1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮጳ ስደተኞችን የማዳን ተግባር

ሐሙስ፣ ኅዳር 4 2007

ከአምስት ቀናት የባሕር መናወጥ ቆይታ በኋላ ከጣሊያኗ ላምፔዱዛ ደሴት እስከ ሊቢያ ጠረፍ የባሕሩ ሞገድ ረግቷል። ካለፈው አንድ ሣምንት አንስቶ ደግሞ «ቪያኖ ዶ ካስቴሎ» የተሰኘችው የፖርቺጊዝ ባሕር ቃኚ መርከብ ከላምፔዱዛ 55 ኪሎ ሜትሮች ደቡባዊ ርቀት ላይ መቅዘፍ ጀምራለች።

https://p.dw.com/p/1Dmb9
ምስል DW/B. Riegert
የመርከቢቱ ዋና ቀዛፊ (ካፒቴን) ዮርግ ሚግዌል ሞራይስ ከ40 ሠራተኞቻቸው ጋር ኹነው ባሕሩ ላይ አደጋ የተጋረጠባቸው ስደተኞች ካሉ ለማግኘት ቅኝት እያደረጉ ነው።
«እስካሁን ምንም አይነት ግዳጅ አልፈፀምንም። ሲመስለኝ በመጥፎ የዓየር ንብረት የተነሳ ሁኔታው የተረጋጋ ኹኗል።»
ካፒቴን ዮርጌ በመርከቢቱ ግዙፍ ራዳር በመታገዝ በባሕሩ ላይ ቅኝቱ የንግድ መርከቦችን፣ የዓሣ አስጋሪ ጀልባዎችን እና የተጠርጣሪ አካላትን እንቅስቃሴ ይከታተላሉ። እስካሁን አንድም የስደተኛ ጀልባ አላገኑም። ምናልባትም ግዙፍ ቃኚ መርከቢቱን እንኳን የሚያንገላታው ብርቱ የባሕር ነውጥ በእንጨት የተሰሩ ትንንሽ የስደተኛ ጀልባዎችን ብትንትናቸውን ሊያወጣ የሚችል ስለሆነም ይሆናል። «ፍሮንቴክስ» በሚባለው የአውሮጳ የድንበር ጠባቂ ኩባንያ ስር የምትንቀሳቀሰው የፖርቺጊዝ ባሕር ቃኚ መርከብ በመቶዎች የሚቆጠሩ የባሕር ላይ ስደተኞችን የማዳን አቅም አላት። ባሕሩ ላይ ስደተኞች ከተገኙም በመርከቢቱ ተጭነው በአቅራቢያው ከሚገኙ የጣሊያን የወደብ ከተማዎች ወደ አንዱ ይወሰዳሉ፤ እዚያም ፖሊሶች ይረከቡዋቸዋል። በአካባቢው ቅኝት ከሚያደርግ አውሮፕላኖች የፊንላንድ አውሮፕላን አብራሪ ላውሪ ፓካላ በላምፔዱዛ አካባቢ ስደተኞችን ለማግኘት ቅኝት ያደርጋሉ።
የ«ትሪቶን» ግብረ-ኃይል ባሕሩ ላይ ቅኝት ሲያደርግ
የ«ትሪቶን» ግብረ-ኃይል ባሕሩ ላይ ቅኝት ሲያደርግምስል DW/B. Riegert
«በተለምዶ እዚህ አካባቢ የሚመጡ ጀልባዎች በስደተኞች የተጨናነቁ ናቸው። ወዲያውኑም ልትለያቸው ትችላለህ። ምክንያቱም የጀልባዎቹ ጣሪያዎች ሳይቀሩ በስደተኞች የተጨናነቁ ናቸው። መደበኛ የዓሳ አስጋሪ ጀልባዎች ግን ጣሪያዎቻቸው ላይ የሚጭኑት የዓሳ ማስገሪያ ቁሳቁሶችን ነው።»
እጅግ ከርቀት መለየት የሚችል ራዳር እና ካሜራዎች የተገጠሙለት የፊንላንድ ቃኚ አውሮፕላን መጀመሪያ አካባቢ ተግባሩ በባልቲክ ባሕር ላይ የዘይት ንጣፎችን እና ብክለቶችን መፈለግ ነበር። አሁን አውሮፕላኑ ላምፔዱዛ ደሴት አካባቢ የሕይወት አድን ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
በባሕር ቅኝት ተግባር እጅግ አስፈላጊዎቹ ባሕር ቃኚ መርከቦች ብቻ ሳይሆኑ ከላምፔዱዛ እና ማልታ ደሴቶች አንስቶ ረዥም ርቀት በመጓዝ እስከ ሊቢያ ጠረፍ የሚያሥሡ ልዩ ራዳሮች እና ካሜራዎች የተገጠሙላቸው አውሮፕላኖችም ናቸው።#b #
ጣሊያን በበኩሏ ከአዲሱ የ«ትሪቶን» ግብረ-ኃይል በተጨማሪ «ማሬ ኖስትሩም» የሚል ስያሜ የሰጠችው በዓለም አቀፍ የባሕር ክልል የሚንቀሳቀስ የነፍስ አድን ተልዕኮ አላት። እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣኛል በሚል ግን የጣሊያን መንግስት ይኽን ተልዕኮ ለማቋረጥ እንደሚሻ ገልጧል። የ«ትሪቶን» ግብረ-ኃይል በኹለት አውሮፕላኖች፣ በአንድ ሔሊኮፕተር እና በስድስት ባሕር ቃኚ መርከቦች የተደራጀ ነው። ሆኖም የጣሊያኑ «ማሬ ኖስትሩም» በአንድ ዓመት ውስጥ ያከናወነውን ያህል ሕይወት የማዳን አቅም አይኖረውም ተብሏል። «ማሬ ኖስትሩም» በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ100,000 በላይ የባሕር ላይ ስደተኞችን ከባሕር ዓሳ ታድጓል። የ«ትሪቶን» ግብረ-ኃይል ሥራ ከጀመረ ሁለት ሣምንታትን አስቆጥሯል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ