1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ቀንድ አገራት ላይ የተሰጠ ትንታኔ

ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2005

«ጅቡቲ በፖለቲካም ይሁን በመገናኛ ብዙኃን ብዙም ትኩረት እየተሰጣት አይደለም»፣ «አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋ ባላት ግጭት ምናልባትም ለድርድር ዝግጁ የሚሆኑበት መንገድ ይፈጠራል» ይላሉ ዶክተር አኔተ ቬበር።

https://p.dw.com/p/16Ikw
2012_07_12_HornVonAfrika.psd

በቅርቡ ከጅቡቲ የተመለሱት ዶክተር አኔተ ቬበር በጀርመን የሳይንስ እና ፖለቲካ ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ናቸው። የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጉሌሕ መንግስት ተቃዋሚዎችን እና መገናኛ ብዙኃንን ይጨቁናሉ በመባል ይወቀሳል፤ ይሁንና ምዕራቢያውያን ጀርመንን ጨምሮ ይህንን መንግስት ሲያወግዙ አይሰማም። ይህም የጅቡቲ መንግስት በባህር ላይ ወንበዴዎች ላይ የተያዘውን ትግል ስለሚደግፉ ነው የሚሉም አልጠፉም። ቬበር በበኩላቸው የታዘቡት የሚከተለው ነው።

« ባለፉት ጊዜያት፣ የነበሩትን ምርጫዎች ብንመለከት፣ ለምሳሌ በ2011ም ይሁን በ2008 ጥሩ አልነበረም። 2011 ፖሊሶች ሰልፍ የወጡ ተቃዋሚዎችን ደብድበዋቸው ነበር። ስለነዚህ ጉዳዮች አውሮፓ ውስጥ ምንም ያህል አልተሰማም። ጅቡቲ በፖለቲካም ይሁን በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት አላገኘችም። ስለሆነም ከምዕራባውያን ውግዘት አይሰማም። »

ጅቡቲ ለአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካዊ ሒደት የጎላ ባይሆንም መካከለኛ ሚና ሊኖራት ይችላል። ለሶማሊያ እና ለሶማሌ ላንድ ጅቡቲ እንደ አማካሪ በመሆን ከዚህ ቀደም ሚና ተጫውታለች በአሁኑ ሰዓት ግን ጅቡቲ ለምዕራባዊያን የጦር ሰፈር ናት። ነው ያሉት ቬበር።

ጅቡቲ እና ኤርትራ ላለፉት 3 አመታት በድንበር የተነሳ ሲጋጩ እንደሰነበቱ ይታወሳል። በዚህስ ረገድ ምን አዲስ ነገር አለ? ዶክተር ቬበር

« የተረጋጋ ይመስላል። ድንበሩ ተከፍቷል። ቪዛም እየተሰጠ ነው። በአጠቃላይ ግን ጅቡቲ ከኤርትራ ጋ የበለጠ ችግር ስላላት ወደ ኢትዮጵያ ስታደላ ይታያል።ስለሆነም የአካባቢው አስታራቂ አካል ቢያስፈልግ ። ከኢትዮጵያ ጋ ሲነፃፀር በኤርትራ ላይ ተቃውሞ ስለምታሳይ ጅቡቲ አማካሪ ልትሆን አትችልም።»

በአፍሪቃ ቀንድ ለምዕራባዊያን ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አመራር ላይ ቬበር ትልቅ ተስፋ እንደሚጥሉ ተናግረዋል። ከዚህም አንዱ በጋራ ተባብሮ የመስራቱ ጉዳይ ነው።

« መንግስት ከህዝቡ ጋ በአንድነት በመሆን እንጂ በተቃራኒው ፖለቲካ እንደማያራምድ ተስፋ አለኝ፤ ከዚህ ሌላ ደግሞ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከትግራይ ስላልሆኑ እና የደቡብ ክልል ሰው በመሆናቸው፤ የኤርትራን እና የኢትዮጵያን ግጭት በስሜት ተሞልተው እንደማይወስኑ ይታመናል።ምናልባትም ለድርድር መንገዶች ይከፈቱ ይሆናል።»

ይህ ብቻ አይደለም። በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ያለው የአገዛዝ ስርዓትም ጥሩ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ባይ ናቸው። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና ሃሰን ሼክ መሐሙድ ስለሚተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ይላሉ ቬበር

« በዚህ አካባቢዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጠ/ሚኒስትርና እና ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት፣ አማፂያን ወይንም የጦር ኃላፊ ያልነበሩ እና በሌላ የስራ ዘርፍ ተሰልፈው የነበሩ በመሆናቸው ነው። ይህ ምናልባትም የአፍሪቃ ቀንድን ሁኔታ ሊያሻሽል ወይንም ሊለውጥ ይችላል። »

ተስፋ ብቻ ሳይሆን ስጋትም እንዳላቸው ቬበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፤በተለይ መንግስት ከፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋ የሚኖረውን የትብብር ስራ በተመለከተ፤

« ለኢትዮጵያ አዲስ አመት ነፃ የተለቀቁት በርካታ እስረኞች እንደ ትልቅ ተስፋ መታየት የለበትም። ይህ በየአመቱ የሚደረግ ነውና ትንሽ መጠበቅ ያስፈልጋል። ምማልባትም የተጠናከረ የምዕራባዊያን ግፊት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ተስፋ የማደርገው ተቃዋሚዎች አቋማቸውን እና መርሃ ገብራችውን ቢያስተዋውቁ በሚል ነው።

ኢትዮጵያ በምዕራብያኑ ዓይን የተረጋጋ መንግስት አላት በመባል ስለምትታይም የሚደረግላት የምዕራብዓዊያን ልገሳ ይቀጥላል ብለው እንደሚያምኑ ዶክተር ቬበር ተናግረዋል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ