሳያል። አርሶ አደር መሐመድ አወል ሃጂ አባ መጫ ይባላሉ በዚያው የኦሮሚያ ክልል ኦሞ ናዳ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመሆን ይህንኑ ማሳካት እንደቻሉ ይናገራሉ።

Äthiopien Addis Ababa | Bauern | Mais Produktion
ምስል Tamirat Dinssa/DW

አርሶ አደር መሐመድ አወል ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ የምርጥ ዘር እና አስፈላጊውን የእርሻ ግብአት በአግባቡ ተጠቅመው እና በባለሞያዎች ታግዘው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 120 ኩንታል በቆሎ ማምረት እንደሚቻል ሲያሳዩ በወቅቱ ከእርሳቸው በተጨማሪ የአካባቢው አርሶ አደሮች ይኸንኑ ተሞክሮ እንዲቀስሙ የእርሻ ስራውን ሂደት እንዲከታተሉ ተደርጎ እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ተከታትሎ በመጡ አመታት ሂደቱን የተከታተሉ አርሶአደሮች ይቅርና እርሳቸውም ያንኑ መድገም እንዳልቻሉ ይገልጻሉ ።አርሶ አደሩ የግብርና የምርምር ግኝቶችን ውጤታማ እና ተከታታይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ሊገዳደሩ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን አቶ በየነ አበበ ይገልጻሉ።በእርግጥ ነው አርሶ አደር  መሐመድ አወል ከግብርና ቴክኖሎጂ ጋር መቀራረባቸው በተፈለገው ፍጥነት ባያራምዳቸውም ዛሬ በትራክተር ለማረስ ወደመሸጋገር መድረሳቸውን ገልጸውልኛል። ይህንን ቃለምልልስ ሳደርግ እንኳ የትራክተር ግዢ እየፈጸሙ መሆኑን ነው የነገሩኝ።  በኢትዮጵያ የምርጥ ዘር ብዜትን ጨምሮ በሚከናወኑ የግብርና ምርምር ስራዎች አርሶአደሩን በቀጥታ ማሳተፉ የምርምር ውጤትን በቀላሉ ለማሸጋገር ብሎም ተቀባይነት ማስገኘቱ አይቀርም። ነገር ግን ጥራትን ጨምሮ የአገልግሎት ጊዜአቸው የሚያበቃ የዝርያ አይነቶችን በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ከገበያ አለማስወጣት አርሶአደሩን ውጤት አልባ ማድረጉ አይቀርም። በተጨማሪም በሀገሪቱ በበቆሎ ላይ ብቻ ያተኮረው የግል ድርጅቶች የዘር ብዜት ስራ ወደ ሌሎች የሰብል አይነቶች ማሳፋፋት ካልተቻለ በግብርና ስራ ላይ ጥገኛ ለሆነች ሀገር ምርጥ ዘርን ጨምሮ ለግብርና ግብዓት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ  ማሳጣቱ አይቀርም ። 

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ