1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዳማ ከተማ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ቆሰሉ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2012

በአዳማ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆሰሉ። በአዳማ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ፈቃዱ "በርካታ ሰዎች ተጎድተዋል። አብዛኞቹ የቆሰሉት በጥይት ነው። ሶስት ሰዎች ሞተዋል። አሁንም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አሉ" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3eZkk
Äthiopien, Adama
ምስል DW/M. Yonas Bula

በአዳማ ከተማ የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት በቀሰቀሰው ተቃውሞ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን አንድ የሕክምና ባለሙያ ተናገሩ። ዛሬ ማለዳ በአዳማ ከተማ በተቀሰቀሰው ከባድ ተቃውሞ የተሳተፉ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት መመታታቸውን በአዳማ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ፈቃዱ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

"በርካታ ሰዎች ተጎድተዋል። አብዛኞቹ የቆሰሉት በጥይት ነው። ሶስት ሰዎች ሞተዋል። አሁንም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አሉ" ብለዋል ዶክተር ደሳለኝ።

የሕክምና ባለሙያው "ከአስር በላይ በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ። የመኖሪያ ቤታቸው በእሳት እንደተቃጠለ ተናግረዋል" ሲሉ አክለዋል።

የፌድራል ፖሊስም ሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ቃል አቀባዮች ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ተከስቷል የተባለውን ተኩስ ጨምሮ በግድያው የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች እና አለመረጋጋት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል። ከኤምባሲው ደጃፍ ጭምር ተቃውሞ እንደነበር አረጋግጧል።

"ኹከት ከተከሰተ በኋላ በከተማው ፖሊስ ተሰማርቷል። በአሁኑ ወቅት ኹኔታው የተረጋጋ አይደለም። ተጨማሪ መረጃ እስኪሰጥ እባካችሁ በመኖሪያ ቤቶቻችሁ ቆዩ" የሚል መልዕክት አስተላልፏል።