1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮጳ የ2014 አበይት ክስተቶች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2007

ከ100 000 ሺ በላይ ስደተኞች አውሮጳ በተለይ ኢጣሊያ መግባታቸው፣ የቀኝ አክራሪዎች-የውጭ ሃገር ዜጎች ጥላቻ መባባስ፣ ብሎም በአውሮጳ ምክር ቤት አሸናፊ ሆነው መውጣት እንዲሁም ሌሎች አበይት ነጥቦች በዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ጥንቅራችን ተካቷል።

https://p.dw.com/p/1E9OU
Berlin 25 Jahre Mauerfall 09.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/Odd Andersen

ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩት የጎርጎሪዮሣዊው 20014 ዓም በአውሮጳ የተከሰቱ አበይት ነጥቦችን አጠር አጠር አድርገን ለመዳሰስ እንሞክራለን። የስደተኞች በአውሮጳ መበራከት እና የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻን የሚመለከተውን ነጥብ ቀዳሚ አድርገነዋል።

በ2014 ዓም ከ170 ሺህ በላይ ስደተኞች አውሮጳ ውስጥ ለጥገኝነት ያመለከቱ ሲሆን፤ በዛው መጠን የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻው በአውሮጳ መስፋፋቱ ይታያል። 2014 በጀርመንም ሆነ በአንዳንድ የአውሮጳ ሃገራት የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻ ጎልቶ የወጣበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የውጭ ሀገር ዜጎች በቀላሉ የማይታለፍ ትንኮሳ ሲደርስባቸው ተስተውሏል። ለአብነት ያኽል ጀርመን ውስጥ በ2014 በኹለት ወራት ብቻ በስደተኞች ላይ 20 ጥቃቶች መሰንዘራቸው ተመዝግቧል። ከነዚህ ጥቃቶች 12ቱ የስደተኞች መጠለያዎች ላይ እሳት በመለኮስ የተፈፀሙ ናቸው። እንዲህ አይነቱ ጥቃት ጀርመን ውስጥ በ1990ዎቹ ቀኝ አክራሪዎች በስደተኞች ላይ ያደርሱ የነበረውን ጥቃት የሚያስታውስ ነው ተብሏል። በጀርመን ለስደተኞች መብት የሚቆረቆረው በምኅፃሩ ፕሮ አዙል የተሰኘው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ጉይንተር ቡርክሐርድት።

ጉይንተር ቡርክሐርድት
ጉይንተር ቡርክሐርድትምስል picture-alliance/dpa

ጀርመን ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ላይ በቀኝ አክራሪዎች የሚደርሱ ጥቃቶች መባባሳቸውን የጀርመን መንግሥት በወቅቱ አስታውቋል ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የችግሩን አሳሳቢነት አጉልተው በማሳየት ላይ ናቸው ። ጀርመን ለጀርመኖች ብቻ የሚል አስተሳሰብ የሚያራምደው ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በምኅፃሩ NPD እና አማራጭ ለጀርመን AFD የተባሉት የጀርመን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ለታዘበ አደገኛነቱን በቀላሉ መረዳትእንደሚቻል ብዙዎች ይስማማሉ። ስለቀኝ አክራሪዎች ጥናት የሚያኪያሄዱት ተመራማሪው ሀዮ ፋንክ።

ይኽ የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻ በግለሰቦች እና በቡድኖች ብቻ የሚፈፀም ትንኮሳ ሆኖ የቀረ አይመስልም። ቀኝ አክራሪዎች እና ጸረ-የውጭ ሀገር ዜጋ አቀንቃኞች በአውሮጳ ምክር ቤት ውስጥ አሸናፊ ሆነው በርካታ ወንበሮችን ለመቆጣጠር ችለዋል። እነዚህ ቀኝ አክራሪዎች ወደ አውሮጳ ምክር ቤት የመጡት በየሃገራቱ በተደረጉ ምርጫዎች የበርካታ ሕዝብ ድምፅ አግኝተው ነው። በአውሮጳ ምክር ቤት የአረንጓዴው ፓርቲ ቡድን አማካሪ ሆነው ካለፉት 20 ዓመታት አንስቶ በማገልገል ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዋለልኝ ኅብረቱ የማኅበራዊ ፍትኅ እና የሠላም ጥያቄዎች ላይ ከመወያየት ይልቅ አወቃቀር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የአውሮጳ ምክር ቤት ሕንፃ
የአውሮጳ ምክር ቤት ሕንፃምስል Reuters/C. Hartmann

በየአምሥት ዓመቱ የሚደረገው የአውሮጳ ምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ በ28ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ውስጥ ተከናውኗል በ2014 ዓም። 500 ሚሊዮን የኅብረቱን አባል ሃገራት ሕዝብ የሚወክሉትን 751 እንደራሴዎች እንዲመርጥ ጥሪ የቀረበው ለ400 ሚልዮን መራጭ ሕዝብ ነበር። በምርጫው ስለ አውሮጳ በጥቂቱ ብዙውን ግን ለሀገራችን የሚሉ ብሔርተኛ እና ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የአብላጫውን የአውሮጳ ሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ችለዋል። የፈረንሣዩ Front National ፓርቲ ዩሮን አስቀርቶ በፈረንሣይ ፍራንክ መገበያየት ቁርጠኛ አቋሙ እንደሆነ ገልጧል። የብሪታንያው UKIP በበኩሉ ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት ሙሉ ለሙሉ እንድትወጣ ፍልጎቱ ፅኑዕ መሆኑን አሳውቋል። የፖለቲካ ተንታኞች 2014 ለአውሮፓ ኅብረት የፅልመት ዘመን ነው ሲሉ ብለውታል።

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን የሥራ ዘመናቸው በተጠናቀቀው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኡዌል ባሮሶ ምትክ አዲስ ፕሬዚዳንት የሾመው በ2014 ሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ነበር። የአውሮጳ ኅብረት የሉክዘምበርጉን የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ዦን ክላውድ ዩንከርን የኅብረቱ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሲሾም በብሪታኒያ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበት ነበር። ብሪታንያ የ59 ዓመቱን አዲስ ፕሬዚዳንት የተቃወመችው ለመፍቀሬ የአውሮጳ ውኅደት ያደላሉ፣ የኃይል ሚዛን ከኅብረቱ ይልቅ ወደ አባል ሃገራቱ እንዳያዘነብል ለሚታገሉ የብራስልስ ባለሥልጣናት ይወግናሉ በሚል ነው።

ዦን ክላውድ ዩንከር
ዦን ክላውድ ዩንከርምስል Imago

ወደ አውሮጳ በሚደረጉ ተደጋጋሚ የባሕር ላይ ጉዞዎች የስደተኞች ጀልባ መስጠም ተደጋጋሚ እልቂት ቢያስከትልም በ2014 ዓም ፍልሰቱ ግን ሊገታ አልቻለም። የአውሮጳ ኅብረት በባሕር ላይ ጉዞ የሚመጡ ስደተኞችን ሕይወት ለማዳን «Triton» የሚልስ ስያሜ የሰጠው የነፍስ አድን ሥራ የተጀመረው በ2014 ዓም ነው። ትሪቶን ሥራ ሲጀምር የጣሊያኑ «Mare Nostrum» ወይንም «ባሕራችን» የተሰኘው የባሕር ላይ ነፍስ አድን ተግባር ወዲያው ነበር የተቋረጠው። ከመቋረጡ በፊት ከ100 ሺህ የሚበልጡ የባሕር ላይ ስደተኞችን ከመስጠም ታድጓል። የማሬ ኖስትሩም ተልዕኮ የመቋረጡ ምክንያት የበጀት ችግር እንደሆነ ጣሊያን አስታውቃለች። በትሪቶን ተልዕኮ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 3,200 ስደተኞች ባሕር ውስጥ ጠልቀው እንዳይሞቱ ርዳታ ማድረጉን የጣሊያን የሀገር አስተዳደር ሚንስትር አንጀሊኖ አልፋኖ በባሕር ላይ ጉዞ ስለሚያልቁ ስደተኞች ሲናገሩ።

ሩስያ ለአውሮጳ የምትልከው ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ
ሩስያ ለአውሮጳ የምትልከው ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧምስል picture alliance/ZUMAPRESS.com

የዩክሬን ቀውስ ያስከተለው የምዕራባውያን እና የሩስያ ፍጥጫ በ2014 ዓም ጎልቶ የወጣ አበይት ክስተት ነበር። ይኽ ክስተት ዕልባት ሳይበጅለት ወደ 2015 ዓም በይደር የተሸጋገረ ጉዳይ ነው። በሩስያ ይደገፋሉ የሚባሉ ታጣቂዎች የዩክሬን ራስ-ገዝ የነበረችውን የልሳነ ምድሪቷ ክሬሚያን መንግሥት ፅሕፈት ቤት እና የምክር ቤት አዳራሽን በመቆጣጠር እንዲሁም በሕንፃዎቹ ላይ የሩሲያን ባንዲራ በመስቀል ነበር የክሬሚያን ቀውስ ያናሩት።ታጣቂዎቹ በዛም ብቻ አልተወሰኑም። የሩስያ ጦር ከዩክሬን መንግስት ጥቃት እንዲታደጋቸው ጥሪ ያስተላልፋሉ። አፍታም ሳይቆይ ባኪያሄዱት ውሳኔ ሕዝብ ልሳነ-ምድሪቱ ክሬሚያ ጠቅልላ ወደ ሩስያ ግዛትነት ተቀላቀለች። በወቅቱ የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል የነበሩ ጎረቤት ሃገራት በሩስያ ድርጊት እጅግ ተደናግጠው ነበር።

የአውሮጳ ኅብረትን ጨምሮ መላው ዓለም የሩስያን ድርጊት ማውገዝ ጀመረ። ሩስያ ግን ውልፍት አልል አለች። በተወሰኑ የሩስያ ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እና የንብረት ማንቀሳቀስ እግድ ማስተላለፋቸውን ዩናይትድ ስቴትስም የአውሮጳ ኅብረትም ተከታትለው አስታወቁ። ሩስያ ግን «ወይ ፍንክች፣ ያባ ቢላዋ ልጅ» ስትል በነዳጅ እና በጋዝ ሀብቷ ጥገኛ የሆኑት አውሮጳውያንን ማስፈራራቷን ተያይዛለች። ሩስያውያን በዩክሬን ቀውስ የተነሳ ከተጣለባቸው ማዕቀብ ባሻገር ልዑካኑ በአውሮጳ ኅብረት ድምፅ እንዳይሰጡም በሌሉበት ታግደዋል ። በአውሮጳ ምክር ቤት የጀርመን ልዑኩ አክሴል ፊሸር።

ዶኔትስክ እና ሉዋንስክ በተሰኙት የዩክሬን ምስራቃዊ ግዛት መፍቀሬ ሩስያ ታጣቂዎች ነፍጥ አንስተው ቀበሮ ጉድጋዳቸው ውስጥ እንደመሸጉ፣ ሩስያ እና አውሮጳ ብሎም መላው ዓለም እንደተፋጠጡ 2014 ሊገባደድ ዳር ዳር በማለት ላይ ነው።

በባልካን ሃገራት የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅም ሌላኛው የ2014 የአውሮጳ ክስተት ነበር። በባልካን ሃገራት እና መካከለኛው አውሮጳ ውስጥ በደረሰዉ ከፍተኛ የዉሃ መጥለቅለቅ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። በደቡብ ምሥራቅ አዉሮጳ በሚገኙ ነዋሪዎች መካከል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዉኃ መጥለቅለቁ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።

በባልካን የጎርፍ መጥለቅለቅ
በባልካን የጎርፍ መጥለቅለቅምስል picture-alliance/dpa

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመቱን የደፈነው በ2014 ዓም ነበር። ይኽንኑ ልዩ ቀን በማስታወስም የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮአሂም ጋውክ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ከ100 ዓመት በፊት የዓለም ጦርነት ያስነሳውን ቀን በአንድነት አስበው ውለዋል። እጎአ ከ1914 -1918 ዓም ድረስ በዘለቀው የ1ኛው የዓለም ጦርነት ከባድ ውጊያ ወደ 30,000 የሚጠጉ የፈረንሳይ እና የጀርመን መታደሮች ሕይወት ጠፍቷል። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙ 100 የፈረንሳይ እና የጀርመን ወጣቶች በዓለም ዙሪያ ዘረኝነትን እናጥፋ የሚል የሰላም መልዕክት አስተላልፈዋል። የጀርመን እና የፈረንሳይ ዕርቀ-ሠላም እና ወዳጅነት ለበርካታ የዓለማችን ክፍሎች አብነት ሊሆን የሚችል ነው ተብሏል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በአውሮጳ ምክር ቤት ቀርበው ንግግር ማድረጋቸው ሌላኛው የ2014 የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን መሪ ፍራንሲስ 750 የምክር ቤት አባላት እና እድምተኞች በተጨናነቁበት የአውሮጳ ምክር ቤት አዳራሽ ስደተኞችን በተመለከተ ሐዘን ባጠላበት ስሜት ንግግር አድርገው ነበር።

የዩክሬን ወታደር ከዩክሬን ሠንደቅ ፊት ቆሞ
የዩክሬን ወታደር ከዩክሬን ሠንደቅ ፊት ቆሞምስል Bulent Kilic/AFP/Getty Images

የበርሊን ግንብ የፈረሰበት 25ኛ ዓመት መታሠቢያ የተከናወነውም በዚሁ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት የጎርጎሪዮሣዊው 2014 ዓም ነበር። እጎአ ከነሐሴ ወር 1961 ዓ ም አንስቶ በርሊንን ከሁለት በመክፈል 28 ዓመታት የዘለቀው 15 ኪሎሜትር ርዝማኔ የነበረው የግንብ አጥር የፈረሰበት 25ኛ ዓመት ጀርመን ውስጥ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል። በአጠቃላይ 155 ኪሎሜትር ርዝማኔ የነበረው የድንበር አጥሩ ፈርሶ፤ ነው ምዕራብ ጀርመንንና ምሥራቅ ጀርመንን ከ25 ዓመት በፊት ለመዋሃድ የበቁት። አንዳንድ ቡድኖች የፈጠሩት የጎጥ፣ የመንደር እና የጎሣ መከ.ፋፈል ዓለምን እንዲህ ፍዳዋን በሚያበላበት ዘመን የጀርመን ውሕደት፤ ለአውሮጳና ለቀሪውም ዓለም አስተምህሮቱ ላቅ ያለ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ