1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞተር ሳይክል እገዳው የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያቶች አስከትሏል

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁለት ሳምንት በኋላ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጭ ሞተር ሳይክሎች በከተማይቱ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ትላንት አስታውቋል። በውሳኔው የተከፉ ሞተረኞች በአዲስ አበባ ቄራ በሚባለው ሰፈር አካባቢ ዛሬ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ሞክረው ፖሊስ እንደከለከላቸው ወጣቶቹ ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3Kn4W
Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche

በአዲስ አበባ የሞተር ሳይክል እገዳን ለመቃወም የሞከሩ በፖሊስ ተከለከሉ

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከሁለት ሳምንት በኋላ ፍቃድ የሌላቸው የሞተር ሳይክሎች ላይ ከእንቅስቃሴ እንደሚያግድ ትላንት ይፋ አድርጓል። እገዳው በከተማይቱ የሚስተዋለውን “ቅሚያ፣ ሌብነት እና ዝርፊያ” ለመቆጣጠር የተላለፈ እንደሆነም ገልጿል። የአስተዳደሩ ውሳኔ የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች አስከትሏል። 

በሞተርሳይክሎቻቸው አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደሩ ሞተረኞች ውሳኔውን አጥብቀው ተቃውመውታል። የከተማይቱ አስተዳደር ሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ የጣለው እገዳ "የለፍቶ አዳሪዎችን ጉሮሮ የሚዘጋ፣ ስራ አጥነትን የሚያበራክት እና ወንጀልንም የሚያስፋፋ ነው ሲሉ" ሞተረኞች፣ ባለንብረቶች እና የሞተር ደንበኞች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW) ሰጥተዋል። 

ውሳኔው "ተወልደው ባደጉበት አዲስ አበባ ባይተዋር እንዳደረጋቸው፤ ተደርጓል የተባለው ጥናትም ፍትሃዊነት የጎደለው ነው" ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ። "ፖሊስ ወንጀለኞችን በተለየ ስምሪት አሳድዶ መያዝ ሲገባው እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማሳለፉ አስጨንቆናል" ሲሉ አክለዋል። "ህግን አክብረው የሚሰሩ ሰዎችን በስመ ሌባ እና ዘራፊ" ከስራ ማገድ አግባብ አይደለም ሲል አንድ ሞተረኛ ውሳኔውን ተቃውሟል።

Äthiopien Addis Abeba Motorräder aus Stadt verbannt
ምስል DW/Solomon Musche

በአዲስ አበባ የግል በሚል የኮድ ቁጥር 2  ሰሌዳ የተለጠፈባቸው ሞተር ሳይክሎች እንደሚበዙ የትራፊክ ፖሊሶች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። በዚህ መልኩ ወደ ስራ የተሰማሩ ሞተረኞች አስተዳደሩ "ወይ አደራጅቶን ወይንም በሌላ አማራጭ ስራችንን እንድንሰራ ሊያደርግ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል። 

የከተማውን አስተዳደርን ውሳኔ ደግፈው የተናገሩት ደግሞ "ውሳኔው የህዝቡን ጭንቀትና ችግር ያገናዘበ ትክክለኛ እርምጃ ነው  ብለውታል። ህጋዊ የሆኑት እንዲሁ ከስራቸው ተፈናቅለው እንዳይቀሩ ግን መንግስት የሆነ አማራጭ ሊያዘጋጅ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

ሙሉ ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

ሰለሞን ሙጬ 

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ